135 ያህን አወድሱ!
የይሖዋን ስም አወድሱ፤
እናንተ የይሖዋ አገልጋዮች፣ ውዳሴ አቅርቡ፤+
2 በይሖዋ ቤት፣
በአምላካችን ቤት ቅጥር ግቢዎች የቆማችሁ ሁሉ አወድሱት።+
3 ይሖዋ ጥሩ ነውና፣+ ያህን አወድሱ።
ደስ የሚያሰኝ ነውና፣ ለስሙ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ።
4 ያህ ያዕቆብን የራሱ፣
እስራኤልን ልዩ ንብረቱ አድርጎ መርጧልና።+
5 ይሖዋ ታላቅ መሆኑን በሚገባ አውቃለሁና፤
ጌታችን ከሌሎች አማልክት ሁሉ የላቀ ነው።+
6 በሰማይና በምድር፣ በባሕሮችና በጥልቆች ውስጥ
ይሖዋ ደስ ያሰኘውን ነገር ሁሉ ያደርጋል።+
7 ደመና ከምድር ዳርቻዎች ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርጋል፤
በዝናብ ጊዜ መብረቅን ያበርቃል፤
ነፋሱን ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።+
8 በግብፅ የተወለደውን
የሰውም ሆነ የእንስሳ በኩር ገደለ።+
9 ግብፅ ሆይ፣ በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ሁሉ ላይ፣+
በመካከልሽ ምልክቶችንና ተአምራትን አደረገ።+
10 ብዙ ብሔራትን መታ፤+
ኃያላን ነገሥታትንም ገደለ፤+
11 የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንን፣+
የባሳንን ንጉሥ ኦግን፣+
የከነአንንም መንግሥታት ሁሉ ድል አደረገ።
12 ምድራቸውን ርስት አድርጎ፣
አዎ፣ ርስት አድርጎ ለሕዝቡ ለእስራኤል ሰጠ።+
13 ይሖዋ ሆይ፣ ስምህ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
ይሖዋ ሆይ፣ ዝናህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዘልቃል።+
14 ይሖዋ ለሕዝቡ ይሟገታልና፤+
ለአገልጋዮቹም ይራራል።+
15 የብሔራት ጣዖቶች ከብርና ከወርቅ የተሠሩ፣
የሰው እጅ ሥራ ናቸው።+
16 አፍ አላቸው፤ መናገር ግን አይችሉም፤+
ዓይን አላቸው፤ ማየት ግን አይችሉም፤
17 ጆሮ አላቸው፤ መስማት ግን አይችሉም።
በአፋቸው ውስጥ እስትንፋስ የለም።+
18 የሚሠሯቸውም ሆኑ የሚታመኑባቸው ሁሉ፣+
እንደ እነሱ ይሆናሉ።+
19 የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ይሖዋን አወድሱ።
የአሮን ቤት ሆይ፣ ይሖዋን አወድሱ።
20 የሌዊ ቤት ሆይ፣ ይሖዋን አወድሱ።+
እናንተ ይሖዋን የምትፈሩ፣ ይሖዋን አወድሱ።
21 በኢየሩሳሌም የሚኖረው ይሖዋ፣+
ከጽዮን ይወደስ።+
ያህን አወድሱ!+