ዘኁልቁ
18 ከዚያም ይሖዋ አሮንን እንዲህ አለው፦ “ከመቅደሱ+ ጋር በተያያዘ ለሚፈጸመው ማንኛውም በደል አንተ፣ ከአንተም ጋር ወንዶች ልጆችህና የአባትህ ቤት ተጠያቂ ትሆናላችሁ፤ ከክህነታችሁ ጋር በተያያዘ ለሚፈጸመው ማንኛውም በደል አንተ፣ ከአንተም ጋር ወንዶች ልጆችህ ተጠያቂ ትሆናላችሁ።+ 2 በተጨማሪም በምሥክሩ ድንኳን+ ፊት ከአንተ ጋር አብረው እንዲሆኑ እንዲሁም አንተንና ወንዶች ልጆችህን እንዲያገለግሉ+ ከአባትህ ነገድ ይኸውም ከሌዊ ነገድ የሆኑትን ወንድሞችህን አቅርባቸው። 3 ከአንተም ሆነ በአጠቃላይ ከድንኳኑ ጋር በተያያዘ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ይወጡ።+ ይሁንና አንተም ሆንክ እነሱ እንዳትሞቱ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ዕቃዎችና ወደ መሠዊያው አይቅረቡ።+ 4 እነሱም ከእናንተ ጋር በመሆን ከመገናኛ ድንኳኑና በድንኳኑ ከሚከናወነው አገልግሎት ሁሉ ጋር በተያያዘ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ይወጣሉ፤ ያልተፈቀደለት ማንኛውም ሰው* ወደ እናንተ መቅረብ የለበትም።+ 5 እናንተም በእስራኤል ሕዝብ ላይ ዳግም ቁጣ እንዳይመጣ+ ከቅዱሱ ስፍራና ከመሠዊያው+ ጋር በተያያዘ የተጣለባችሁን ኃላፊነት ተወጡ።+ 6 እኔ ራሴ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን ሌዋውያን ከእስራኤላውያን መካከል ወስጄ ለእናንተ ስጦታ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ።+ እነሱም በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ የሚከናወነውን አገልግሎት እንዲፈጽሙ ለይሖዋ የተሰጡ ናቸው።+ 7 ከመሠዊያውና በመጋረጃው ውስጥ ካለው+ ነገር ጋር የተያያዙትን የክህነት ሥራዎቻችሁን የማከናወኑ ኃላፊነት የተጣለው በአንተና በወንዶች ልጆችህ ላይ ነው፤ እናንተም ይህን አገልግሎት ታከናውናላችሁ።+ የክህነት አገልግሎቱን ለእናንተ ስጦታ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ፤ ወደዚያ የሚቀርብ ማንኛውም ያልተፈቀደለት ሰው* ይገደል።”+
8 በተጨማሪም ይሖዋ አሮንን እንዲህ አለው፦ “ለእኔ በሚቀርቡት መዋጮዎች+ ላይ እኔ ራሴ ኃላፊ አድርጌ ሾሜሃለሁ። እስራኤላውያን የሚያዋጧቸውን ቅዱስ ነገሮች ሁሉ ለአንተና ለወንዶች ልጆችህ ድርሻችሁ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ፤ ይህም ቋሚ ድርሻችሁ ነው።+ 9 በእሳት ከሚቀርቡት እጅግ ቅዱስ የሆኑ መባዎች ውስጥ የሚከተሉት የአንተ ይሆናሉ፦ ለእኔ የሚያመጡትን የእህል መባቸውን፣+ የኃጢአት መባቸውንና+ የበደል መባቸውን+ ጨምሮ የሚያቀርቡት ማንኛውም መባ የአንተ ይሆናል። ይህ ለአንተና ለወንዶች ልጆችህ እጅግ የተቀደሰ ነገር ነው። 10 እጅግ ቅዱስ በሆነ ስፍራ ብላው።+ እያንዳንዱ ወንድ ይብላው። ይህ ለአንተ የተቀደሰ ነገር ነው።+ 11 እስራኤላውያን ከሚወዘወዝ መባቸው+ ሁሉ ጋር መዋጮ አድርገው የሚያመጧቸው ስጦታዎች+ የአንተ ይሆናሉ። እነዚህን ለአንተ፣ ከአንተም ጋር ለወንዶች ልጆችህና ለሴቶች ልጆችህ ቋሚ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ።+ በቤትህ ያለ ማንኛውም ንጹሕ የሆነ ሰው ሊበላው ይችላል።+
12 “ለይሖዋ የሚሰጡትን ምርጥ የሆነውን ዘይት ሁሉ፣ ምርጥ የሆነውን አዲስ የወይን ጠጅና እህል ሁሉ ይኸውም የፍሬያቸውን በኩራት+ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።+ 13 በምድራቸው ላይ መጀመሪያ የደረሰው ለይሖዋ የሚያመጡት ፍሬ ሁሉ የአንተ ይሆናል።+ በቤትህ ያለ ማንኛውም ንጹሕ የሆነ ሰው ሊበላው ይችላል።
14 “በእስራኤል ውስጥ ቅዱስ ለሆነ ዓላማ የተለየ ማንኛውም ነገር* የአንተ ይሆናል።+
