ኢያሱ
23 ይሖዋ እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፋቸው+ ከብዙ ጊዜ በኋላ፣ ኢያሱም አርጅቶና ዕድሜው ገፍቶ ሳለ+ 2 ኢያሱ እስራኤላውያንን በሙሉ፣ ሽማግሌዎቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ዳኞቻቸውንና አለቆቻቸውን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦+ “እንግዲህ እኔ አርጅቻለሁ፤ ዕድሜዬም ገፍቷል። 3 አምላካችሁ ይሖዋ ለእናንተ ሲል በእነዚህ ብሔራት ላይ ያደረገውን ሁሉ ራሳችሁ አይታችኋል፤ ምክንያቱም ለእናንተ እየተዋጋላችሁ የነበረው አምላካችሁ ይሖዋ ነው።+ 4 እኔም ከዮርዳኖስ አንስቶ በስተ ምዕራብ* እስከሚገኘው እስከ ታላቁ ባሕር* ድረስ ያጠፋኋቸውን ብሔራት ሁሉ ምድር+ ጨምሮ የቀሩትን ብሔራት ምድር+ ለየነገዶቻችሁ ርስት እንዲሆን በዕጣ አከፋፍዬ+ ሰጥቻችኋለሁ። 5 እነሱን ከፊታችሁ ያባረራቸው አምላካችሁ ይሖዋ ነው፤+ እሱም ለእናንተ ሲል አባረራቸው፤* እናንተም አምላካችሁ ይሖዋ በገባላችሁ ቃል መሠረት ምድራቸውን ወረሳችሁ።+
6 “እንግዲህ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ+ ውስጥ ከተጻፈው ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ፈጽሞ ዞር ሳትሉ+ ሕጉን ሁሉ ለመጠበቅና ለመፈጸም ደፋሮች ሁኑ፤ 7 እንዲሁም በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ብሔራት ጋር አትቀላቀሉ።+ ሌላው ቀርቶ የአማልክታቸውን ስም አታንሱ፤+ በእነሱም አትማሉ፤ ፈጽሞ አታገልግሏቸው እንዲሁም አትስገዱላቸው።+ 8 ከዚህ ይልቅ እስከዚህ ቀን ድረስ እንዳደረጋችሁት ሁሉ ከአምላካችሁ ከይሖዋ ጋር ተጣብቃችሁ ኑሩ።+ 9 ይሖዋ ታላላቅና ኃያላን ብሔራትን ከፊታችሁ ያባርራቸዋል፤+ እስከዚህ ቀን ድረስ አንድም ሰው ሊቋቋማችሁ አልቻለም።+ 10 አምላካችሁ ይሖዋ በገባላችሁ ቃል መሠረት+ ለእናንተ ስለሚዋጋላችሁ+ ከእናንተ አንዱ፣ ሺህ ሰው ያሳድዳል።+ 11 ስለዚህ አምላካችሁን ይሖዋን በመውደድ+ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።*+
12 “ይሁንና ወደ ኋላ ዞር ብትሉና ከእነዚህ ብሔራት መካከል ተርፈው ከእናንተ ጋር ከቀሩት+ ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ብትመሠርቱ፣ በጋብቻ ብትዛመዱ+ እንዲሁም እናንተ ከእነሱ ጋር ብትወዳጁ፣ እነሱም ከእናንተ ጋር ወዳጅነት ቢመሠርቱ 13 አምላካችሁ ይሖዋ ከዚህ በኋላ ለእናንተ ሲል እነዚህን ብሔራት እንደማያባርራቸው* በእርግጥ እወቁ።+ እነሱም አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር ላይ እስክትጠፉ ድረስ ወጥመድ፣ አሽክላ፣ ለጀርባችሁ ጅራፍ እንዲሁም በዓይናችሁ ውስጥ እንዳለ እሾህ ይሆኑባችኋል።+
14 “እንግዲህ እኔ መሞቻዬ ተቃርቧል፤* አምላካችሁ ይሖዋ ከገባላችሁ መልካም ቃል ሁሉ አንዲቷም እንኳ ሳትፈጸም እንዳልቀረች በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ* ታውቃላችሁ። ሁሉም ተፈጽሞላችኋል። ከመካከላቸው ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም።+ 15 ሆኖም አምላካችሁ ይሖዋ የገባላችሁ መልካም ቃል በሙሉ እንደተፈጸመላችሁ ሁሉ ይሖዋ አመጣባችኋለሁ ብሎ+ የተናገረውን ጥፋት ሁሉ* ያመጣባችኋል፤ አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድርም ያጠፋችኋል።+ 16 አምላካችሁ ይሖዋ እንድትጠብቁት ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ካፈረሳችሁ እንዲሁም ሄዳችሁ ሌሎች አማልክትን ካገለገላችሁና ለእነሱ ከሰገዳችሁ የይሖዋ ቁጣ በእናንተ ላይ ይነድዳል፤+ ከሰጣችሁም መልካም ምድር ላይ በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”+