37 “ከዚህም የተነሳ ልቤ ይመታል፤
ከስፍራውም ይዘላል።
2 የድምፁን ጉምጉምታ፣
ከአፉም የሚወጣውን ነጎድጓድ በጥሞና ስሙ።
3 ከሰማያት በታች ይልከዋል፤
መብረቁንም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይሰደዋል።+
4 ከዚያም በኋላ ድምፅ ያስተጋባል፤
ግርማ በተላበሰ ድምፅ ያንጎደጉዳል፤+
ድምፁም በሚሰማበት ጊዜ አይከለክለውም።
5 አምላክ በሚያስደንቅ ሁኔታ በድምፁ ያንጎደጉዳል፤+
እኛ መረዳት የማንችላቸውን ታላላቅ ነገሮች ያደርጋል።+
6 በረዶውን ‘ወደ መሬት ውረድ፣’+
ዶፉን ዝናብም ‘በኃይል ውረድ’ ይለዋልና።+
7 ሟች የሆነ ሰው ሁሉ ሥራውን እንዲያውቅ፣
አምላክ የእያንዳንዱን ሰው ሥራ ያስቆማል።
8 የዱር አራዊት ወደ ጎሬአቸው ይገባሉ፤
በዋሻዎቻቸውም ውስጥ ይቀመጣሉ።
9 አውሎ ነፋስ ከማደሪያው ይነፍሳል፤+
ቅዝቃዜም ከሰሜን ነፋሳት ይመጣል።+
10 በአምላክ እስትንፋስ በረዶ ይገኛል፤+
የተንጣለሉትም ውኃዎች ግግር በረዶ ይሆናሉ።+
11 አዎ፣ ደመናትን እርጥበት ያሸክማቸዋል፤
በደመናት መካከል መብረቁን ይበትናል፤+
12 እሱ በመራቸው አቅጣጫ ይሽከረከራሉ፤
ሰዎች በሚኖሩበት የምድር ገጽ ላይ እሱ ያዘዘውን ሁሉ ይፈጽማሉ።+
13 ለቅጣትም+ ሆነ ለምድሩ ሲል
አሊያም ታማኝ ፍቅር ለማሳየት ይህ እንዲሆን ያደርጋል።+
14 ኢዮብ ሆይ፣ ይህን ስማ፤
ቆም ብለህ የአምላክን ድንቅ ሥራዎች በጥሞና አስብ።+
15 አምላክ ደመናትን እንዴት እንደሚቆጣጠር፣
ከደመናውም እንዴት መብረቅ እንደሚያበርቅ ታውቃለህ?
16 ደመናት እንዴት እንደሚንሳፈፉ ታውቃለህ?+
እነዚህ፣ እውቀቱ ፍጹም የሆነው አምላክ ድንቅ ሥራዎች ናቸው።+
17 ምድር በደቡብ ነፋስ ጸጥ ስትል፣
ልብስህ የሚሞቀው ለምንድን ነው?+
18 እንደ ብረት መስተዋት ጠንካራ የሆኑትን ሰማያት፣
ከእሱ ጋር ልትዘረጋ ትችላለህ?+
19 ለእሱ የምንለውን ንገረን፤
ጨለማ ውስጥ ስለሆን መልስ መስጠት አንችልም።
20 እኔ መናገር እንደምፈልግ ለእሱ ማሳወቅ ያስፈልጋል?
ወይስ እሱ ሊያውቀው የሚገባ ነገር የተናገረ ሰው አለ?+
21 በሰማይ ላይ ብርሃን ቢኖርም፣
ነፋስ ነፍሶ ደመናቱን ካልበተነ፣
ሰዎች ብርሃኑን ማየት አይችሉም።
22 ከሰሜን ወርቃማ ጨረር ይወጣል፤
የአምላክ ግርማ+ አስፈሪ ነው።
23 ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከመረዳት ችሎታችን በላይ ነው፤+
ኃይሉ ታላቅ ነው፤+
ደግሞም ፍትሑንና ታላቅ ጽድቁን አይጥስም።+
24 ስለዚህ ሰዎች ሊፈሩት ይገባል።+
ጠቢብ ነን ብለው ለሚያስቡ ሁሉ ሞገስ አያሳይምና።”+