ሁለተኛ ነገሥት
13 የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ+ ልጅ ኢዮዓስ+ በነገሠ በ23ኛው ዓመት የኢዩ+ ልጅ ኢዮዓካዝ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያም ሆኖ ለ17 ዓመት ገዛ። 2 እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ እንዲሁም የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ያደረገውን ኃጢአት መሥራቱን ቀጠለ።+ ከዚያም አልራቀም። 3 በመሆኑም የይሖዋ ቁጣ+ በእስራኤል ላይ ነደደ፤+ በዘመናቸውም ሁሉ በሶርያ ንጉሥ በሃዛኤል+ እጅና በሃዛኤል ልጅ በቤንሃዳድ+ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
4 ከጊዜ በኋላ ኢዮዓካዝ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ለመነ፤ ይሖዋም ሰማው፤ ምክንያቱም የሶርያ ንጉሥ በእስራኤላውያን ላይ ያደረሰውን ጭቆና አይቶ ነበር።+ 5 ስለሆነም ይሖዋ ለእስራኤላውያን ከሶርያውያን እጅ ነፃ የሚያወጣ አዳኝ ሰጣቸው፤+ እስራኤላውያንም እንደቀድሟቸው በየቤታቸው መኖር ጀመሩ።* 6 (እነሱ ግን የኢዮርብዓም ቤት እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ካደረገው ኃጢአት ዞር አላሉም።+ ይህን ኃጢአት መፈጸማቸውን ቀጠሉ፤* የማምለኪያ ዓምዱም*+ በሰማርያ እንደቆመ ነበር።) 7 ኢዮዓካዝ የቀረው 50 ፈረሰኞች፣ 10 ሠረገሎችና 10,000 እግረኛ ወታደሮች ብቻ ያሉት ሠራዊት ነበር፤ ምክንያቱም የሶርያ ንጉሥ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ረጋግጦ ደምስሷቸው ነበር።+
8 የቀረው የኢዮዓካዝ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉና ኃያልነቱ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 9 በመጨረሻም ኢዮዓካዝ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ቀበሩት፤+ ልጁም ኢዮዓስ በምትኩ ነገሠ።
10 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓስ+ በነገሠ በ37ኛው ዓመት የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። 11 እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ሁሉ ዞር አላለም።+ እነዚህን ኃጢአቶች መፈጸሙን* ቀጠለ።
12 የቀረው የኢዮዓስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉና ኃያልነቱ እንዲሁም ከይሁዳ ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንዴት እንደተዋጋ+ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 13 በመጨረሻም ኢዮዓስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓምም*+ በዙፋኑ ተቀመጠ። ኢዮዓስም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር በሰማርያ ተቀበረ።+
14 ኤልሳዕ+ ለሞት በዳረገው በሽታ ተይዞ በነበረበት ወቅት የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ወደ እሱ ወርዶ “አባቴ፣ አባቴ! የእስራኤል ሠረገላና ፈረሰኞች!”+ በማለት ላዩ ላይ ተደፍቶ አለቀሰ። 15 ኤልሳዕም “በል ደጋንና ቀስቶች አምጣ” አለው። እሱም ደጋንና ቀስቶች አመጣ። 16 ከዚያም ኤልሳዕ የእስራኤልን ንጉሥ “ደጋኑን በእጅህ ያዝ” አለው። ንጉሡም ደጋኑን በእጁ ያዘ፤ በመቀጠልም ኤልሳዕ እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ ጫነ። 17 ከዚያም “በምሥራቅ በኩል ያለውን መስኮት ክፈት” አለው። እሱም ከፈተ። ኤልሳዕም “አስፈንጥር!” አለው። እሱም አስፈነጠረ። ኤልሳዕም “የይሖዋ የድል* ቀስት፤ በሶርያ ላይ የሚወነጨፍ የድል* ቀስት! ሶርያውያንን ድምጥማጣቸውን እስክታጠፋ ድረስ አፌቅ+ ላይ ትመታቸዋለህ”* አለው።
18 ኤልሳዕ በመቀጠል “ቀስቶቹን ያዝ” አለው፤ እሱም ያዘ። ከዚያም የእስራኤልን ንጉሥ “መሬቱን ውጋ” አለው። እሱም መሬቱን ሦስት ጊዜ ወግቶ አቆመ። 19 በዚህ ጊዜ የእውነተኛው አምላክ ሰው በእሱ ላይ ተቆጥቶ እንዲህ አለው፦ “መሬቱን አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መውጋት ነበረብህ! እንደዚያ ብታደርግ ኖሮ ሶርያውያንን ሙሉ በሙሉ ድምጥማጣቸውን ታጠፋ ነበር፤ አሁን ግን ሶርያን የምትመታው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው።”+
20 ከዚያም ኤልሳዕ ሞተ፤ ተቀበረም። በዓመቱ መጀመሪያ* ላይ ወደ ምድሪቱ ዘልቀው የሚገቡ የሞዓባውያን ወራሪ ቡድኖች+ ነበሩ። 21 የተወሰኑ ሰዎች አንድ ሰው ሊቀብሩ ሲሉ ወራሪውን ቡድን ተመለከቱ፤ ስለዚህ ሰውየውን ኤልሳዕ የተቀበረበት ቦታ ውስጥ ወርውረው እየሮጡ ሄዱ። ሰውየውም የኤልሳዕን አፅም በነካ ጊዜ ሕያው ሆነ፤+ በእግሩም ቆመ።
22 የሶርያ ንጉሥ ሃዛኤል+ በኢዮዓካዝ ዘመን ሁሉ እስራኤልን ይጨቁን ነበር።+ 23 ሆኖም ይሖዋ ከአብርሃም፣+ ከይስሐቅና+ ከያዕቆብ+ ጋር ስለገባው ቃል ኪዳን ሲል ሞገስና አሳቢነት አሳያቸው፤ ምሕረትም አደረገላቸው።+ ሊያጠፋቸው አልፈለገም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ከፊቱ አላስወገዳቸውም። 24 የሶርያ ንጉሥ ሃዛኤል በሞተ ጊዜ ልጁ ቤንሃዳድ በእሱ ምትክ ነገሠ። 25 ከዚያም የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ፣ ሃዛኤል ከአባቱ ከኢዮዓካዝ ላይ በጦርነት የወሰዳቸውን ከተሞች ከሃዛኤል ልጅ ከቤንሃዳድ አስመለሰ። ኢዮዓስ ሦስት ጊዜ መታው፤*+ የእስራኤልንም ከተሞች መልሶ ያዘ።