አንደኛ ሳሙኤል
30 በሦስተኛው ቀን ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ጺቅላግ+ ሲመጡ አማሌቃውያን+ በስተ ደቡብ* ያለውን አካባቢና ጺቅላግን ወረው ነበር፤ እነሱም በጺቅላግ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፤ በእሳትም አቃጠሏት። 2 ሴቶችንና+ በዚያ የነበሩትንም ሁሉ ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ማርከው ወሰዱ። አንድም ሰው አልገደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ሁሉንም ይዘው ሄዱ። 3 ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ጺቅላግ ሲመጡ ከተማዋ በእሳት ተቃጥላ አገኟት፤ ሚስቶቻቸውም ሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው በምርኮ ተወስደው ነበር። 4 በመሆኑም ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ለማልቀስ አቅም እስኪያጡ ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። 5 ሁለቱ የዳዊት ሚስቶችም ማለትም ኢይዝራኤላዊቷ አኪኖዓም እና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢጋኤል በምርኮ ተወስደው ነበር።+ 6 ዳዊት ሰዎቹ ሊወግሩት እየተማከሩ ስለነበር እጅግ ተጨነቀ፤ ምክንያቱም ሰዎቹ* ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው በመወሰዳቸው ተመርረው ነበር። ይሁንና ዳዊት በአምላኩ በይሖዋ ራሱን አበረታ።+
7 ከዚያም ዳዊት የአሂሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን+ “እባክህ፣ ኤፉዱን አምጣልኝ”+ አለው። አብያታርም ኤፉዱን ለዳዊት አመጣለት። 8 ዳዊትም “ይህን ወራሪ ቡድን ላሳደው? እደርስበት ይሆን?” ሲል ይሖዋን ጠየቀ።+ እሱም “በእርግጥ ስለምትደርስባቸውና የወሰዱትን ሁሉ ከእጃቸው ስለምታስጥል ሂድ አሳዳቸው” አለው።+
9 ዳዊትም ወዲያውኑ አብረውት ከነበሩት 600 ሰዎች+ ጋር ወጣ፤ እነሱም እስከ በሶር ሸለቆ* ድረስ ሄዱ፤ በዚያም የተወሰኑ ሰዎች ወደ ኋላ ቀሩ። 10 ዳዊትም ከ400 ሰዎች ጋር ሆኖ ማሳደዱን ቀጠለ፤ በጣም ከመድከማቸው የተነሳ የበሶርን ሸለቆ መሻገር ያልቻሉት 200 ሰዎች ግን እዚያው ቀሩ።+
11 ከዚያም ሜዳ ላይ አንድ ግብፃዊ አግኝተው ወደ ዳዊት አመጡት። የሚበላው ምግብና የሚጠጣው ውኃ ሰጡት። 12 በተጨማሪም ቁራሽ የበለስ ጥፍጥፍና ሁለት የዘቢብ ቂጣ ሰጡት። እሱም ከበላ በኋላ ብርታት አገኘ፤* ምክንያቱም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ሙሉ እህልም ሆነ ውኃ አልቀመሰም ነበር። 13 ዳዊትም “ለመሆኑ አንተ የማን ነህ? የመጣኸውስ ከየት ነው?” አለው፤ እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ “እኔ ለአንድ አማሌቃዊ ባሪያ የሆንኩ ግብፃዊ ነኝ፤ ሆኖም ከሦስት ቀን በፊት ታምሜ ስለነበር ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ። 14 የከሪታውያንን+ ምድር ደቡባዊ ክፍል፣* የይሁዳን ግዛትና የካሌብን+ ደቡባዊ ክፍል* ወረርን፤ ጺቅላግንም በእሳት አጋየናት።” 15 በዚህ ጊዜ ዳዊት “ይህ ወራሪ ቡድን ወዳለበት መርተህ ትወስደኛለህ?” አለው። እሱም “ብቻ እንደማትገድለኝና ለጌታዬ አሳልፈህ እንደማትሰጠኝ በአምላክ ማልልኝ እንጂ ወራሪው ቡድን ወዳለበት መርቼ አደርስሃለሁ” አለው።
