አንደኛ ሳሙኤል
10 ሳሙኤልም የዘይት ዕቃውን አንስቶ ዘይቱን በሳኦል ራስ ላይ አፈሰሰው።+ ከዚያም ሳመውና እንዲህ አለው፦ “በርስቱ+ ላይ መሪ እንድትሆን ይሖዋ ቀብቶህ የለም?+ 2 ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ በቢንያም ግዛት ውስጥ በምትገኘው በጸልጻህ ባለው የራሔል መቃብር+ አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፤ እነሱም እንዲህ ይሉሃል፦ ‘ስትፈልጋቸው የነበሩት አህዮች ተገኝተዋል፤ አባትህ ግን ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ+ ስለ እናንተ እየተጨነቀ ነው። ደግሞም “የልጄን ነገር ምን ባደርግ ይሻላል?” እያለ ነው።’ 3 አንተም ከዚያ ተነስተህ ታቦር የሚገኘው ትልቅ ዛፍ አጠገብ እስክትደርስ ድረስ ጉዞህን ቀጥል፤ እዚያም ሦስት ሰዎች በቤቴል+ ወደሚገኘው ወደ እውነተኛው አምላክ ሲወጡ ታገኛለህ፤ እነሱም አንደኛው ሦስት የፍየል ግልገል፣ ሌላኛው ሦስት ዳቦ፣ ሌላኛው ደግሞ በእንስራ የወይን ጠጅ ይዘዋል። 4 እነዚህ ሰዎች ስለ ደህንነትህ ከጠየቁህ በኋላ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፤ አንተም ዳቦዎቹን ተቀበላቸው። 5 ከዚህ በኋላ የፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ወዳለበት ወደ እውነተኛው አምላክ ኮረብታ ትመጣለህ። ወደ ከተማዋም በምትደርስበት ጊዜ ትንቢት እየተናገረ ከኮረብታው የሚወርድ አንድ የነቢያት ቡድን ታገኛለህ፤ ከፊት ከፊቱም ባለ አውታር መሣሪያ፣ አታሞ፣ ዋሽንትና በገና የሚጫወቱ ሰዎች ይሄዳሉ። 6 የይሖዋ መንፈስ ኃይል ይሰጥሃል፤+ አንተም ከእነሱ ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ ተለውጠህም እንደ ሌላ ሰው ትሆናለህ።+ 7 እነዚህ ምልክቶች ሲፈጸሙ ስታይ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤ ምክንያቱም እውነተኛው አምላክ ከአንተ ጋር ነው። 8 ከዚያም ከእኔ ቀድመህ ወደ ጊልጋል+ ውረድ፤ እኔም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን ለማቅረብ አንተ ወዳለህበት እወርዳለሁ። እኔ ወደ አንተ እስክመጣ ድረስ ሰባት ቀን መጠበቅ አለብህ። ከዚያም ምን ማድረግ እንዳለብህ አሳውቅሃለሁ።”
9 ሳኦልም ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን ሲያዞር አምላክ የሳኦል ልብ ወደ ሌላ ሰው ልብ እንዲለወጥ አደረገ፤ እነዚህም ሁሉ ምልክቶች በዚያው ቀን ተፈጸሙ። 10 በመሆኑም ከዚያ ተነስተው ወደ ኮረብታው ሄዱ፤ አንድ የነቢያት ቡድንም አገኘው። ወዲያውም የአምላክ መንፈስ ኃይል ሰጠው፤+ እሱም አብሯቸው ትንቢት መናገር ጀመረ።+ 11 ቀደም ሲል ያውቁት የነበሩት ሁሉ ከነቢያቱ ጋር ሆኖ ትንቢት ሲናገር ሲያዩት እርስ በርሳቸው “የቂስ ልጅ ምን ሆኗል? ሳኦልም ከነቢያት አንዱ ሆነ እንዴ?” ተባባሉ። 12 ከዚያም የአካባቢው ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው “ለመሆኑ የእነሱስ አባት ማን ነው?” አለ። “ሳኦልም ከነቢያት አንዱ ሆነ እንዴ?” የሚል ምሳሌያዊ አባባል የኖረው በዚህ የተነሳ ነው።+
