አንደኛ ሳሙኤል
20 ከዚያም ዳዊት በራማ ከምትገኘው ከናዮት ሸሸ። ሆኖም ወደ ዮናታን መጥቶ “ምን አደረግኩ?+ የፈጸምኩትስ በደል ምንድን ነው? አባትህ ሕይወቴን* ለማጥፋት የሚፈልገው በእሱ ላይ ምን ኃጢአት ሠርቼ ነው?” አለው። 2 ዮናታንም እንዲህ አለው፦ “ይሄማ የማይታሰብ ነው!+ ፈጽሞ አትሞትም! አባቴ እንደሆነ ትልቅም ሆነ ትንሽ፣ ለእኔ ሳይነግረኝ ምንም ነገር አያደርግም። ታዲያ አባቴ ይህን ነገር ከእኔ የሚደብቅበት ምን ምክንያት አለው? እንዲህማ አይሆንም።” 3 ዳዊት ግን እንደገና ማለለት፤ እንዲህም አለው፦ “አባትህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን+ በሚገባ ስለሚያውቅ ‘ዮናታን ሊያዝን ስለሚችል ይህን ነገር ማወቅ የለበትም’ ብሎ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ* እምላለሁ፣ በእኔና በሞት መካከል ያለው አንድ እርምጃ ብቻ ነው!”+
4 ከዚያም ዮናታን ዳዊትን “የምትለውን* ማንኛውንም ነገር አደርግልሃለሁ” አለው። 5 በዚህ ጊዜ ዳዊት ዮናታንን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፣ ነገ አዲስ ጨረቃ+ የምትወጣበት ቀን ነው፤ እኔም ከንጉሡ ጋር ለመመገብ በማዕድ መቀመጥ ይጠበቅብኛል፤ አንተ ካሰናበትከኝ ግን እስከ ሦስተኛው ቀን ምሽት ድረስ ወደ ሜዳ ሄጄ እደበቃለሁ። 6 ምናልባት አባትህ አለመኖሬን አስተውሎ ከጠየቀ ‘ዳዊት በከተማው በቤተልሔም+ ለመላ ቤተሰቡ የሚቀርብ ዓመታዊ መሥዋዕት ስላለ ቶሎ ወደዚያ ይሄድ ዘንድ እንድፈቅድለት ለመነኝ’ በለው።+ 7 እሱም ‘ጥሩ ነው!’ ካለ አገልጋይህን የሚያሰጋው ነገር የለም ማለት ነው። ከተቆጣ ግን በእኔ ላይ ጉዳት ለማድረስ እንደቆረጠ እወቅ። 8 አገልጋይህ ከአንተ ጋር በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን እንዲገባ ያደረግከው+ አንተ ስለሆንክ ለአገልጋይህ ታማኝ ፍቅር አሳየው።+ በእኔ ላይ ጥፋት ከተገኘ+ ግን አንተው ራስህ ግደለኝ። ለምን ለአባትህ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ?”
