ሁለተኛ ነገሥት
11 የአካዝያስ እናት ጎቶልያ+ ልጇ መሞቱን+ ባየች ጊዜ ተነስታ የንጉሣውያኑን ቤተሰብ* በሙሉ አጠፋች።+ 2 ይሁንና የአካዝያስ እህት የሆነችው የንጉሥ ኢዮራም ልጅ የሆሼባ ሊገደሉ ከነበሩት የንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮዓስን+ ሰርቃ በመውሰድ እሱንና ሞግዚቱን በውስጠኛው መኝታ ክፍል አስቀመጠቻቸው። እነሱም ጎቶልያ እንዳታየው ደብቀው አቆዩት፤ በመሆኑም ሳይገደል ቀረ። 3 እሱም ከእሷ ጋር ለስድስት ዓመት በይሖዋ ቤት ተደብቆ ቆየ፤ በዚህ ጊዜ ጎቶልያ በምድሪቱ ላይ ትገዛ ነበር።
4 በሰባተኛው ዓመት ዮዳሄ መልእክት ልኮ ካራውያን ጠባቂዎቹንና የቤተ መንግሥቱን ዘቦች* የሚያዙትን መቶ አለቆች+ እሱ ወዳለበት ወደ ይሖዋ ቤት አስመጣ። ከዚያም ከእነሱ ጋር ስምምነት* አደረገ፤ እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ አስማላቸው፤ ይህን ካደረገም በኋላ የንጉሡን ልጅ አሳያቸው።+ 5 እንዲህም ሲል አዘዛቸው፦ “እናንተም እንዲህ ታደርጋላችሁ፦ ከመካከላችሁ አንድ ሦስተኛ የምትሆኑት በሰንበት ቀን ገብታችሁ የንጉሡን ቤት*+ በተጠንቀቅ ትጠብቃላችሁ፤ 6 አንድ ሦስተኛ የምትሆኑት ደግሞ በመሠረት በር ላይ ትሆናላችሁ፤ ሌላው አንድ ሦስተኛ ከቤተ መንግሥቱ ዘቦች ኋላ ባለው በር ላይ ይሆናል። ቤቱን በየተራ ትጠብቃላችሁ። 7 ከመካከላችሁ በሰንበት ቀን ከሥራ ነፃ የሚሆኑት ሁለቱ ቡድኖች ንጉሡን ከጥቃት ለመከላከል የይሖዋን ቤት በተጠንቀቅ ይጠብቁ። 8 እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያችሁን በእጃችሁ ይዛችሁ ንጉሡን ዙሪያውን ክበቡት። ረድፉን ጥሶ የገባ ማንኛውም ሰው ይገደላል። ንጉሡ በሚሄድበት ሁሉ* አብራችሁት ሁኑ።”
9 መቶ አለቆቹ+ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዛቸው አደረጉ። እያንዳንዳቸውም በሰንበት ቀን ተረኛ የሚሆኑትንና በሰንበት ቀን ከሥራ ነፃ የሚሆኑትን የራሳቸውን ሰዎች ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ።+ 10 ከዚያም ካህኑ በይሖዋ ቤት የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮችና ክብ ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው። 11 የቤተ መንግሥቱ ዘቦችም+ እያንዳንዳቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው በስተ ቀኝ በኩል ካለው የቤቱ ጎን አንስቶ በስተ ግራ በኩል እስካለው የቤቱ ጎን ድረስ በመሠዊያውና+ በቤቱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ ቆሙ። 12 ከዚያም ዮዳሄ የንጉሡን ልጅ+ አውጥቶ አክሊሉን* ጫነበት፤ ምሥክሩንም*+ ሰጠው፤ በዚህም መንገድ አነገሡት፤ ደግሞም ቀቡት። እያጨበጨቡም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” ይሉ ጀመር።+
13 ጎቶልያ ሕዝቡ ሲሯሯጥ ስትሰማ ወዲያውኑ በይሖዋ ቤት ወዳለው ሕዝብ መጣች።+ 14 ከዚያም በነበረው ልማድ መሠረት ንጉሡ ዓምዱ አጠገብ ቆሞ አየች።+ አለቆቹና መለከት ነፊዎቹ+ ከንጉሡ ጋር ነበሩ፤ የምድሪቱም ሕዝብ ሁሉ እጅግ እየተደሰተና መለከት እየነፋ ነበር። በዚህ ጊዜ ጎቶልያ ልብሷን ቀዳ “ይህ ሴራ ነው! ሴራ ነው!” በማለት ጮኸች። 15 ካህኑ ዮዳሄ ግን በሠራዊቱ ላይ የተሾሙትን መቶ አለቆች+ “ከረድፉ መካከል አውጧት፤ እሷን ተከትሎ የሚመጣ ሰው ካለ በሰይፍ ግደሉት!” በማለት አዘዛቸው። ካህኑ “በይሖዋ ቤት ውስጥ እንዳትገድሏት” ብሎ ነበር። 16 በመሆኑም ያዟት፤ ፈረሶች ወደ ንጉሡ ቤት*+ የሚገቡበት ቦታ ላይ ስትደርስ ተገደለች።
17 ከዚያም ዮዳሄ የይሖዋ ሕዝብ ሆነው እንዲቀጥሉ ይሖዋ፣ ንጉሡና ሕዝቡ ቃል ኪዳን እንዲጋቡ አደረገ፤+ በተጨማሪም ንጉሡና ሕዝቡ ቃል ኪዳን እንዲጋቡ አደረገ።+ 18 ከዚህም በኋላ የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ወደ ባአል ቤት* መጥቶ መሠዊያዎቹን አፈራረሰ፤+ ምስሎቹንም እንክትክት አድርጎ ሰባበረ፤+ የባአል ካህን የነበረውን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ገደሉት።+
ከዚያም ካህኑ በይሖዋ ቤት ላይ የበላይ ተመልካቾችን ሾመ።+ 19 በተጨማሪም ንጉሡን አጅበው ከይሖዋ ቤት ወደ ታች እንዲያመጡት መቶ አለቆቹን፣+ ካራውያን ጠባቂዎቹን፣ የቤተ መንግሥት ዘቦቹንና+ የምድሪቱን ሕዝብ ሁሉ ሰበሰበ፤ እነሱም ወደ ቤተ መንግሥቱ ዘቦች በር በሚወስደው መንገድ በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጡ።* እሱም በነገሥታቱ ዙፋን ላይ ተቀመጠ።+ 20 በመሆኑም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ እጅግ ተደሰተ፤ ጎቶልያንም በንጉሡ ቤት በሰይፍ ስለገደሏት ከተማዋ ጸጥታ ሰፈነባት።