15 “ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ለይሖዋ የሚያቀርቡት የእያንዳንዱ ሕይወት ያለው ነገር* በኩር ሁሉ+ የአንተ መሆን ይኖርበታል። ሆኖም ከሰው በኩር የሆነውን ሁሉ መዋጀት ይኖርብሃል፤+ እንዲሁም ርኩስ ከሆነ እንስሳ በኩር የሆነውን ሁሉ መዋጀት ይገባሃል።+ 16 አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሲሆነው እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል*+ መሠረት በተተመነለት ዋጋ ይኸውም በአምስት የብር ሰቅል* ወጆ ልትዋጀው ይገባል። አንዱ ሰቅል 20 ጌራ* ነው። 17 በኩር የሆነውን በሬ፣ በኩር የሆነውን ተባዕት በግና በኩር የሆነውን ፍየል ግን መዋጀት የለብህም።+ እነዚህ የተቀደሱ ነገሮች ናቸው። ደማቸውን በመሠዊያው ላይ እርጨው፤+ ስባቸውን ደግሞ ለይሖዋ ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ የሚሰጥ በእሳት የሚቀርብ መባ አድርገህ አጭሰው።+ 18 ሥጋቸው የአንተ ይሆናል። እንደሚወዘወዘው መባ ፍርምባና እንደ ቀኙ እግር ሁሉ ይህም የአንተ ይሆናል።+ 19 እስራኤላውያን ለይሖዋ የሚያዋጧቸውን ቅዱስ መዋጮዎች+ በሙሉ ለአንተ፣ ከአንተም ጋር ለወንዶች ልጆችህና ለሴቶች ልጆችህ ቋሚ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ።+ ይህም በይሖዋ ፊት ለአንተ፣ ከአንተም ጋር ለዘሮችህ የተገባ ዘላቂ የጨው ቃል ኪዳን* ነው።”
20 ይሖዋም በመቀጠል አሮንን እንዲህ አለው፦ “አንተ በምድራቸው ውርሻ አይኖርህም፤ በመካከላቸውም ርስት አይኖርህም።+ በእስራኤላውያን መካከል የአንተ ድርሻም ሆነ ውርሻ እኔ ነኝ።+
21 “እንግዲህ የሌዊ ወንዶች ልጆች ለሚያከናውኑት አገልግሎት ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ ለሚሰጡት አገልግሎት በእስራኤል ውስጥ ያለውን የማንኛውንም ነገር አንድ አሥረኛ ውርሻ አድርጌ እንደሰጠኋቸው+ ልብ በል። 22 ከእንግዲህ እስራኤላውያን ወደ መገናኛ ድንኳኑ መቅረብ አይችሉም፤ ከቀረቡ ግን ኃጢአት ሆኖባቸው ይሞታሉ። 23 በመገናኛ ድንኳኑ የሚቀርበውን አገልግሎት ማከናወን ያለባቸው ሌዋውያኑ ራሳቸው ናቸው፤ ሕዝቡ ለሚፈጽመው ስህተት ተጠያቂ የሚሆኑት እነሱ ናቸው።+ በእስራኤላውያን መካከል በውርስ የሚያገኙት ርስት አይኖራቸውም፤+ ይህም በትውልዶቻችሁ ሁሉ የሚቀጥል ዘላቂ ደንብ ነው። 24 ምክንያቱም የእስራኤል ሕዝብ መዋጮ አድርጎ ለይሖዋ የሚያዋጣውን አንድ አሥረኛ ለሌዋውያኑ ውርሻ አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ። እኔም ‘በእስራኤላውያን መካከል በውርስ የሚያገኙት ርስት አይኖራቸውም’ ያልኳቸው ለዚህ ነው።”+
25 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 26 “ሌዋውያኑን እንዲህ በላቸው፦ ‘ከእስራኤላውያን ላይ ውርሻችሁ አድርጌ የሰጠኋችሁን አንድ አሥረኛ ከእነሱ እጅ ትቀበላላችሁ፤+ እናንተ ደግሞ የአንድ አሥረኛውን አንድ አሥረኛ ለይሖዋ መዋጮ አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ።+ 27 ይህ ለእናንተ እንደ መዋጮ ይኸውም ከአውድማ እንደገባ እህል+ ወይም ከወይን መጭመቂያ አሊያም ከዘይት መጭመቂያ እንደተገኘ የተትረፈረፈ ምርት ተደርጎ ይታሰብላችኋል። 28 በዚህ መንገድ እናንተም ከእስራኤላውያን ከምትቀበሉት አንድ አሥረኛ ሁሉ ላይ ለይሖዋ መዋጮ ታዋጣላችሁ፤ ከእሱም ላይ የይሖዋን መዋጮ ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ። 29 ከምትቀበሏቸው ስጦታዎች+ ሁሉ ላይ ምርጥ የሆነውን እንደ ቅዱስ ነገር አድርጋችሁ ለይሖዋ ሁሉንም ዓይነት መዋጮ ታዋጣላችሁ።’
30 “እንዲህም በላቸው፦ ‘ከስጦታዎቹ ላይ ምርጥ የሆነውን በምታዋጡበት ጊዜ ይህ ለእናንተ ለሌዋውያኑ ከአውድማ እንደገባ ምርት እንዲሁም ከወይን መጭመቂያ ወይም ከዘይት መጭመቂያ እንደተገኘ ምርት ተደርጎ ይታሰብላችኋል። 31 ይህ በመገናኛ ድንኳኑ ለምታከናውኑት አገልግሎት የተሰጠ ደሞዛችሁ ስለሆነ እናንተም ሆናችሁ ቤተሰባችሁ በየትኛውም ቦታ ልትበሉት ትችላላችሁ።+ 32 ከስጦታዎቹ ላይ ምርጥ የሆነውን መዋጮ እስካደረጋችሁ ድረስ ኃጢአት አይሆንባችሁም፤ የእስራኤላውያንን ቅዱስ ነገሮች ማርከስ የለባችሁም፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ግን ትሞታላችሁ።’”+