16 በመሆኑም ሰዎቹ ከፍልስጤማውያን ምድርና ከይሁዳ ምድር በወሰዱት ታላቅ ምርኮ የተነሳ በየቦታው ተበታትነው ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ይደሰቱ ወደነበረበት ቦታ መርቶ ወሰደው። 17 ከዚያም ዳዊት ጎህ ሳይቀድ ጀምሮ እስከ ማግስቱ ምሽት ድረስ መታቸው፤ ፈጽሞም አጠፋቸው፤ በግመል ተቀምጠው ከሸሹት 400 ሰዎች በስተቀር አንድም ሰው አላመለጠም።+ 18 ዳዊትም አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣለ፤+ ሁለቱን ሚስቶቹንም አስመለሰ። 19 ከትንሽ እስከ ትልቅ ምንም የጎደለ ነገር አልነበረም። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ሆነ ዘርፈው የወሰዱባቸውን ንብረት ሁሉ አስመለሱ፤+ ዳዊት የወሰዱትን ሁሉ አስመለሰ። 20 በመሆኑም ዳዊት መንጎቹንና ከብቶቹን በሙሉ ወሰደ፤ እነሱም ከራሳቸው ከብቶች ፊት ፊት ነዷቸው። እነሱም “ይህ የዳዊት ምርኮ ነው” አሉ።
21 ከዚያም ዳዊት በጣም ከመድከማቸው የተነሳ አብረውት ሊሄዱ ወዳልቻሉትና በበሶር ሸለቆ+ ቀርተው ወደነበሩት 200 ሰዎች መጣ፤ እነሱም ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ለመቀበል ወጡ። ዳዊትም ወደ ሰዎቹ በቀረበ ጊዜ ስለ ደህንነታቸው ጠየቃቸው። 22 ሆኖም ከዳዊት ጋር አብረው ከሄዱት መካከል ክፉ የሆኑትና የማይረቡት ሰዎች “እነዚህ ሰዎች አብረውን ስላልሄዱ እያንዳንዳቸው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ይሂዱ እንጂ ካመጣነው ምርኮ ላይ ምንም ነገር አንሰጣቸውም” አሉ። 23 ዳዊት ግን እንዲህ አለ፦ “ወንድሞቼ ይሖዋ በሰጠን ነገርማ እንዲህ ማድረግ የለባችሁም። የጠበቀንና የመጣብንን ወራሪ ቡድን በእጃችን አሳልፎ የሰጠን እሱ ነው።+ 24 ታዲያ አሁን ይህን የምትሉትን ማን ይሰማችኋል? ወደ ውጊያ የዘመተው ሰው የሚያገኘው ድርሻና ጓዝ የጠበቀው ሰው የሚያገኘው ድርሻ እኩል ነው።+ ሁሉም ድርሻ ይኖረዋል።”+ 25 ዳዊትም ከዚያ ቀን ጀምሮ እስከዚህ ዕለት ድረስ ይህን ለእስራኤል ሥርዓትና ደንብ አድርጎ አጸደቀው።
26 ዳዊትም ወደ ጺቅላግ በተመለሰ ጊዜ “ከይሖዋ ጠላቶች ከተገኘው ምርኮ የተሰጠ ስጦታ* ይኸውላችሁ” በማለት ወዳጆቹ ለሆኑት የይሁዳ ሽማግሌዎች ከምርኮው ላይ የተወሰነውን ላከ። 27 ስጦታውንም በቤቴል፣+ በኔጌብ* ራሞት፣ በያቲር፣+ 28 በአሮዔር፣ በሲፍሞት፣ በኤሽተሞዓ፣+ 29 በራካል፣ በየራህምኤል+ ከተሞች፣ በቄናውያን+ ከተሞች፣ 30 በሆርማ፣+ በቦርአሻን፣ በአታክ፣ 31 በኬብሮን+ እንዲሁም ዳዊትና ሰዎቹ በሚያዘወትሩባቸው ስፍራዎች ሁሉ ለነበሩት ላከ።