ሁለተኛ ነገሥት
10 አክዓብ+ በሰማርያ 70 ወንዶች ልጆች ነበሩት። በመሆኑም ኢዩ ደብዳቤዎች ጽፎ በሰማርያ ወደሚገኙት የኢይዝራኤል መኳንንትና ሽማግሌዎች እንዲሁም ወደ አክዓብ ልጆች ሞግዚቶች* ላከ፤+ መልእክቱ እንዲህ የሚል ነበር፦ 2 “አሁን ይህ ደብዳቤ ሲደርሳችሁ የጌታችሁ ወንዶች ልጆች ከእናንተ ጋር ይሆናሉ፤ እንዲሁም የጦር ሠረገሎች፣ ፈረሶች፣ የተመሸገች ከተማና የጦር መሣሪያ ይኖራችኋል። 3 በመሆኑም ከጌታችሁ ወንዶች ልጆች መካከል የተሻለውንና ብቃት ያለውን* መርጣችሁ በአባቱ ዙፋን ላይ አስቀምጡት። ከዚያም ለጌታችሁ ቤት ተዋጉ።”
4 እነሱ ግን በፍርሃት ተውጠው “ሁለት ነገሥታት በፊቱ ሊቆሙ ካልቻሉ+ እኛ እንዴት ልንቆም እንችላለን?” አሉ። 5 በመሆኑም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ፣* የከተማዋ ገዢ፣ ሽማግሌዎቹና ሞግዚቶቹ “እኛ የአንተ አገልጋዮች ነን፤ አንተ ያልከንን ሁሉ እናደርጋለን። ማንንም አናነግሥም። አንተ ራስህ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” በማለት ወደ ኢዩ መልእክት ላኩ።
6 ከዚያም ኢዩ “የእኔ ከሆናችሁና እኔን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ከሆናችሁ የጌታችሁን ወንዶች ልጆች ራስ ቆርጣችሁ ነገ በዚህ ሰዓት ወደ ኢይዝራኤል ይዛችሁልኝ ኑ” የሚል ሁለተኛ ደብዳቤ ጻፈላቸው።
በዚህ ጊዜ 70ዎቹ የንጉሡ ልጆች አሳዳጊዎቻቸው ከሆኑት ታዋቂ የከተማዋ ሰዎች ጋር ነበሩ። 7 እነሱም ደብዳቤው እንደደረሳቸው 70ዎቹን የንጉሡን ልጆች ወስደው አረዷቸው፤+ ከዚያም ጭንቅላታቸውን በቅርጫቶች ውስጥ አድርገው ወደ ኢይዝራኤል ላኩለት። 8 መልእክተኛውም ገብቶ “የንጉሡን ልጆች ጭንቅላት አምጥተዋል” አለው። እሱም “በከተማዋ መግቢያ በር ላይ ሁለት ቦታ ቆልላችሁ እስከ ጠዋት ድረስ አቆዩአቸው” አለ። 9 ከዚያም ጠዋት ላይ ሲወጣ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ቆሞ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ንጹሐን* ናችሁ። በጌታዬ ላይ ያሴርኩትና የገደልኩት እኔ ነኝ፤+ እነዚህን ሁሉ ግን የገደላቸው ማን ነው? 10 እንግዲህ ይሖዋ በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው የይሖዋ ቃል አንዱም እንኳ ሳይፈጸም እንደማይቀር* እወቁ፤+ ይሖዋ በአገልጋዩ በኤልያስ አማካኝነት የተናገረውን ቃል ፈጽሟል።”+ 11 በተጨማሪም ኢዩ በኢይዝራኤል ከአክዓብ ቤት የቀሩትን ሁሉ እንዲሁም ታዋቂ የሆኑ ሰዎቹን፣ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳያስቀር ገደላቸው።+
12 ከዚያም ተነስቶ ወደ ሰማርያ አቀና። በመንገዱ ላይም የእረኞች ማቆያ ቤት* ይገኝ ነበር። 13 በዚያም ኢዩ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን+ ወንድሞች አገኛቸው፤ እሱም “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲላቸው “እኛ የአካዝያስ ወንድሞች ነን፤ የንጉሡን ልጆችና የንጉሡን እናት* ልጆች ደህንነት ለመጠየቅ እየወረድን ነው” አሉት። 14 እሱም ወዲያውኑ “በሕይወት እንዳሉ ያዟቸው!” አለ። በመሆኑም በሕይወት እንዳሉ ያዟቸው፤ በእረኞች ማቆያው ቤት አጠገብ በሚገኘው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ 42ቱን ሰዎች አረዷቸው። ከመካከላቸው አንድም ሰው አላስተረፈም።+
15 ከዚያ ተነስቶ ሲሄድ የሬካብን+ ልጅ ኢዮናዳብን+ ወደ እሱ ሲመጣ አገኘው። ኢዩም ሰላምታ ሰጥቶት* “የእኔ ልብ ከልብህ ጋር እንደሆነው ሁሉ የአንተስ ልብ ሙሉ በሙሉ* ከእኔ ጋር ነው?” አለው።
ኢዮናዳብም “አዎ ነው” ሲል መለሰለት።
ኢዩም “እንደዚያ ከሆነ እጅህን ስጠኝ” አለው።
እሱም እጁን ሰጠው፤ ኢዩም ጎትቶ ወደ ሠረገላው አወጣው። 16 ከዚያም “አብረኸኝ ሂድና ይሖዋን የሚቀናቀንን ማንኛውንም ነገር እንደማልታገሥ* እይ”+ አለው። እነሱም በጦር ሠረገላው አብሮት እንዲሄድ አደረጉ። 17 ከዚያም ወደ ሰማርያ መጣ፤ ደግሞም ይሖዋ ለኤልያስ በነገረው ቃል መሠረት+ ኢዩ በሰማርያ የሚገኙትን ከአክዓብ ቤት የቀሩትን በሙሉ ጠራርጎ እስኪያጠፋቸው ድረስ መታቸው።+
