ዕዝራ
3 በሰባተኛው ወር+ እስራኤላውያን* በከተሞቻቸው ውስጥ ነበሩ፤ እነሱም ልክ እንደ አንድ ሰው ሆነው በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 2 የየሆጼዴቅ ልጅ የሹዋና+ አብረውት የሚያገለግሉት ካህናት እንዲሁም የሰላትያል+ ልጅ ዘሩባቤልና+ ወንድሞቹ በእውነተኛው አምላክ ሰው በሙሴ ሕግ+ ውስጥ በተጻፈው መሠረት በላዩ ላይ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን ለማቅረብ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ።
3 በዙሪያቸው ባሉት አገሮች በሚኖሩት ሕዝቦች የተነሳ ፍርሃት አድሮባቸው+ የነበረ ቢሆንም መሠዊያውን በቀድሞ ቦታው ላይ ሠሩት፤ በላዩም ላይ ለይሖዋ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን ይኸውም ጠዋትና ማታ የሚቀርቡትን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ማቅረብ ጀመሩ።+ 4 ከዚያም በሕጉ ላይ በተጻፈው መሠረት የዳስ* በዓልን አከበሩ፤+ እንዲሁም በእያንዳንዱ ቀን እንዲቀርብ በታዘዘው መጠን መሠረት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን አቀረቡ።+ 5 ከዚያም የተለመደውን የሚቃጠል መባ፣+ ለአዲስ ጨረቃና+ ለተቀደሱት የይሖዋ በዓላት+ የሚቀርቡትን መባዎች እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ለይሖዋ የሚያቀርበውን የፈቃደኝነት መባ+ አቀረቡ። 6 የይሖዋ ቤተ መቅደስ መሠረት ገና ያልተጣለ ቢሆንም ከሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን+ አንስቶ ለይሖዋ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን ማቅረብ ጀመሩ።
7 ለድንጋይ ጠራቢዎቹና+ ለእጅ ጥበብ ባለሙያዎቹም+ ገንዘብ ሰጡ፤ በተጨማሪም የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ+ በሰጣቸው ፈቃድ መሠረት የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን ከሊባኖስ ወደ ኢዮጴ+ ወደብ ለሚያመጡ ለሲዶና እና ለጢሮስ ሰዎች የሚበላና የሚጠጣ ነገር እንዲሁም ዘይት ሰጡ።
8 በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እውነተኛው አምላክ ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የየሆጼዴቅ ልጅ የሹዋ እንዲሁም ካህናቱን፣ ሌዋውያኑንና ከምርኮ ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱትን+ በሙሉ ጨምሮ የቀሩት ወንድሞቻቸው ሥራውን ጀመሩ፤ የይሖዋን ቤት ሥራ በበላይነት እንዲቆጣጠሩም ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ ሌዋውያንን ሾሙ። 9 በመሆኑም የሹዋ፣ ወንዶች ልጆቹና ወንድሞቹ፣ ቃድሚኤልና ወንዶች ልጆቹ እንዲሁም የይሁዳ ወንዶች ልጆች ሌዋውያን ከሆኑት የሄናዳድ+ ወንዶች ልጆች፣ ከእነሱ ወንዶች ልጆችና ከወንድሞቻቸው ጋር ሆነው በእውነተኛው አምላክ ቤት ውስጥ ሥራውን የሚሠሩትን ሰዎች በበላይነት ለመቆጣጠር ተባበሩ።
10 የይሖዋን ቤተ መቅደስ የሚገነቡት ሰዎች መሠረቱን ሲጥሉ+ የክህነት ልብሳቸውን የለበሱት ካህናት በመለከት፣+ ሌዋውያኑ የአሳፍ ወንዶች ልጆች ደግሞ በሲምባል* የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት በሰጠው መመሪያ መሠረት ይሖዋን ለማወደስ ተነሱ።+ 11 “እሱ ጥሩ ነውና፤ ለእስራኤል የሚያሳየውም ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና”+ በማለት እየተቀባበሉ+ ይሖዋን ማወደስና ማመስገን ጀመሩ። ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ የይሖዋ ቤት መሠረት በመጣሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይሖዋን አወደሰ። 12 የቀድሞውን ቤት ያዩ ሽማግሌዎች ይኸውም ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑና ከአባቶች ቤት መሪዎች መካከል አብዛኞቹ የዚህ ቤት መሠረት ሲጣል ሲያዩ+ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ብዙዎቹ ግን በደስታ እልልታቸውን አቀለጡት።+ 13 ሕዝቡ ድምፁ ከሩቅ እስኪሰማ ድረስ ከፍ ባለ ድምፅ ይጮኽ ስለነበር ሰዎቹ የደስታውን እልልታ ከለቅሶው ጩኸት መለየት አልቻሉም ነበር።