የዮሐንስ ወንጌል
18 ኢየሱስ ስለ እነዚህ ነገሮች ከጸለየ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የቄድሮንን ሸለቆ*+ ተሻግሮ ወደ አንድ የአትክልት ስፍራ ሄደ፤ እሱና ደቀ መዛሙርቱም ወደ አትክልት ስፍራው ገቡ።+ 2 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብዙ ጊዜ በዚህ ስፍራ ይገናኝ ስለነበር አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ቦታውን ያውቅ ነበር። 3 ስለዚህ ይሁዳ አንድ የወታደሮች ቡድን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች አስከትሎ መጣ፤ እነሱም ችቦና መብራት እንዲሁም መሣሪያ ይዘው ነበር።+ 4 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሚደርስበትን ነገር ሁሉ ስላወቀ ወደ ፊት ራመድ ብሎ “ማንን ነው የምትፈልጉት?” አላቸው። 5 እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ”+ ሲሉ መለሱለት። እሱም “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ከእነሱ ጋር ቆሞ ነበር።+
6 ይሁን እንጂ ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ሲላቸው ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ።+ 7 ዳግመኛም “ማንን ነው የምትፈልጉት?” ሲል ጠየቃቸው። እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ” አሉት። 8 ኢየሱስም መልሶ “እኔ ነኝ አልኳችሁ እኮ። የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው ይሂዱ” አለ። 9 ይህም የሆነው “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ መካከል አንዱም እንኳ አልጠፋብኝም”+ ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
10 በዚህ ጊዜ ሰይፍ ይዞ የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቆረጠው።+ የባሪያውም ስም ማልኮስ ነበር። 11 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ጴጥሮስን “ሰይፉን ወደ ሰገባው መልስ።+ አብ የሰጠኝን ጽዋ መጠጣት አይኖርብኝም?” አለው።+
12 ከዚያም ወታደሮቹና የጦር አዛዡ እንዲሁም ከአይሁዳውያን የተላኩት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። 13 በመጀመሪያም ወደ ሐና ወሰዱት፤ ምክንያቱም ሐና በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት+ የነበረው የቀያፋ+ አማት ነበር። 14 ቀያፋ ደግሞ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት ለእነሱ የተሻለ እንደሚሆን ለአይሁዳውያን ምክር የሰጠው ሰው ነው።+
15 ስምዖን ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን እየተከተሉ ነበር።+ ይህን ደቀ መዝሙር ሊቀ ካህናቱ ያውቀው ስለነበር ከኢየሱስ ጋር ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ፤ 16 ጴጥሮስ ግን ውጭ በር ላይ ቆሞ ነበር። ስለሆነም ሊቀ ካህናቱ የሚያውቀው ይህ ደቀ መዝሙር ወጥቶ በር ጠባቂዋን አነጋገራትና ጴጥሮስን አስገባው። 17 በር ጠባቂ የነበረችውም አገልጋይ ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ ነህ አይደል?” አለችው። እሱም “አይደለሁም” አለ።+ 18 ብርድ ስለነበር ባሪያዎቹና የቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች ባቀጣጠሉት ከሰል ዙሪያ ቆመው እየሞቁ ነበር። ጴጥሮስም ከእነሱ ጋር ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር።
19 በዚህ ጊዜ የካህናት አለቃው ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። 20 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ። አይሁዳውያን ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብና በቤተ መቅደሱ ሁልጊዜ አስተምር ነበር፤+ በስውር የተናገርኩት ምንም ነገር የለም። 21 እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? እኔ የነገርኳቸውን ነገር የሰሙትን ሰዎች ጠይቃቸው። እነዚህ የተናገርኩትን ያውቃሉ።” 22 ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች አንዱ በጥፊ መታውና+ “ለካህናት አለቃው የምትመልሰው እንዲህ ነው?” አለው። 23 ኢየሱስም “የተሳሳተ ነገር ተናግሬ ከሆነ ስህተቴ ምን እንደሆነ ንገረኝ፤* የተናገርኩት ነገር ትክክል ከሆነ ግን ለምን ትመታኛለህ?” ሲል መለሰለት። 24 ከዚያም ሐና ኢየሱስን እንደታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው።+
25 ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት እየሞቀ ነበር። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ “አንተም ከእሱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነህ አይደል?” አሉት። እሱም “አይደለሁም” ሲል ካደ።+ 26 ከሊቀ ካህናቱ ባሪያዎች አንዱ ይኸውም ጴጥሮስ ጆሮውን የቆረጠው+ ሰው ዘመድ “በአትክልቱ ስፍራ ከእሱ ጋር አይቼህ አልነበረም?” አለው። 27 ይሁን እንጂ ጴጥሮስ እንደገና ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።+
28 ከዚያም ኢየሱስን ከቀያፋ ቤት ወደ ገዢው መኖሪያ ወሰዱት።+ ጊዜውም ማለዳ ነበር። ሆኖም እነሱ ፋሲካን መብላት ይችሉ ዘንድ እንዳይረክሱ+ ወደ ገዢው መኖሪያ አልገቡም። 29 ስለዚህ ጲላጦስ እነሱ ወዳሉበት ወጥቶ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?” አላቸው። 30 እነሱም መልሰው “ይህ ሰው ጥፋተኛ* ባይሆን ኖሮ ለአንተ አሳልፈን አንሰጠውም ነበር” አሉት። 31 ስለዚህ ጲላጦስ “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው።+ አይሁዳውያኑም “እኛ ማንንም ሰው ለመግደል ሕግ አይፈቅድልንም” አሉት።+ 32 ይህ የሆነው ኢየሱስ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚሞት ለማመልከት የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው።+
33 ስለሆነም ጲላጦስ ወደ ገዢው መኖሪያ ተመልሶ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” አለው።+ 34 ኢየሱስም መልሶ “ይህ የራስህ ጥያቄ ነው ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነግረውህ ነው?” አለው። 35 ጲላጦስም “እኔ አይሁዳዊ ነኝ እንዴ? ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ የራስህ ሕዝብና የካህናት አለቆች ናቸው። ያደረግከው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። 36 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦+ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም።+ መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር።+ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።” 37 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “እንግዲያው አንተ ንጉሥ ነህ?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ ንጉሥ እንደሆንኩ አንተ ራስህ እየተናገርክ ነው።+ እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመሥከር ነው።+ ከእውነት ጎን የቆመ ሁሉ ቃሌን ይሰማል።” 38 ጲላጦስም “እውነት ምንድን ነው?” አለው።
ይህን ከተናገረ በኋላ እንደገና አይሁዳውያኑ ወዳሉበት ወጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም።+ 39 ከዚህም በላይ በልማዳችሁ መሠረት በፋሲካ አንድ ሰው ለእናንተ መፍታቴ አይቀርም።+ ስለዚህ የአይሁዳውያንን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” 40 እነሱም እንደገና በመጮኽ “ይህን ሰው አንፈልግም፤ በርባንን ፍታልን!” አሉ። በርባን ግን ወንበዴ ነበር።+