ኢያሱ
5 ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ* የሚገኙት የአሞራውያን+ ነገሥታት ሁሉ እንዲሁም በባሕሩ አጠገብ ያሉት የከነአናውያን+ ነገሥታት በሙሉ ይሖዋ እስራኤላውያን ዮርዳኖስን እስኪሻገሩ ድረስ የወንዙን ውኃ በፊታቸው እንዳደረቀው ሲሰሙ ልባቸው ቀለጠ፤+ በእስራኤላውያንም የተነሳ ወኔ ከድቷቸው ነበር።*+
2 በዚያን ጊዜ ይሖዋ ኢያሱን “የባልጩት ቢላ ሠርተህ እስራኤላውያን ወንዶችን እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ግረዛቸው”+ አለው። 3 ስለሆነም ኢያሱ የባልጩት ቢላ ሠርቶ እስራኤላውያን ወንዶችን ጊብዓትሃራሎት* በተባለ ስፍራ ገረዛቸው።+ 4 ኢያሱ የገረዛቸው በዚህ የተነሳ ነው፦ ከግብፅ በወጣው ሕዝብ መካከል የነበሩት ወንዶች ሁሉ ይኸውም ለውጊያ ብቁ የሆኑት* ወንዶች በሙሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በጉዞ ላይ ሳሉ በምድረ በዳ ሞተዋል።+ 5 ከግብፅ የወጣው ሕዝብ ሁሉ ተገርዞ ነበር፤ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በጉዞ ላይ ሳሉ በምድረ በዳ የተወለደው ሕዝብ ግን አልተገረዘም ነበር። 6 መላው ብሔር ይኸውም የይሖዋን ቃል ያልታዘዙት+ ከግብፅ የወጡት ለውጊያ ብቁ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ሞተው እስኪያልቁ ድረስ እስራኤላውያን በምድረ በዳ 40 ዓመት ተጓዙ።+ ይሖዋም ለእኛ ለመስጠት ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር+ ይኸውም ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር+ እንዲያዩ ፈጽሞ እንደማይፈቅድላቸው ይሖዋ ምሎ ነበር።+ 7 በመሆኑም በእነሱ ምትክ ወንዶች ልጆቻቸውን አስነሳ።+ ኢያሱም እነዚህን ገረዛቸው፤ ምክንያቱም በጉዞ ላይ ሳሉ ስላልገረዟቸው ከነሸለፈታቸው ነበሩ።
8 እነሱም መላውን ብሔር ገርዘው ሲጨርሱ የተገረዙት ከቁስላቸው እስኪያገግሙ ድረስ እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ቆዩ።
9 ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን “በዛሬው ዕለት የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ” አለው። በመሆኑም የዚያ ስፍራ ስም ጊልጋል*+ ተባለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የሚታወቀው በዚሁ ስሙ ነው።
10 እስራኤላውያንም በጊልጋል እንደሰፈሩ ቆዩ፤ ወሩ በገባ በ14ኛው ቀን ምሽት ላይም በኢያሪኮ በረሃማ ሜዳ የፋሲካን* በዓል አከበሩ።+ 11 ከፋሲካውም ቀን በኋላ በዚያው ዕለት የምድሪቱን ፍሬ ማለትም ቂጣና*+ የተጠበሰ እሸት በሉ። 12 ከምድሪቱ ፍሬ በበሉበት ቀን ማግስት መናው ተቋረጠ፤+ ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን መና አልወረደላቸውም፤ ከዚህ ይልቅ በዚያ ዓመት የከነአንን ምድር ፍሬ መብላት ጀመሩ።+
13 ኢያሱ በኢያሪኮ አቅራቢያ ሳለ፣ ቀና ብሎ ሲመለከት የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ+ አንድ ሰው ፊት ለፊቱ ቆሞ አየ።+ ኢያሱም ወደ እሱ ሄዶ “ከእኛ ወገን ነህ ወይስ ከጠላቶቻችን?” ሲል ጠየቀው። 14 እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ “አይደለሁም፤ እኔ አሁን የመጣሁት የይሖዋ ሠራዊት አለቃ ሆኜ ነው።”+ በዚህ ጊዜ ኢያሱ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ በመስገድ “ታዲያ ጌታዬ ለአገልጋዩ የሚነግረው ምንድን ነው?” አለው። 15 የይሖዋ ሠራዊት አለቃም ኢያሱን “የቆምክበት ስፍራ ቅዱስ ስለሆነ ጫማህን አውልቅ” አለው። ኢያሱም ወዲያውኑ እንደተባለው አደረገ።+