ለፊልሞና የተጻፈ ደብዳቤ
1 ለክርስቶስ ኢየሱስ ሲል እስረኛ ከሆነው ከጳውሎስና+ ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፣+ ለተወደደው የሥራ ባልደረባችን ለፊልሞና፣ 2 ለእህታችን ለአፍብያና አብሮን የክርስቶስ ወታደር ለሆነው ለአርክጳ+ እንዲሁም በቤትህ ላለው ጉባኤ፦+
3 አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
4 አንተን በጸሎቴ በጠቀስኩ ቁጥር ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤+ 5 ስለ እምነትህ እንዲሁም ለጌታ ኢየሱስና ለቅዱሳን ሁሉ ስላለህ ፍቅር እሰማለሁና። 6 ከሌሎች ጋር የምትጋራው እምነት በክርስቶስ አማካኝነት መልካም ነገሮችን ሁሉ እንደተቀበልን እንድትገነዘብ ይረዳህ ዘንድ እጸልያለሁ። 7 ወንድሜ ሆይ፣ ስለምታሳየው ፍቅር በመስማቴ እጅግ ተደስቻለሁ እንዲሁም ተጽናንቻለሁ፤ ምክንያቱም የቅዱሳን ልብ* በአንተ አማካኝነት ታድሷል።
8 ስለዚህ ተገቢ የሆነውን ነገር እንድታደርግ አንተን ለማዘዝ ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ሙሉ ነፃነት ቢኖረኝም፣ 9 እኔ ጳውሎስ አረጋዊና አሁን ደግሞ ለክርስቶስ ኢየሱስ ስል እስረኛ እንደመሆኔ መጠን ፍቅርን መሠረት በማድረግ እለምንሃለሁ። 10 በእስር ላይ እያለሁ እንደ አባት የሆንኩለትን+ ልጄን አናሲሞስን+ በተመለከተ እለምንሃለሁ። 11 እሱ ቀደም ሲል ምንም አይጠቅምህም ነበር፤ አሁን ግን ለአንተም ሆነ ለእኔ የሚጠቅም ሰው ሆኗል። 12 እሱን፣ አዎ ከልቤ የምወደውን እሱን ወደ አንተ መልሼ ልኬዋለሁ።
13 ለምሥራቹ ስል እዚህ ታስሬ ሳለሁ+ በአንተ ፋንታ እኔን እንዲያገለግል ለራሴ እዚሁ ባስቀረው ደስ ይለኝ ነበር። 14 ነገር ግን የምታደርገው መልካም ነገር በራስህ ፈቃድ እንጂ በግዴታ እንዳይሆን አንተ ሳትስማማ ምንም ነገር ማድረግ አልፈልግም።+ 15 ምናልባት ለአጭር ጊዜ* ከአንተ ጠፍቶ የሄደው፣ ተመልሶ ለዘለቄታው የአንተ ሆኖ እንዲኖር ይሆናል፤ 16 ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ+ ሳይሆን ከባሪያ ይበልጥ እንደተወደደ ወንድምህ ነው፤+ በተለይ ለእኔ ተወዳጅ ወንድም ነው፤ ሆኖም በሰብዓዊ ግንኙነታችሁም ሆነ ከጌታ ጋር ባላችሁ ዝምድና ለአንተ ይበልጥ ተወዳጅ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። 17 ስለዚህ እኔን እንደ ወዳጅ አድርገህ ከቆጠርከኝ እኔን እንደምትቀበለኝ አድርገህ እሱን በደግነት ተቀበለው። 18 ከዚህም በተጨማሪ የበደለህ ነገር ካለ ወይም የአንተ ዕዳ ካለበት ዕዳውን በእኔ ላይ አስበው። 19 እኔ ጳውሎስ ይህን በራሴ እጅ ጽፌልሃለሁ፦ ያለበትን ዕዳ እኔ እከፍልሃለሁ፤ ደግሞም ከሕይወትህ ጋር በተያያዘም እንኳ የእኔ ባለዕዳ እንደሆንክ መናገር አያስፈልገኝም። 20 ወንድሜ ሆይ፣ ሁለታችንም የጌታ ደቀ መዛሙርት በመሆናችን በዚህ ረገድ እንድትተባበረኝ እፈልጋለሁ፦ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደመሆንህ መጠን ልቤን* አድስልኝ።
21 ይህን የምጽፍልህ በዚህ እንደምትስማማ በመተማመንና ከምጠይቅህም በላይ እንደምታደርግ በማወቅ ነው። 22 ከዚህም ሌላ ጸሎታችሁ ተሰምቶ ወደ እናንተ እንደምመለስ*+ ተስፋ ስለማደርግ ማረፊያ አዘጋጅልኝ።
23 በክርስቶስ ኢየሱስ የተነሳ አብሮኝ እስረኛ የሆነው ኤጳፍራ+ ሰላምታ ያቀርብልሃል፤ 24 የሥራ ባልደረቦቼ የሆኑት ማርቆስ፣ አርስጥሮኮስ፣+ ዴማስና+ ሉቃስም+ ሰላም ብለውሃል።
25 የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እናንተ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን።