የሐዋርያት ሥራ
2 በጴንጤቆስጤ* በዓል ቀን+ ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር። 2 ድንገትም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ ተቀምጠውበት የነበረውንም ቤት ሞላው።+ 3 የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ አረፉ፤ 4 ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤+ መንፈስም እንዲናገሩ ባስቻላቸው መሠረት በተለያዩ ቋንቋዎች* ይናገሩ ጀመር።+
5 በዚያን ጊዜ በምድር ዙሪያ ካለ አገር ሁሉ የመጡ ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም ነበሩ።+ 6 ስለዚህ ይህ ድምፅ በተሰማ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ እያንዳንዱም ሰው ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ። 7 ደግሞም ሕዝቡ እጅግ ተደንቀው እንዲህ አሉ፦ “እንዴ፣ እነዚህ እየተናገሩ ያሉት የገሊላ ሰዎች አይደሉም?+ 8 ታዲያ እያንዳንዳችን በአገራችን ቋንቋ* ሲናገሩ የምንሰማው እንዴት ነው? 9 እኛ ከጳርቴና፣ ከሜዶን፣+ ከኤላም፣+ ከሜሶጶጣሚያ፣ ከይሁዳ፣ ከቀጰዶቅያ፣ ከጳንጦስ፣ ከእስያ አውራጃ፣+ 10 ከፍርግያ፣ ከጵንፍልያ፣ ከግብፅ፣ በቀሬና አቅራቢያ ካሉት የሊቢያ አውራጃዎችና ከሮም የመጣን አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጥን ሰዎች፣+ 11 የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች ሁላችን ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እየሰማናቸው ነው።” 12 ስለዚህ ሁሉም ተገርመውና ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ይባባሉ ነበር። 13 ይሁን እንጂ ሌሎች “ያልፈላ የወይን ጠጅ* ተግተው ነው” በማለት አፌዙባቸው።
14 ጴጥሮስ ግን ከአሥራ አንዱ+ ጋር ተነስቶ በመቆም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፦ “እናንተ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ፣ አንድ ማወቅ ያለባችሁ ነገር ስላለ ንግግሬን በጥሞና አዳምጡ። 15 ጊዜው ገና ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ስለሆነ እነዚህ ሰዎች እናንተ እንዳሰባችሁት አልሰከሩም። 16 ከዚህ ይልቅ ይህ የሆነው በነቢዩ ኢዩኤል በኩል እንዲህ ተብሎ በተነገረው መሠረት ነው፦ 17 ‘አምላክ እንዲህ ይላል፦ “በመጨረሻው ቀን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ወጣቶቻችሁ ራእዮችን ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤+ 18 በዚያ ቀን በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀር ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ እነሱም ትንቢት ይናገራሉ።+ 19 በላይ በሰማይ ድንቅ ነገሮች፣ በታች በምድር ደግሞ ተአምራዊ ምልክቶች አሳያለሁ፤ ደም፣ እሳትና የጭስ ደመናም ይታያል። 20 ታላቁና ክብራማው የይሖዋ* ቀን ከመምጣቱ በፊት ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። 21 የይሖዋን* ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”’+
22 “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ይህን ቃል ስሙ፦ እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት በመካከላችሁ የፈጸማቸው ተአምራት፣ ድንቅ ነገሮችና ምልክቶች የናዝሬቱ ኢየሱስ በአምላክ የተላከ ሰው እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።+ 23 ይህ ሰው ለሞት አልፎ ተሰጠ። ይህም አምላክ አስቀድሞ የወሰነው ፈቃዱና* የሚያውቀው ነገር ነበር።+ እናንተም በክፉ ሰዎች እጅ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።+ 24 አምላክ ግን ከሞት ጣር* አላቆ አስነሳው፤+ ምክንያቱም ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለም።+ 25 ዳዊትም ስለ እሱ እንዲህ ይላል፦ ‘ይሖዋን* ሁልጊዜ በፊቴ* አደርገዋለሁ፤ እሱ በቀኜ ስለሆነ ፈጽሞ አልናወጥም። 26 ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሴት አደረገ። እኔም በተስፋ እኖራለሁ፤* 27 ምክንያቱም በመቃብር* አትተወኝም፤* ታማኝ አገልጋይህም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም።+ 28 የሕይወትን መንገድ አሳውቀኸኛል፤ በፊትህ በታላቅ ደስታ እንድሞላ ታደርገኛለህ።’+