9 በዚህ ጊዜ ዮናታን “እንዲህ ብለህ ማሰብማ የለብህም! አባቴ በአንተ ላይ ጉዳት ለማድረስ መቁረጡን ባውቅ እንዴት ሳልነግርህ ዝም እላለሁ?” አለው።+ 10 ከዚያም ዳዊት ዮናታንን “ታዲያ አባትህ ክፉ ቃል ቢመልስልህ ማን ይነግረኛል?” አለው። 11 ዮናታንም ዳዊትን “ና፣ ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው። በመሆኑም ተያይዘው ወደ ሜዳ ወጡ። 12 ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ነገ በዚህ ጊዜ ወይም ከነገ ወዲያ አባቴ ያለውን አመለካከት ባላጣራ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ምሥክር ይሁንብኝ። እሱ ለዳዊት ጥሩ አመለካከት ካለው ወደ አንተ ልኬ የማላሳውቅህ ይመስልሃል? 13 አባቴ በአንተ ላይ ጉዳት ለማድረስ አስቦ ቢሆንና እኔ ግን ይህን ሳላሳውቅህ ብቀር እንዲሁም በሰላም እንድትሄድ ባላደርግ ይሖዋ በዮናታን ላይ ይህን ያድርግበት፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣበት። ይሖዋ ከአባቴ ጋር እንደነበር+ ሁሉ ከአንተም ጋር ይሁን።+ 14 አንተስ ብትሆን በሕይወት ሳለሁም ሆነ ስሞት የይሖዋን ታማኝ ፍቅር አታሳየኝም?+ 15 ይሖዋ የዳዊትን ጠላቶች በሙሉ ከምድር ገጽ ጠራርጎ በሚያጠፋበት ጊዜም ለቤተሰቤ+ ታማኝ ፍቅርህን ከማሳየት ፈጽሞ ወደኋላ አትበል።” 16 ስለዚህ ዮናታን “ይሖዋ የዳዊትን ጠላቶች ይፋረዳቸዋል” በማለት ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን ገባ። 17 በመሆኑም ዮናታን ዳዊት ለእሱ ባለው ፍቅር እንደገና እንዲምልለት አደረገ፤ ምክንያቱም ዳዊትን እንደ ራሱ* ይወደው ነበር።+
18 ዮናታንም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ነገ አዲስ ጨረቃ+ የምትወጣበት ቀን ነው፤ የምትቀመጥበት ቦታ ባዶ ስለሚሆን አለመኖርህ ይታወቃል። 19 በሦስተኛውም ቀን፣ አለመኖርህ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤ አንተም ያን ቀን* ተደብቀህበት ወደነበረው ቦታ ሂድ፤ እዚህ ድንጋይ አጠገብም ቆይ። 20 እኔም ዒላማ የምመታ አስመስዬ በድንጋዩ አጠገብ ሦስት ቀስቶችን አስፈነጥራለሁ። 21 አገልጋዩንም ‘ሂድ፣ ፍላጻዎቹን አምጣቸው’ ብዬ እልከዋለሁ። አገልጋዩን ‘ፍላጻዎቹ ከአንተ በዚህኛው በኩል ናቸው፤ አምጣቸው’ ካልኩት ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ ሁሉ ነገር ሰላም ስለሆነና ምንም የሚያሰጋህ ነገር ስለሌለ ተመልሰህ መምጣት ትችላለህ። 22 ሆኖም ልጁን ‘ፍላጻዎቹ ከአንተ ወዲያ ናቸው’ ካልኩት ይሖዋ አሰናብቶሃልና ሂድ። 23 እኔና አንተ የተጋባነውን ቃል+ በተመለከተም ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ለዘላለም ምሥክር ይሁን።”+