13 እሱም ትንቢት ተናግሮ ሲጨርስ ወደ ኮረብታው መጣ። 14 በኋላም የሳኦል አባት ወንድም ሳኦልንና አገልጋዩን “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ሳኦልም “አህዮቹን ፍለጋ ሄደን ነበር፤+ ሆኖም በዚያ ልናገኛቸው ስላልቻልን ወደ ሳሙኤል ሄድን” አለው። 15 የሳኦልም አጎት “እስቲ ንገረኝ፣ ሳሙኤል ምን አላችሁ?” አለው። 16 ሳኦልም መልሶ አጎቱን “አህዮቹ መገኘታቸውን በትክክል ነገረን” አለው። ይሁን እንጂ ሳሙኤል ስለ ንግሥና የነገረውን ነገር አልነገረውም።
17 ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን በምጽጳ+ በይሖዋ ፊት እንዲሰበሰብ ከጠራ በኋላ 18 እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤልን ከግብፅ ያወጣሁት እንዲሁም ከግብፅ እጅና+ ይጨቁኗችሁ ከነበሩት መንግሥታት ሁሉ እጅ የታደግኳችሁ እኔ ነኝ። 19 ዛሬ ግን እናንተ ከመከራችሁና ከጭንቀታችሁ ሁሉ ያዳናችሁን አምላካችሁን አንቀበልም በማለት+ “አይሆንም፣ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን” አላችሁ። ስለዚህ አሁን በየነገዳችሁና በየሺህ ምድባችሁ* ሆናችሁ በይሖዋ ፊት ቁሙ።’”
20 ስለዚህ ሳሙኤል የእስራኤል ነገዶች በሙሉ እንዲቀርቡ አደረገ፤+ ከእነሱም መካከል የቢንያም ነገድ ተመረጠ።+ 21 ከዚያም የቢንያም ነገድ በየቤተሰቡ ሆኖ እንዲቀርብ አደረገ፤ የማጥራውያን ቤተሰብም ተመረጠ። በመጨረሻም የቂስ ልጅ ሳኦል ተመረጠ።+ ሆኖም ፈልገው ሊያገኙት አልቻሉም። 22 ስለዚህ “ለመሆኑ ሰውየው እዚህ መጥቷል?” በማለት ይሖዋን ጠየቁ።+ ይሖዋም “ያውላችሁ፣ ጓዙ መካከል ተደብቋል” አላቸው። 23 በመሆኑም ሮጠው ከዚያ አመጡት። እሱም በሕዝቡ መካከል በቆመ ጊዜ ከትከሻው በላይ ዘለግ ብሎ በቁመት ከሌሎቹ ሰዎች ሁሉ በልጦ ይታይ ነበር።+ 24 ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ “ይሖዋ የመረጠውን ሰው አያችሁት?+ ከሕዝቡ ሁሉ መካከል እንደ እሱ ያለ የለም” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” በማለት መጮኽ ጀመረ።
25 ሳሙኤልም ለነገሥታት ምን ሊደረግላቸው እንደሚገባ ለሕዝቡ ተናገረ፤+ እንዲሁም በመጽሐፍ ጽፎ በይሖዋ ፊት አስቀመጠው። ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን ሁሉ ወደየቤቱ አሰናበተ። 26 ሳኦልም ይሖዋ ልባቸውን ባነሳሳው ተዋጊዎች ታጅቦ በጊብዓ ወዳለው ቤቱ ሄደ። 27 አንዳንድ የማይረቡ ሰዎች ግን “ይህ ሰው እንዴት ሊያድነን ይችላል?” አሉ።+ በመሆኑም ናቁት፤ ምንም ዓይነት ስጦታም አላመጡለትም።+ እሱ ግን ዝም አለ።*