ሁለተኛ ሳሙኤል
11 በዓመቱ መባቻ፣* ነገሥታት ለውጊያ በሚዘምቱበት ወቅት ዳዊት አሞናውያንን እንዲያጠፉ ኢዮዓብን፣ አገልጋዮቹንና መላውን የእስራኤል ሠራዊት ላከ፤ እነሱም ራባን+ ከበቡ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት ኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር።+
2 አንድ ቀን ምሽት፣* ዳዊት ከአልጋው ተነስቶ በንጉሡ ቤት* ሰገነት ላይ ይንጎራደድ ነበር። በሰገነቱ ላይ ሳለም አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ እሷም በጣም ውብ ነበረች። 3 ዳዊትም ስለ ሴትየዋ ማንነት እንዲጠይቅ አንድ ሰው ላከ፤ ሰውየውም “ሴቲቱ የኤሊያም+ ልጅ፣ የሂታዊው+ የኦርዮ+ ሚስት ቤርሳቤህ+ ናት” ብሎ ነገረው። 4 ከዚያም ዳዊት ሴትየዋን እንዲያመጧት መልእክተኞችን ላከ።+ እሷም ወደ እሱ ገባች፤ አብሯትም ተኛ።+ (ይህ የሆነው ራሷን ከርኩሰቷ* እያነጻች ሳለ ነበር።)+ በኋላም ሴትየዋ ወደ ቤቷ ተመለሰች።
5 ሴትየዋም ፀነሰች፤ ለዳዊትም “አርግዣለሁ” የሚል መልእክት ላከችበት። 6 በዚህ ጊዜ ዳዊት “ሂታዊውን ኦርዮን ወደ እኔ ላከው” በማለት ወደ ኢዮዓብ መልእክት ላከበት። በመሆኑም ኢዮዓብ ኦርዮን ወደ ዳዊት ላከው። 7 ኦርዮም በመጣ ጊዜ ዳዊት ስለ ኢዮዓብ ደህንነት፣ ስለ ሠራዊቱ ሁኔታና ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው። 8 ከዚያም ዳዊት ኦርዮን “እንግዲህ ወደ ቤትህ ውረድና ዘና በል”* አለው። ኦርዮ ከንጉሡ ቤት ወጥቶ በሄደ ጊዜ የንጉሡ የደግነት ስጦታ* ተላከለት። 9 ኦርዮ ግን ከሌሎቹ የጌታው አገልጋዮች ጋር በንጉሡ ቤት ደጃፍ ላይ ተኛ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም። 10 በመሆኑም ለዳዊት “ኦርዮ እኮ ወደ ቤቱ አልወረደም” ብለው ነገሩት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ኦርዮን “ከመንገድ ገና መግባትህ አይደለም እንዴ? ታዲያ ወደ ቤትህ ያልወረድከው ለምንድን ነው?” አለው። 11 ኦርዮም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ታቦቱም+ ሆነ እስራኤልና ይሁዳ ያሉት ዳስ ውስጥ ነው፤ ጌታዬ ኢዮዓብና የጌታዬ አገልጋዮችም አውላላ ሜዳ ላይ ሰፍረዋል። ታዲያ እኔ ለመብላትና ለመጠጣት፣ ከሚስቴም ጋር ለመተኛት ወደ ቤቴ ልሂድ?+ በአንተና በሕያውነትህ* እምላለሁ ይህን ፈጽሞ አላደርገውም!”
12 ከዚያም ዳዊት ኦርዮን “እንግዲያውስ ዛሬን እዚህ ቆይና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። በመሆኑም ኦርዮ ያን ቀንና ቀጣዩን ቀን ኢየሩሳሌም ቆየ። 13 ዳዊትም አብሮት እንዲበላና እንዲጠጣ አስጠራው፤ አሰከረውም። ሆኖም ኦርዮ ምሽት ላይ ከጌታው አገልጋዮች ጋር ለመተኛት ወጥቶ ወደ መኝታው ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም። 14 ሲነጋም ዳዊት ለኢዮዓብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮ እጅ ላከለት። 15 በደብዳቤውም ላይ “ኦርዮን ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው። እሱም ተመቶ እንዲሞት እናንተ ከኋላው አፈግፍጉ” ብሎ ጻፈ።+
16 ኢዮዓብም ከተማዋን በጥንቃቄ ይመለከት ነበር፤ ኦርዮንም ኃይለኛ ተዋጊዎች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር መደበው። 17 የከተማዋም ሰዎች ወጥተው ከኢዮዓብ ጋር ሲዋጉ ከዳዊት አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ወደቁ፤ ከሞቱትም ሰዎች መካከል ሂታዊው ኦርዮ ይገኝበታል።+ 18 ከዚያም ኢዮዓብ የጦርነቱን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልጽ ወሬ ለዳዊት ላከ። 19 መልእክተኛውንም እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “አጠቃላይ የጦርነቱን ሁኔታ ለንጉሡ ነግረህ ስትጨርስ 20 ንጉሡ ሊቆጣና እንዲህ ሊልህ ይችላል፦ ‘ከተማዋን ለመውጋት ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው? ቅጥሩ አናት ላይ ሆነው እንደሚወነጭፉባችሁ አታውቁም? 21 የየሩቤሼትን+ ልጅ አቢሜሌክን የገደለው ማን ሆነና ነው?+ በቅጥሩ አናት ላይ ሆና መጅ በመልቀቅ በቴቤጽ የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችም? ታዲያ እናንተ ይህን ያህል ወደ ቅጥሩ የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ በዚህ ጊዜ ‘አገልጋይህ ሂታዊው ኦርዮም ሞቷል’ በለው።”
22 በመሆኑም መልእክተኛው ተነስቶ ሄደ፤ ኢዮዓብ የላከውንም መልእክት ሁሉ ለዳዊት ነገረው። 23 መልእክተኛውም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹ አየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወደ ሜዳው ወጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማው መግቢያ ድረስ እንዲያፈገፍጉ አደረግናቸው። 24 ቀስተኞቹም ቅጥሩ አናት ላይ ሆነው በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ያስወነጭፉ ጀመር፤ በዚህም የተነሳ ከንጉሡ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ተገደሉ፤ አገልጋይህ ሂታዊው ኦርዮም ሞተ።”+ 25 በዚህ ጊዜ ዳዊት መልእክተኛውን “ኢዮዓብን እንዲህ በለው፦ ‘መቼም ሰይፍ አንዱን እንደሚበላ ሁሉ ሌላውንም ስለሚበላ ይህ ሁኔታ አይረብሽህ። ብቻ አንተ በከተማዋ ላይ ውጊያህን በማፋፋም በቁጥጥር ሥር አውላት።’+ አንተም አበረታታው” አለው።
26 የኦርዮ ሚስት ባሏ መሞቱን ስትሰማ ለባለቤቷ አለቀሰችለት። 27 የሐዘኑ ጊዜ እንዳበቃም ዳዊት ልኮ ወደ ቤቱ አስመጣት፤ እሷም ሚስቱ ሆነች፤+ ወንድ ልጅም ወለደችለት። ሆኖም ዳዊት ያደረገው ነገር ይሖዋን በጣም አሳዝኖት* ነበር።+