24 በመሆኑም ዳዊት ወደ ሜዳ ሄዶ ተደበቀ። አዲስ ጨረቃ ስትወጣም ንጉሡ ለመብላት በማዕድ ተቀመጠ።+ 25 ንጉሡ እንደተለመደው በግድግዳው በኩል ባለው መቀመጫው ላይ ተቀምጦ ነበር። ዮናታን ከፊት ለፊቱ፣ አበኔር+ ደግሞ ከሳኦል ጎን ተቀምጠው ነበር፤ የዳዊት ቦታ ግን ባዶ ነበር። 26 ሳኦል ‘መቼም ዳዊት እንዳይነጻ+ የሚያደርገው የሆነ ነገር ገጥሞት መሆን ይኖርበታል። አዎ፣ ረክሶ መሆን አለበት’ ብሎ ስላሰበ በዚያን ቀን ምንም አልተናገረም። 27 አዲስ ጨረቃ በወጣችበት ቀን ማግስት ይኸውም በሁለተኛው ቀን የዳዊት ቦታ ክፍት እንደሆነ ነበር። ከዚያም ሳኦል ልጁን ዮናታንን “የእሴይ+ ልጅ ትናንትም፣ ዛሬም ማዕድ ላይ ያልተገኘው ለምንድን ነው?” አለው። 28 ዮናታንም ለሳኦል እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ዳዊት ወደ ቤተልሔም ይሄድ ዘንድ እንድፈቅድለት ለመነኝ።+ 29 እንዲህም አለኝ፦ ‘ቤተሰባችን በከተማዋ ውስጥ መሥዋዕት ስለሚያቀርብና ወንድሜም በዚያ እንድገኝ ስለጠራኝ እባክህ እንድሄድ ፍቀድልኝ። እንግዲህ በፊትህ ሞገስ ካገኘሁ እባክህ ወንድሞቼን አይ ዘንድ ሹልክ ብዬ ልሂድ።’ ዳዊት በንጉሡ ማዕድ ላይ ያልተገኘው ለዚህ ነው።” 30 በዚህ ጊዜ ሳኦል በዮናታን ላይ እጅግ ተቆጣ፤ እንዲህም አለው፦ “አንተ የዚያች ዓመፀኛ ሴት ልጅ፣ በራስህም ሆነ በእናትህ* ላይ ውርደት ለማምጣት ከእሴይ ልጅ ጋር መወገንህን የማላውቅ መሰለህ? 31 የእሴይ ልጅ በምድር ላይ በሕይወት እስካለ ድረስ አንተም ሆንክ መንግሥትህ አትጸኑም።+ እሱ መሞት ስላለበት* በል አሁኑኑ ልከህ አስመጣልኝ።”+
32 ዮናታን ግን አባቱን ሳኦልን “ለምን ይገደላል?+ ጥፋቱስ ምንድን ነው?” አለው። 33 በዚህ ጊዜ ሳኦል እሱን ለመግደል ጦሩን ወረወረበት፤+ ስለሆነም ዮናታን አባቱ፣ ዳዊትን ለመግደል ቆርጦ መነሳቱን አወቀ።+ 34 ዮናታንም ወዲያውኑ በታላቅ ቁጣ ከማዕዱ ላይ ተነሳ፤ በዳዊት ምክንያት በጣም ስላዘነና+ የገዛ አባቱም ስላዋረደው አዲስ ጨረቃ በወጣች በሁለተኛው ቀን ምንም ምግብ አልቀመሰም።
35 ዮናታንም በማለዳ ተነስቶ ከዳዊት ጋር ወደተቀጣጠሩበት ቦታ ሄደ፤ አንድ ወጣት አገልጋይም አብሮት ነበር።+ 36 እሱም አገልጋዩን “ሂድ፣ ሩጥ፤ የምወነጭፋቸውንም ፍላጻዎች ፈልግ” አለው። ከዚያም አገልጋዩ ሮጠ፤ ዮናታንም ፍላጻውን ከእሱ አሳልፎ ወነጨፈው። 37 አገልጋዩም ዮናታን የወነጨፈው ፍላጻ ያረፈበት ቦታ ሲደርስ ዮናታን አገልጋዩን ጠርቶ “ፍላጻው ያለው ከአንተ ወዲያ አይደለም?” አለው። 38 ዮናታንም በድጋሚ አገልጋዩን ጠርቶ “ፍጠን እንጂ! ቶሎ በል! አትዘግይ!” አለው። የዮናታን አገልጋይም ፍላጻዎቹን አንስቶ ወደ ጌታው ተመለሰ። 39 አገልጋዩ ስለ ጉዳዩ የሚያውቀው ነገር አልነበረም፤ የዚህ ትርጉም ምን እንደሆነ የሚያውቁት ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነበሩ። 40 ከዚያም ዮናታን የጦር መሣሪያዎቹን ለአገልጋዩ ሰጥቶ “ሂድ፣ ወደ ከተማ ይዘሃቸው ተመለስ” አለው።
41 አገልጋዩም ሲሄድ ዳዊት በስተ ደቡብ በኩል ከሚገኝ በአቅራቢያው ካለ ስፍራ ተነስቶ መጣ። ሦስት ጊዜም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ እጅ ነሳ፤ ከዚያም ተሳሳሙ፤ ተላቀሱ፤ ይበልጥ ያለቀሰው ግን ዳዊት ነበር። 42 ዮናታንም ዳዊትን “ሁለታችንም ‘ይሖዋ በእኔና በአንተ፣ በዘሮቼና በዘሮችህ መካከል ለዘላለም ይሁን’+ ብለን በይሖዋ ስም ስለተማማልን+ በሰላም ሂድ” አለው።
ከዚያም ዳዊት ተነስቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማዋ ተመለሰ።