ዘካርያስ
5 ዳግመኛ ቀና ብዬ ስመለከት የሚበር ጥቅልል አየሁ። 2 እሱም “የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ።
እኔም “ርዝመቱ 20 ክንድ፣* ወርዱ ደግሞ 10 ክንድ የሆነ የሚበር ጥቅልል አያለሁ” ስል መለስኩለት።
3 ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ በመላው ምድር ላይ የሚወጣው እርግማን ነው፤ ምክንያቱም የሚሰርቁ ሁሉ+ በአንደኛው በኩል በተጻፈው መሠረት አልተቀጡም፤ ደግሞም በሐሰት የሚምሉ ሁሉ+ በሌላኛው በኩል በተጻፈው መሠረት አልተቀጡም። 4 ‘እኔ ልኬዋለሁ’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ ‘ወደ ሌባውም ቤት ይገባል፤ በስሜ በሐሰት ወደሚምለውም ሰው ቤት ይገባል፤ በዚያም ቤት ውስጥ ይቀመጣል፤ እንጨቱንና ድንጋዩን ጨምሮ ቤቱን ይበላዋል።’”
5 ከዚያም ሲያነጋግረኝ የነበረው መልአክ ወደ እኔ ቀርቦ “እባክህ ቀና ብለህ የምትወጣውን ነገር ተመልከት” አለኝ።
6 እኔም “ምንድን ነች?” አልኩ።
እሱም መልሶ “ይህች የምትወጣው የኢፍ መስፈሪያ* ናት” አለ። አክሎም “በምድሪቱ ሁሉ የሰዎቹ መልክ ይህ ነው” አለ። 7 እኔም ከእርሳስ የተሠራው ክቡ መክደኛ ሲነሳ አየሁ፤ በመስፈሪያዋም ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር። 8 እሱም “ይህች ሴት ክፋትን ታመለክታለች” አለኝ። ከዚያም የኢፍ መስፈሪያዋ ውስጥ መልሶ ጣላት፤ ቀጥሎም ከእርሳስ የተሠራውን ከባዱን መክደኛ መስፈሪያዋ አፍ ላይ ገጠመው።
9 ከዚያም ቀና ብዬ ስመለከት ሁለት ሴቶች ወደ ፊት ሲመጡ አየሁ፤ በነፋስም መካከል ወደ ላይ ተወነጨፉ። ክንፎቻቸው የራዛ* ዓይነት ክንፎች ነበሩ። እነሱም መስፈሪያዋን በምድርና በሰማይ መካከል አነሷት። 10 እኔም ያነጋግረኝ የነበረውን መልአክ “የኢፍ መስፈሪያዋን ወዴት እየወሰዷት ነው?” ስል ጠየቅኩት።
11 እሱም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ቤት ሊሠሩላት ወደ ሰናኦር*+ ምድር እየወሰዷት ነው፤ ቤቱም በተዘጋጀ ጊዜ በዚያ በተገቢው ቦታዋ ላይ ያስቀምጧታል።”