ሁለተኛ ሳሙኤል
15 ከዚህ ሁሉ በኋላ አቢሴሎም ሠረገላ፣ ፈረሶችና ከፊቱ የሚሮጡ 50 ሰዎች አዘጋጀ።+ 2 አቢሴሎምም በጠዋት ተነስቶ ወደ ከተማዋ በር+ በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆም ነበር። ማንም ሰው ሙግት ኖሮት ፍርድ ለማግኘት+ ወደ ንጉሡ በሚመጣበት ጊዜ አቢሴሎም ይጠራውና “ለመሆኑ አንተ የየትኛው ከተማ ሰው ነህ?” ይለው ነበር፤ እሱም “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች መካከል ከአንዱ ነው” ይለዋል። 3 አቢሴሎምም “አቤቱታህ ትክክልና ተገቢ ነው፤ ግን ምን ያደርጋል፣ ከንጉሡ ዘንድ ጉዳይህን የሚሰማልህ አንድም ሰው አታገኝም” ይለው ነበር። 4 ከዚያም አቢሴሎም “ምነው በምድሪቱ ላይ ዳኛ ሆኜ በተሾምኩ! ሙግት ያለው ወይም ፍርድ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደ እኔ መጥቶ ፍትሕ ማግኘት ይችል ነበር” ይል ነበር።
5 እንዲሁም አንድ ሰው ሊሰግድለት ወደ እሱ በሚቀርብበት ጊዜ አቢሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር።+ 6 አቢሴሎምም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጣው እስራኤላዊ በሙሉ እንዲህ ያደርግ ነበር፤ በዚህ መንገድ አቢሴሎም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።+
7 በአራቱ* ዓመት ማብቂያ ላይ አቢሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ ለይሖዋ የተሳልኩትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን+ ልሂድ። 8 ምክንያቱም እኔ አገልጋይህ በሶርያ ባለችው በገሹር+ በነበርኩበት ጊዜ ‘ይሖዋ ወደ ኢየሩሳሌም ከመለሰኝ ለይሖዋ መባ* አቀርባለሁ’ በማለት ተስዬ+ ነበር።” 9 በመሆኑም ንጉሡ “በሰላም ሂድ” አለው። እሱም ተነስቶ ወደ ኬብሮን ሄደ።
10 አቢሴሎምም “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ ‘አቢሴሎም በኬብሮን ነገሠ!’+ ብላችሁ አውጁ” በማለት በመላው የእስራኤል ነገዶች መካከል ሰላዮችን አሰማራ። 11 በዚህ ጊዜ ከኢየሩሳሌም 200 ሰዎች ከአቢሴሎም ጋር ወደዚያ ሄደው ነበር፤ ጥሪ ቀርቦላቸው የሄዱት እነዚህ ሰዎች ምንም የጠረጠሩትና የሚያውቁት ነገር አልነበረም። 12 በተጨማሪም አቢሴሎም መሥዋዕቶቹን በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊትን አማካሪ+ ጊሎአዊውን አኪጦፌልን+ ከከተማው ከጊሎ+ ልኮ አስጠራው። አቢሴሎም የጠነሰሰው ሴራ እየተጠናከረ ሄደ፤ ከአቢሴሎም ጎን የተሰለፈውም ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መጣ።+
13 በኋላም አንድ ሰው ወደ ዳዊት መጥቶ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ወደ አቢሴሎም ሸፍቷል” ሲል ነገረው። 14 ዳዊትም በኢየሩሳሌም አብረውት የነበሩትን አገልጋዮቹን በሙሉ ወዲያውኑ እንዲህ አላቸው፦ “ተነሱ፣ እንሽሽ፤+ አለዚያ አንዳችንም ከአቢሴሎም እጅ አናመልጥም! በፍጥነት መጥቶ እንዳይዘንና እንዳያጠፋን፣ ከተማዋንም በሰይፍ እንዳይመታ ቶሎ ብለን ከዚህ እንሂድ!”+ 15 የንጉሡ አገልጋዮችም ንጉሡን “እኛ አገልጋዮችህ ጌታዬ ንጉሡ የወሰነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን” አሉት።+ 16 በመሆኑም ንጉሡ ቤተሰቡን ሁሉ አስከትሎ ወጣ፤ ሆኖም ቤቱን* እንዲጠብቁ አሥር ቁባቶቹን እዚያው አስቀረ።+ 17 ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ አስከትሎ ተጓዘ፤ እነሱም ቤትሜርሃቅ ሲደርሱ ቆሙ።
