ለቲቶ የተጻፈ ደብዳቤ
1 የአምላክ ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ። ይህ ሐዋርያ፣ አገልግሎቱ ከአምላክ ምርጦች እምነትና ከእውነት ትክክለኛ እውቀት ጋር የሚስማማ ሲሆን ይህ እውነት ለአምላክ ያደሩ ሆኖ ከመኖር ጋር የተቆራኘ ነው፤ 2 ደግሞም ሊዋሽ የማይችለው አምላክ+ ከረጅም ዘመናት በፊት በሰጠው የዘላለም ሕይወት+ ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነው፤ 3 ይሁንና አዳኛችን በሆነው አምላክ ትእዛዝ በአደራ በተሰጠኝ+ የስብከቱ ሥራ አማካኝነት ራሱ በወሰነው ጊዜ ቃሉ እንዲታወቅ አደረገ፤ 4 የጋራችን በሆነው እምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለቲቶ፦
አባት ከሆነው አምላክና አዳኛችን ከሆነው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ለአንተ ይሁን።
5 አንተን በቀርጤስ የተውኩህ ያልተስተካከሉትን* ነገሮች እንድታስተካክልና በሰጠሁህ መመሪያ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው፤ 6 ይኸውም ከክስ ነፃ የሆነ፣ የአንዲት ሚስት ባል እንዲሁም በስድነት* ወይም በዓመፀኝነት የማይከሰሱ አማኝ የሆኑ ልጆች ያሉት ማንም ሰው ካለ እንድትሾም ነው።+ 7 ምክንያቱም የበላይ ተመልካች በአምላክ የተሾመ መጋቢ እንደመሆኑ መጠን ከክስ ነፃ መሆን አለበት፤ በራሱ ሐሳብ የሚመራ፣+ ግልፍተኛ፣+ ሰካራም፣ ኃይለኛና* አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚስገበገብ ሊሆን አይገባም፤ 8 ከዚህ ይልቅ እንግዳ ተቀባይ፣+ ጥሩ የሆነውን ነገር የሚወድ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣*+ ጻድቅ፣ ታማኝ፣+ ራሱን የሚገዛ፣+ 9 እንዲሁም ትክክለኛ* በሆነው ትምህርት+ ማበረታታትም* ሆነ ይህን ትምህርት የሚቃወሙትን መውቀስ+ ይችል ዘንድ የማስተማር ጥበቡን+ ሲጠቀም የታመነውን ቃል* በጥብቅ የሚከተል ሊሆን ይገባል።
10 ዓመፀኞች፣ በከንቱ የሚለፈልፉና አታላዮች የሆኑ በተለይም ግርዘትን በጥብቅ የሚከተሉ ብዙ ሰዎች አሉና።+ 11 እነዚህ ሰዎች አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን ትምህርት በማስተማር የመላውን ቤተሰብ እምነት እያፈረሱ ስለሆነ አፋቸውን ማዘጋት ያስፈልጋል። 12 ከእነሱ መካከል የሆነ የገዛ ራሳቸው ነቢይ “የቀርጤስ ሰዎች ምንጊዜም ውሸታሞች፣ አደገኛ አውሬዎችና ሥራ ፈት ሆዳሞች ናቸው” ብሏል።
13 ይህ የምሥክርነት ቃል እውነት ነው። ለዚህም ሲባል እነሱን አጥብቀህ መውቀስህን ቀጥል፤ ይኸውም በእምነት ጠንካሮች* እንዲሆኑ 14 እንዲሁም ለአይሁዳውያን ተረቶችና ከእውነት የራቁ ሰዎች ለሚሰጡት ትእዛዝ ትኩረት እንዳይሰጡ ነው። 15 ንጹሕ ለሆኑ ሰዎች ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤+ ለረከሱና እምነት ለሌላቸው ሰዎች ግን ንጹሕ የሆነ ነገር የለም፤ አእምሯቸውም ሆነ ሕሊናቸው የረከሰ ነውና።+ 16 አምላክን እንደሚያውቁ በይፋ ይናገራሉ፤ ሆኖም በሥራቸው ይክዱታል፤+ ምክንያቱም አስጸያፊና የማይታዘዙ እንዲሁም ለማንኛውም ዓይነት መልካም ሥራ የማይበቁ ናቸው።