9 እውነተኛ ጥበብ ቤቷን ሠራች፤
ሰባቱን ምሰሶዎቿንም ጠርባ አዘጋጀች።
2 ሥጋዋን በሚገባ አዘጋጀች፤
የወይን ጠጇንም ደባለቀች፤
ደግሞም ገበታዋን አሰናዳች።
3 ከከተማዋ በላይ ባሉ ከፍታ ቦታዎች ላይ ሆነው
እንዲህ ብለው እንዲጣሩ ሴት አገልጋዮቿን ላከች፦+
4 “ተሞክሮ የሌለው ሁሉ ወደዚህ ይምጣ።”
ማስተዋል ለጎደለው እንዲህ ትላለች፦
5 “ኑ፣ ያዘጋጀሁትን ምግብ ብሉ፤
የደባለቅኩትንም የወይን ጠጅ ጠጡ።
6 አላዋቂነታችሁን ተዉ፤ በሕይወትም ኑሩ፤+
በማስተዋል መንገድ ወደ ፊት ሂዱ።”+
7 ፌዘኛን የሚያርም በራሱ ላይ ውርደት ያመጣል፤+
ክፉን ሰው የሚወቅስም ሁሉ ጉዳት ይደርስበታል።
8 ፌዘኛን አትውቀስ፤ አለዚያ ይጠላሃል።+
ጥበበኛን ሰው ውቀሰው፤ እሱም ይወድሃል።+
9 ጥበበኛን ሰው አስተምረው፤ ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል።+
ጻድቅን ሰው አስተምረው፤ ተጨማሪ እውቀት ያገኛል።
10 የጥበብ መጀመሪያ ይሖዋን መፍራት ነው፤+
እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ ማወቅም+ ማስተዋል ነው።
11 በእኔ ምክንያት ዘመንህ ይረዝማል፤+
በሕይወትህም ላይ ዕድሜ ይጨመርልሃል።
12 ጥበበኛ ብትሆን፣ ጥበበኛነትህ የሚጠቅመው ራስህን ነው፤
ፌዘኛ ብትሆን ግን መዘዙን የምትቀበለው አንተው ነህ።
13 ማስተዋል የጎደላት ሴት ጯኺ ናት።+
እሷ ጨርሶ ማመዛዘን አትችልም፤ ደግሞም አንዳች ነገር አታውቅም።
14 በከተማዋ ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ፣
በቤቷ ደጃፍ ወንበር ላይ ትቀመጣለች፤+
15 በጎዳናው የሚያልፉትን፣
ቀጥ ብለው በመንገዳቸው የሚሄዱትን ትጣራለች፦
16 “ተሞክሮ የሌለው ሁሉ ወደዚህ ይምጣ።”
ማስተዋል ለጎደላቸው ሁሉ እንዲህ ትላለች፦+
17 “የተሰረቀ ውኃ ይጣፍጣል፤
ተደብቀው የበሉት ምግብም ይጥማል።”+
18 እሱ ግን በሞት የተረቱት በዚያ እንዳሉ፣
እንግዶቿም በመቃብር ጥልቅ ውስጥ እንደሚገኙ አያውቅም።+