18 ከዚያም አብረውት የሄዱት* አገልጋዮቹ በሙሉ፣ ከሪታውያን በሙሉ፣ ጴሌታውያን+ በሙሉ እንዲሁም ከጌት+ ተከትለውት የመጡት 600 ጌታውያን+ ንጉሡ እያያቸው አለፉ።* 19 ንጉሡም ጌታዊውን ኢታይን+ እንዲህ አለው፦ “ከእኛ ጋር የምትሄደው ለምንድን ነው? በል ተመለስና ከአዲሱ ንጉሥ ጋር ተቀመጥ፤ አንተ ለራስህ ከአገርህ ተሰደህ የመጣህ የባዕድ አገር ሰው ነህ። 20 የመጣኸው ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ ዛሬ እኔ ወደምሄድበት ቦታ ሁሉ አብረህ እንድትሄድ በማድረግ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? በል አሁን ወንድሞችህን ይዘህ ተመለስ፤ ይሖዋም ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ያሳይህ!”+ 21 ኢታይ ግን ለንጉሡ “ሕያው በሆነው በይሖዋና ሕያው በሆነው በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፣ በሕይወት ብኖርም ሆነ ብሞት ጌታዬ ንጉሡ በሚገኝበት በማንኛውም ቦታ ሁሉ እኔ አገልጋይህም በዚያ እሆናለሁ!” ሲል መለሰ።+ 22 በዚህ ጊዜ ዳዊት ኢታይን+ “እሺ፣ እለፍ” አለው። በመሆኑም ጌታዊው ኢታይ ከሰዎቹና ከልጆቹ ሁሉ ጋር አለፈ።
23 እነዚህ ሁሉ ሰዎች በሚያልፉበት ጊዜ በአካባቢው ያሉ ሰዎች በሙሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያለቅሱ ነበር፤ ንጉሡም በቄድሮን ሸለቆ+ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ምድረ በዳው ወደሚወስደው መንገድ ተሻገረ። 24 ሳዶቅም+ በዚያ ነበር፤ የእውነተኛውን አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት+ የተሸከሙት ሌዋውያንም+ በሙሉ ከእሱ ጋር ነበሩ፤ እነሱም የእውነተኛውን አምላክ ታቦት አስቀመጡት፤ ሕዝቡ ሁሉ ከተማዋን ለቆ ከተሻገረም በኋላ አብያታር+ ወጣ። 25 ሆኖም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፦ “የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወደ ከተማዋ መልሱት።+ በይሖዋ ፊት ሞገስ ካገኘሁ እንድመለስና ታቦቱንም ሆነ ማደሪያ ስፍራውን እንዳይ ያደርገኝ ይሆናል።+ 26 ይሁንና እሱ ‘በአንተ አልተደሰትኩም’ ካለኝ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግብኝ።” 27 ንጉሡም ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፦ “አንተ ባለ ራእይ አይደለህም?+ በል እንግዲህ ወደ ከተማዋ በሰላም ተመለስ፤ ሁለቱን ልጆቻችሁን ማለትም የገዛ ልጅህን አኪማዓስንና የአብያታርን ልጅ ዮናታንን+ ይዘህ ተመለስ። 28 እኔም ከእናንተ አንድ መልእክት እስኪመጣልኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኙት መልካዎች* አጠገብ እቆያለሁ።”+ 29 ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እነሱም በዚያ ተቀመጡ።
30 ዳዊት የደብረ ዘይትን ተራራ*+ ሽቅብ ሲወጣ እያለቀሰ ነበር፤ እሱም ራሱን ተከናንቦ ባዶ እግሩን ይሄድ ነበር። አብረውት የነበሩት ሰዎችም ሁሉ ራሳቸውን ተከናንበው እያለቀሱ ሽቅብ ወጡ። 31 ከዚያም ዳዊት “ከአቢሴሎም+ ጋር ካሴሩት+ ሰዎች አንዱ እኮ አኪጦፌል ነው” ተብሎ ተነገረው። በዚህ ጊዜ ዳዊት “ይሖዋ ሆይ፣+ እባክህ የአኪጦፌልን ምክር የሞኝ ምክር+ አድርገው!” አለ።
32 ዳዊት ሕዝቡ ለአምላክ ይሰግድበት ወደነበረው የተራራ ጫፍ ሲደርስ አርካዊው+ ኩሲ+ ልብሱን ቀዶና በራሱ ላይ አቧራ ነስንሶ እሱን ለማግኘት በዚያ ይጠባበቅ ነበር። 33 ዳዊት ግን እንዲህ አለው፦ “አብረኸኝ የምትሻገር ከሆነ ሸክም ትሆንብኛለህ። 34 ከዚህ ይልቅ ወደ ከተማዋ ተመልሰህ አቢሴሎምን ‘ንጉሥ ሆይ፣ እኔ የአንተ አገልጋይ ነኝ።+ ቀደም ሲል የአባትህ አገልጋይ ነበርኩ፤ አሁን ግን የአንተ አገልጋይ ነኝ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር ታከሽፍልኛለህ።+ 35 ካህናት የሆኑት ሳዶቅና አብያታር እዚያው ከአንተ ጋር አይደሉም? ከንጉሡ ቤት የምትሰማውን ነገር ሁሉ ካህናት ለሆኑት ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው።+ 36 ከእነሱም ጋር ሁለቱ ልጆቻቸው ማለትም የሳዶቅ ልጅ አኪማዓስና+ የአብያታር ልጅ ዮናታን+ አሉ፤ እናንተም የምትሰሙትን ማንኛውንም ነገር በእነሱ በኩል ልካችሁ አሳውቁኝ።” 37 በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የዳዊት ወዳጅ*+ የሆነው ኩሲ ወደ ከተማዋ ሄደ።