ለተሰሎንቄ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ
3 ስለዚህ ከዚህ በላይ መታገሥ ስላልቻልን* በአቴንስ+ ብቻችንን መቅረት እንደሚሻል ተሰማን፤ 2 በመሆኑም እምነታችሁ ይጠነክር ዘንድ እንዲያጸናችሁ እንዲሁም እንዲያበረታታችሁ ጢሞቴዎስን+ ላክንላችሁ፤ እሱ ወንድማችንና ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች የሚያውጅ የአምላክ አገልጋይ* ነው፤ 3 የላክነውም ማንም በእነዚህ መከራዎች እንዳይናወጥ* ነው። እንዲህ ካሉ መከራዎች ማምለጥ እንደማንችል እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና።+ 4 አብረናችሁ በነበርንበት ጊዜ መከራ መቀበላችን እንደማይቀር አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ ደግሞም እንደምታውቁት ይኸው ነገር ደርሷል።+ 5 ስለዚህ ከዚህ በላይ መታገሥ ባልቻልኩ ጊዜ ስለ ታማኝነታችሁ ለመስማት እሱን ላክሁት፤+ ይህን ያደረግኩት ምናልባት ፈታኙ+ በሆነ መንገድ ፈትኗችሁ ድካማችን ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ስለሰጋሁ ነው።
6 ይሁንና ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ አሁን ወደ እኛ መጥቶ+ ስለ ታማኝነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ ምሥራች አብስሮናል፤ ደግሞም እኛን ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስታውሱንና እኛ እናንተን ለማየት እንደምንናፍቅ ሁሉ እናንተም እኛን ለማየት እንደምትናፍቁ ነግሮናል። 7 ወንድሞች፣ በችግራችንና በመከራችን ሁሉ በእናንተና ባሳያችሁት ታማኝነት የተነሳ የተጽናናነው ለዚህ ነው።+ 8 ምክንያቱም ከጌታ ጋር ባላችሁ ዝምድና ጸንታችሁ የምትቆሙ ከሆነ ሕይወታችን ይታደሳል።* 9 በእናንተ የተነሳ በአምላካችን ፊት ለተሰማን ታላቅ ደስታ በአጸፋው ስለ እናንተ ምስጋናችንን ለአምላክ ለመግለጽ ምን ማድረግ እንችላለን? 10 ፊታችሁን ማየትና ከእምነታችሁ የጎደለውን ነገር ማሟላት እንችል ዘንድ አቅማችን በሚፈቅደው መጠን ሌት ተቀን ምልጃ እናቀርባለን።+
11 አሁንም አምላካችንና አባታችን እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ወደ እናንተ እንድንመጣ መንገዳችንን ያቅኑልን። 12 በተጨማሪም እኛ ለእናንተ ፍቅር እንዳለን ሁሉ እርስ በርስም ሆነ ለሰዎች ሁሉ የምታሳዩትን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ ብሎም ያትረፍርፍላችሁ፤+ 13 ይህም ጌታችን ኢየሱስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር በሚገኝበት ጊዜ+ በአምላካችንና በአባታችን ፊት ልባችሁን እንዲያጸናና ያላንዳች እንከን ቅዱስ እንዲያደርግ ነው።+