18 በተጨማሪም ኢዩ ሕዝቡን ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “አክዓብ ባአልን ያመለከው በትንሹ ነው፤+ ኢዩ ግን በላቀ ሁኔታ ያመልከዋል። 19 በመሆኑም የባአልን ነቢያት+ ሁሉ፣ አምላኪዎቹን ሁሉና ካህናቱን+ ሁሉ ጥሩልኝ። ለባአል ታላቅ መሥዋዕት ስለማቀርብ አንድም ሰው እንዳይቀር። የሚቀር ካለ በሕይወት አይኖርም።” ሆኖም ኢዩ ይህን ያለው የባአልን አምላኪዎች ለማጥፋት ተንኮል አስቦ ነው።
20 በመቀጠልም ኢዩ “ለባአል የተቀደሰ ጉባኤ አውጁ”* አለ። እነሱም ይህንኑ አወጁ። 21 ከዚያም ኢዩ በመላው እስራኤል መልእክት ላከ፤ የባአል አምላኪዎችም በሙሉ መጡ። ሳይመጣ የቀረ አንድም ሰው አልነበረም። እነሱም ወደ ባአል ቤት*+ ገቡ፤ የባአልም ቤት ከአፍ እስከ ገደፉ ሞላ። 22 ኢዩም የልብስ ቤቱን ኃላፊ “ለባአል አምላኪዎች ሁሉ ልብስ አውጣላቸው” አለው። እሱም ልብሶቹን አወጣላቸው። 23 ከዚያም ኢዩና የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ+ ወደ ባአል ቤት ገቡ። የባአልንም አምላኪዎች “ከባአል አምላኪዎች በስተቀር አንድም የይሖዋ አምላኪ እዚህ አለመኖሩን በሚገባ አረጋግጡ” አላቸው። 24 በመጨረሻም መሥዋዕቶችንና የሚቃጠሉ መባዎችን ለማቅረብ ገቡ። ኢዩም የራሱ የሆኑ 80 ሰዎችን ውጭ አቁሞ “በእጃችሁ አሳልፌ ከምሰጣችሁ ሰዎች መካከል አንድ ሰው ቢያመልጥ የእናንተ ሕይወት በዚያ ሰው ሕይወት* ይተካል” አላቸው።
25 ኢዩም የሚቃጠለውን መባ አቅርቦ እንደጨረሰ ጠባቂዎቹንና* የጦር መኮንኖቹን “ግቡና ጨፍጭፏቸው! አንድም ሰው እንዳያመልጥ!”+ አላቸው። ጠባቂዎቹና የጦር መኮንኖቹም በሰይፍ ጨፈጨፏቸው፤ ሬሳቸውንም ወደ ውጭ ጣሉ፤ እስከ ባአል ቤት ውስጠኛ መቅደስም * ድረስ ዘልቀው ገቡ። 26 ከዚያም የባአልን ቤት የማምለኪያ ዓምዶች+ አውጥተው አንድ በአንድ አቃጠሉ።+ 27 የባአልን የማምለኪያ ዓምድ ፈረካከሱ፤+ የባአልንም ቤት+ በማፈራረስ መጸዳጃ ቦታ እንዲሆን አደረጉ፤ እስከ ዛሬም ድረስ እንደዚያው ነው።
28 በዚህ መንገድ ኢዩ ባአልን ከእስራኤል አስወገደ። 29 ሆኖም የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኃጢአት ይኸውም በቤቴልና በዳን ከነበሩት የወርቅ ጥጆች+ ጋር በተያያዘ እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ያደረገውን ኃጢአት ከመከተል ዞር አላለም። 30 ስለሆነም ይሖዋ ኢዩን “በአክዓብ ቤት ላይ በልቤ ያሰብኩትን+ ሁሉ በመፈጸም በፊቴ መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር ስላደረግክ ልጆችህ እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ”+ አለው። 31 ኢዩ ግን በሙሉ ልቡ በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ሕግ ይሄድ ዘንድ አልተጠነቀቀም።+ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።+
32 በዚያ ዘመን ይሖዋ የእስራኤልን ግዛት መቆራረስ* ጀመረ። ሃዛኤል በሁሉም የእስራኤል ግዛት ጥቃት ይሰነዝር ነበር፤+ 33 ይህም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን የጊልያድ ምድር ሁሉ ማለትም ጋዳውያን፣ ሮቤላውያንና ምናሴያውያን+ የሚኖሩበትን ምድር እንዲሁም ከአርኖን ሸለቆ* አጠገብ ካለው ከአሮዔር አንስቶ እስከ ጊልያድና እስከ ባሳን+ ድረስ ያለውን አካባቢ ያጠቃልላል።
34 የቀረው የኢዩ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉና ኃያልነቱ ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 35 በመጨረሻም ኢዩ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነሱም በሰማርያ ቀበሩት፤ ልጁ ኢዮዓካዝም+ በምትኩ ነገሠ። 36 ኢዩ በሰማርያ ሆኖ በእስራኤል ላይ የገዛበት ዘመን ርዝመት* 28 ዓመት ነበር።