ዘፍጥረት
23 ሣራም 127 ዓመት ኖረች፤ ሣራ በሕይወት የኖረችው ይህን ያህል ዓመት ነበር።+ 2 ሣራም በቂርያትአርባ+ ይኸውም በከነአን ምድር+ በሚገኘው በኬብሮን+ ሞተች፤ አብርሃምም በሣራ ሞት ያዝንና ያለቅስ ጀመር። 3 ከዚያም አብርሃም ከሚስቱ አስከሬን አጠገብ ተነሳ፤ የሄትንም+ ወንዶች ልጆች እንዲህ አላቸው፦ 4 “እኔ በመካከላችሁ የምኖር የባዕድ አገር ሰውና ሰፋሪ ነኝ።+ አስከሬኔን ወስጄ እንድቀብር በመካከላችሁ የመቃብር ቦታ የሚሆን መሬት ስጡኝ።” 5 በዚህ ጊዜ የሄት ወንዶች ልጆች ለአብርሃም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ 6 “ስማን ጌታዬ። አንተ እኮ በመካከላችን አምላክ የመረጠህ አለቃ* ነህ።+ ካሉን የመቃብር ስፍራዎች ምርጥ በሆነው ቦታ አስከሬንህን መቅበር ትችላለህ። ከእኛ መካከል አስከሬንህን እንዳትቀብር የመቃብር ቦታውን የሚከለክልህ ማንም የለም።”
7 በመሆኑም አብርሃም ተነሳ፤ ለዚያ አገር ሰዎች ይኸውም ለሄት+ ወንዶች ልጆች ሰገደ፤ 8 እንዲህም አላቸው፦ “አስከሬኔን ወስጄ እንድቀብር ከፈቀዳችሁልኝ* አንዴ ስሙኝ፤ የጾሃር ልጅ የሆነውን ኤፍሮንን 9 በእርሻ ቦታው ዳርቻ ላይ የሚገኘውን የእሱ ንብረት የሆነውን የማክፈላ ዋሻ እንዲሸጥልኝ ለምኑልኝ። የመቃብር ስፍራ የሚሆን ርስት+ እንዲኖረኝ ቦታው የሚያወጣውን ብር+ በሙሉ ልስጠውና በእናንተ ፊት ይሽጥልኝ።”
10 ኤፍሮን በሄት ወንዶች ልጆች መካከል ተቀምጦ ነበር። ስለሆነም ሂታዊው ኤፍሮን የሄት ወንዶች ልጆች እየሰሙ በከተማው በር+ በሚገቡት ሰዎች ሁሉ ፊት ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ 11 “የለም ጌታዬ! አዳምጠኝ። የእርሻ ቦታውንም ሆነ በውስጡ ያለውን ዋሻ ሰጥቼሃለሁ። የሕዝቤ ልጆች በተገኙበት ለአንተ ሰጥቼሃለሁ። አስከሬንህን በዚያ ቅበር።” 12 በዚህ ጊዜ አብርሃም በአገሩ ሰዎች ፊት ሰገደ፤ 13 የአገሩ ሰዎችም እየሰሙ ኤፍሮንን እንዲህ አለው፦ “ፈቃድህ ከሆነ ስማኝ! የእርሻ ቦታው የሚያወጣውን ብር በሙሉ እሰጥሃለሁ። አስከሬኔን በዚያ እንድቀብር ብሩን ተቀበለኝ።”
14 ከዚያም ኤፍሮን ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰ፦ 15 “ጌታዬ እኔ የምልህን ስማኝ። የዚህ መሬት ዋጋ 400 የብር ሰቅል* ነው፤ ታዲያ ይህ በእኔና በአንተ መካከል ያን ያህል ትልቅ ነገር ሆኖ ነው? ይልቁንስ አስከሬንህን በዚያ ቅበር።” 16 አብርሃም፣ ኤፍሮን ያለውን ሰማ፤ አብርሃምም ኤፍሮን በሄት ወንዶች ልጆች ፊት የተናገረውን የብር መጠን ሰጠው፤ በነጋዴዎቹ ዘንድ ተቀባይነት ባለው ሚዛን መሠረት 400 ሰቅል* ብር ለኤፍሮን መዘነለት።+ 17 በዚህ መንገድ በማምሬ ፊት ለፊት የነበረው በማክፈላ የሚገኘው የኤፍሮን የእርሻ ቦታ ይኸውም የእርሻ ቦታው፣ በውስጡ ያለው ዋሻና በእርሻ ቦታው ክልል ውስጥ የሚገኙት ዛፎች በሙሉ 18 አብርሃም የገዛቸው ንብረቶች መሆናቸው የሄት ወንዶች ልጆች በተገኙበት በከተማው በር በሚገቡት ሰዎች ሁሉ ፊት ተረጋገጠ። 19 ከዚያ በኋላ አብርሃም ሚስቱን ሣራን በማምሬ ይኸውም በከነአን ምድር ባለው በኬብሮን ፊት ለፊት በሚገኘው በማክፈላ የእርሻ ቦታ ውስጥ ባለው ዋሻ ቀበራት። 20 በዚህ መንገድ የእርሻ ቦታውና በውስጡ የሚገኘው ዋሻ የመቃብር ቦታ እንዲሆን ከሄት ወንዶች ልጆች ለአብርሃም በርስትነት ተሰጠ።+