ዘካርያስ
14 “እነሆ፣ የይሖዋ ቀን ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ከአንቺ* የተማረከው በመካከልሽ ይከፋፈላል። 2 ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ ብሔራትን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከተማዋም ትያዛለች፤ ቤቶቹ ይዘረፋሉ፤ ሴቶቹም ይደፈራሉ። የከተማዋም እኩሌታ ለግዞት ይዳረጋል፤ ከሕዝቡ መካከል የሚቀሩት ሰዎች ግን ከከተማዋ አይወገዱም።
3 “ይሖዋ ይወጣል፤ በጦርነት ቀን እንደሚዋጋው እነዚያን ብሔራት ይዋጋል።+ 4 በዚያ ቀን እግሮቹ በስተ ምሥራቅ በኢየሩሳሌም ትይዩ በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ+ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ከምሥራቅ* አንስቶ እስከ ምዕራብ* ድረስ ለሁለት ይከፈላል፤ እጅግ ትልቅ ሸለቆም ይፈጠራል፤ የተራራው አንዱ ግማሽ ወደ ሰሜን፣ ሌላው ግማሽ ደግሞ ወደ ደቡብ ፈቀቅ ይላል። 5 እናንተ በተራሮቼ መካከል ወዳለው ሸለቆ ትሸሻላችሁ፤ በተራሮቹ መካከል ያለው ሸለቆ እስከ አዜል ድረስ ይደርሳልና። በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያ ዘመን ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሳ+ ሸሽታችሁ እንደነበረ ሁሉ አሁንም ትሸሻላችሁ። አምላኬ ይሖዋም ይመጣል፤ ቅዱሳኑም ሁሉ ከእሱ ጋር ይሆናሉ።+
6 “በዚያ ቀን ደማቅ ብርሃን አይኖርም፤+ ነገሮች ሁሉ ባሉበት ይረጋሉ።* 7 ያም ቀን የይሖዋ ቀን ተብሎ የሚታወቅ ልዩ ቀን ይሆናል።+ ቀንም ሆነ ሌሊት አይሆንም፤ በመሸም ጊዜ ብርሃን ይኖራል። 8 በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ሕያው ውኃዎች+ ይወጣሉ፤+ ግማሾቹ በስተ ምሥራቅ ወዳለው ባሕር፣*+ ግማሾቹ ደግሞ በስተ ምዕራብ ወዳለው ባሕር* ይፈስሳሉ።+ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል። 9 ይሖዋም በመላው ምድር ላይ ይነግሣል።+ በዚያ ቀን ይሖዋ አንድ፣+ ስሙም አንድ ይሆናል።+
10 “ከጌባ+ አንስቶ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ እስካለችው እስከ ሪሞን+ ድረስ መላው ምድር እንደ አረባ+ ይሆናል፤ ኢየሩሳሌም በቀድሞ ስፍራዋ ላይ ትነሳለች፤ የሰዎችም መኖሪያ ትሆናለች፤+ ደግሞም ከቢንያም በር+ አንስቶ እስከ መጀመሪያው በርና እስከ ማዕዘን በር ድረስ ያለው ስፍራ ሁሉ እንዲሁም ከሃናንኤል ማማ+ አንስቶ እስከ ንጉሡ የወይን መጭመቂያዎች* ድረስ ያለው ስፍራ ሁሉ ሰው ይኖርበታል። 11 በከተማዋም ውስጥ ሰዎች ይኖራሉ፤ ከእንግዲህም ጥፋት እንዲደርስባት አትረገምም፤+ ደግሞም ኢየሩሳሌም ሰዎች ያለስጋት የሚኖሩባት ቦታ ትሆናለች።+
12 “ይሖዋ ኢየሩሳሌምን የሚወጉ ሕዝቦችን ሁሉ የሚቀስፍበት መቅሰፍት ይህ ነው፦+ በእግራቸው ቆመው እያለ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዓይኖቻቸውም በጉድጓዶቻቸው ውስጥ ይበሰብሳሉ፤ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል።
13 “በዚያ ቀን ከይሖዋ ዘንድ የመጣ ሽብር በመካከላቸው ይሰራጫል፤ እያንዳንዱም ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ እጁንም በባልንጀራው እጅ ላይ ያነሳል።*+ 14 ይሁዳም ራሱ በኢየሩሳሌም በሚደረገው ውጊያ ይካፈላል፤ በዙሪያዋም ያሉ ብሔራት ሁሉ ሀብት ይኸውም ወርቅ፣ ብርና ልብስ በብዛት ይሰበሰባል።+
15 “በየሰፈሩ ባሉት ፈረሶች፣ በቅሎዎች፣ ግመሎች፣ አህዮችና መንጎች ሁሉ ላይ ተመሳሳይ መቅሰፍት ይወርዳል።
16 “በኢየሩሳሌም ላይ ከተነሱት ብሔራት ሁሉ የሚተርፉት ሰዎች በሙሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ለመስገድና*+ የዳስ* በዓልን ለማክበር+ በየዓመቱ ይወጣሉ።+ 17 ይሁንና ከምድር ብሔራት መካከል ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም የማይወጡ ቢኖሩ ዝናብ አይዘንብላቸውም።+ 18 የግብፅ ሰዎች ባይወጡና ወደ ከተማዋ ባይገቡ ዝናብ አይዘንብላቸውም። እንዲያውም ይሖዋ የዳስ በዓልን ለማክበር ባልመጡት ብሔራት ላይ በሚያመጣቸው መቅሰፍቶች ይቀሰፋሉ። 19 ግብፅ ለፈጸመችው ኃጢአትና የዳስ በዓልን ለማክበር ያልወጡት ብሔራት ሁሉ ለሠሩት ኃጢአት ይህ ቅጣት ይደርስባቸዋል።
20 “በዚያ ቀን በፈረሶቹ ቃጭል ላይ ‘ቅድስና የይሖዋ ነው!’ ተብሎ ይጻፋል።+ በይሖዋ ቤት ያሉት ድስቶች+ በመሠዊያው ፊት እንዳሉት ሳህኖች+ ይሆናሉ። 21 በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ድስቶች በሙሉ ቅዱስና ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ የተወሰኑ ይሆናሉ፤ መሥዋዕት የሚያቀርቡትም ሁሉ ገብተው የተወሰኑትን ድስቶች ለመቀቀያ ይጠቀሙባቸዋል። በዚያ ቀን በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ቤት ዳግመኛ ከነአናዊ* አይገኝም።”+