29 “ወንድሞች፣ ከቀድሞ አባቶች አንዱ የሆነው ዳዊት እንደሞተና እንደተቀበረ+ እንዲሁም መቃብሩ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ እንደሚገኝ ለእናንተ በግልጽ እንድናገር ፍቀዱልኝ። 30 እሱ ነቢይ ስለነበረና አምላክ ከዘሮቹ አንዱን* በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ በመሐላ ቃል እንደገባለት ስላወቀ+ 31 አምላክ ክርስቶስን በመቃብር* እንደማይተወውና ሥጋውም እንደማይበሰብስ* አስቀድሞ ተረድቶ ስለ ትንሣኤው ተናገረ።+ 32 ይህን ኢየሱስን አምላክ ከሞት አስነሳው፤ እኛ ሁላችንም ለዚህ ነገር ምሥክሮች ነን።+ 33 ስለዚህ ወደ አምላክ ቀኝ ከፍ ከፍ ስለተደረገና+ ቃል የተገባውን ቅዱስ መንፈስ ከአብ ስለተቀበለ+ ይህን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። 34 ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ ሆኖም እሱ ራሱ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ ‘ይሖዋ* ጌታዬን እንዲህ ብሎታል፦ “በቀኜ ተቀመጥ፤ 35 ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ሁን።”’+ 36 ስለዚህ ይህን እናንተ በእንጨት ላይ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን+ አምላክ ጌታም+ ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ቤት ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።”
37 ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው እጅግ ተነክቶ ጴጥሮስንና የቀሩትን ሐዋርያት “ወንድሞች፣ ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሏቸው። 38 ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፦ “ንስሐ ግቡ፤+ እያንዳንዳችሁም ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ+ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤+ የመንፈስ ቅዱስንም ነፃ ስጦታ ትቀበላላችሁ። 39 ምክንያቱም የተስፋው ቃል+ ለእናንተና ለልጆቻችሁ እንዲሁም ይሖዋ* አምላካችን ወደ ራሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነው።”+ 40 በሌላ ብዙ ቃልም በሚገባ* መሠከረላቸው፤ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” እያለም አጥብቆ አሳሰባቸው።+ 41 ስለዚህ ቃሉን በደስታ የተቀበሉ ተጠመቁ፤+ በዚያም ቀን 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች* ተጨመሩ።+ 42 የሐዋርያቱንም ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ፤ አንድ ላይ ይሰበሰቡ፣* ምግባቸውንም አብረው ይበሉ+ እንዲሁም በጸሎት ይተጉ ነበር።+
43 ሰው ሁሉ* ፍርሃት አደረበት፤ ሐዋርያቱም ብዙ ድንቅ ነገሮችና ተአምራዊ ምልክቶች ያደርጉ ጀመር።+ 44 ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውም ነገር ሁሉ የጋራ ነበር፤ 45 በተጨማሪም ያላቸውን ሀብትና ንብረት በመሸጥ+ ገንዘቡን ለሁሉም አከፋፈሉ። ለእያንዳንዱም ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ሰጡ።+ 46 በየዕለቱም በአንድ ልብ ሆነው በቤተ መቅደሱ አዘውትረው ይገኙ ነበር፤ ምግባቸውንም በተለያዩ ቤቶች ይበሉ የነበረ ሲሆን የሚመገቡትም በታላቅ ደስታና በንጹሕ ልብ ነበር፤ 47 አምላክንም ያወድሱ የነበረ ከመሆኑም በላይ በሰው ሁሉ ፊት ሞገስ አግኝተው ነበር። ይሖዋም* የሚድኑ ሰዎችን በየዕለቱ በእነሱ ላይ ይጨምር ነበር።+