ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ
7 አብርሃም ነገሥታትን ድል አድርጎ ሲመለስ የሳሌም ንጉሥና የልዑሉ አምላክ ካህን የሆነው ይህ መልከጼዴቅ አግኝቶት ባረከው፤+ 2 አብርሃም ደግሞ ከሁሉ ነገር አንድ አሥረኛ ሰጠው።* በመጀመሪያ ስሙ “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው፤ ደግሞም የሳሌም ንጉሥ ማለትም “የሰላም ንጉሥ” ነው። 3 አባትና እናትም ሆነ የዘር ሐረግ እንዲሁም ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን ልጅ እንዲመስል በመደረጉ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።+
4 እንግዲህ የቤተሰብ ራስ* የሆነው አብርሃም ምርጥ ከሆነው ምርኮ ላይ አንድ አሥረኛውን የሰጠው+ ይህ ሰው ምን ያህል ታላቅ እንደነበረ ተመልከቱ። 5 እርግጥ የክህነት ኃላፊነት የሚቀበሉ ከሌዊ ልጆች ወገን የሆኑት ሰዎች+ ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም ከሕዝቡ ማለትም ከገዛ ወንድሞቻቸው አሥራት እንዲሰበስቡ ሕጉ ያዛል።+ 6 ሆኖም ከእነሱ የትውልድ ሐረግ ያልመጣው ይህ ሰው ከአብርሃም አሥራት የተቀበለ ሲሆን የተስፋ ቃል የተሰጠውን ሰው ባርኮታል።+ 7 እንግዲህ አነስተኛ የሆነው ከእሱ በሚበልጠው እንደተባረከ ምንም ጥርጥር የለውም። 8 በአንድ በኩል አሥራት የሚቀበሉት ሟች የሆኑ ሰዎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ግን አሥራት የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሠከረለት ሰው ነው።+ 9 እንግዲህ አሥራት የሚቀበለው ሌዊ እንኳ በአብርሃም በኩል አሥራት ከፍሏል ማለት ይቻላል፤ 10 መልከጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ውስጥ* ነበርና።+
11 እንግዲህ ፍጽምና ሊገኝ የሚችለው በሌዊ ክህነት አማካኝነት ቢሆን ኖሮ+ (ክህነቱ ለሕዝቡ የተሰጠው ሕግ አንዱ ገጽታ ስለሆነ)፣ እንደ አሮን ሥርዓት ሳይሆን እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት+ ያለ ተብሎ የተነገረለት ሌላ ካህን መነሳቱ ምን ያስፈልግ ነበር? 12 ክህነቱ ስለሚለወጥ ሕጉም የግድ መለወጥ ያስፈልገዋልና።+ 13 ይህ ሁሉ ነገር የተነገረለት ሰው ከሌላ ነገድ የመጣ ነውና፤ ከዚህ ነገድ ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም።+ 14 ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የታወቀ ነውና፤+ ይሁንና ሙሴ ከዚህ ነገድ ካህናት እንደሚገኙ የተናገረው ነገር የለም።
15 ደግሞም እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን+ ሲነሳ ይህ ጉዳይ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤+ 16 እሱ ካህን የሆነው በሥጋዊ ትውልድ ላይ በተመካውና ሕጉ በያዘው መሥፈርት ሳይሆን የማይጠፋ ሕይወት+ እንዲኖረው ባስቻለው ኃይል ነው። 17 “እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመሥክሮለታልና።+
18 እንግዲህ የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና ፍሬ ቢስ በመሆኑ ተሽሯል።+ 19 ሕጉ የትኛውንም ነገር ወደ ፍጽምና አላደረሰምና፤+ ወደ አምላክ የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ+ መሰጠቱ ግን ይህን ማድረግ ችሏል።+ 20 በተጨማሪም ይህ ያለመሐላ እንዳልሆነ ሁሉ 21 (ያለመሐላ ካህናት የሆኑ ሰዎች አሉና፤ እሱ ግን በመሐላ ካህን ሆኗል፤ ይህም የሆነው “ይሖዋ* ‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሏል፤ ደግሞም ሐሳቡን አይለውጥም”* በማለት ስለ እሱ የተናገረው አምላክ በማለው መሐላ መሠረት ነው፤)+ 22 እንደዚሁም ኢየሱስ ለተሻለ ቃል ኪዳን ዋስትና* ሆኗል።+ 23 ከዚህም በተጨማሪ ካህናት አገልግሎታቸውን እንዳይቀጥሉ ሞት ስለሚያግዳቸው አንዱ ሌላውን እየተካ እንዲያገለግል ብዙዎች ካህናት መሆን ነበረባቸው፤+ 24 እሱ ግን ለዘላለም+ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር ክህነቱ ተተኪ የለውም። 25 ስለሆነም ለእነሱ ለመማለድ ሁልጊዜ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ የሚቀርቡትን ፈጽሞ ሊያድናቸውም ይችላል።+
26 እኛ የሚያስፈልገን ታማኝ፣ ቅን የሆነ፣ ያልረከሰ፣+ ከኃጢአተኞች የተለየና ከሰማያት በላይ ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ነው።+ 27 እነዚያ ሊቃነ ካህናት ያደርጉ እንደነበረው፣ በመጀመሪያ ለራሱ ኃጢአት ከዚያም ለሕዝቡ ኃጢአት+ በየዕለቱ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤+ ምክንያቱም ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ይህን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈጽሞታል።+ 28 ሕጉ ድክመት ያለባቸውን ሰዎች ሊቃነ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤+ ከሕጉ በኋላ የመጣው የመሐላ ቃል+ ግን ለዘላለም ፍጹም የተደረገውን ልጅ+ ይሾማል።