አስቴር
2 ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሐሽዌሮስ+ ቁጣው ሲበርድለት አስጢን ያደረገችውን ነገርና+ በእሷ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ+ አስታወሰ። 2 ከዚያም የንጉሡ የቅርብ አገልጋዮች እንዲህ አሉ፦ “ለንጉሡ ቆንጆ የሆኑ ወጣት ደናግል ይፈለጉለት። 3 ንጉሡም ቆንጆ የሆኑትን ወጣት ደናግል ሁሉ ሰብስበው በሹሻን* ግንብ* ወደሚገኘው፣ ሴቶች ወደሚኖሩበት ቤት* እንዲያመጧቸው በግዛቱ ውስጥ በሚገኙት አውራጃዎች ሁሉ+ ሰዎችን ይሹም። እነሱም የንጉሡ ጃንደረባና የሴቶቹ ጠባቂ በሆነው በሄጌ+ ኃላፊነት ሥር ይሁኑ፤ የውበት እንክብካቤም ይደረግላቸው።* 4 ንጉሡ እጅግ ደስ የተሰኘባት ወጣትም በአስጢን ምትክ ንግሥት ትሆናለች።”+ ንጉሡም በሐሳቡ ደስ ተሰኘ፤ እንደተባለውም አደረገ።
5 በዚህ ጊዜ መርዶክዮስ+ የተባለ አንድ አይሁዳዊ በሹሻን*+ ግንብ* ይኖር ነበር፤ እሱም የቢንያማዊው+ የቂስ ልጅ፣ የሺምአይ ልጅ የሆነው የያኢር ልጅ ነው፤ 6 ይህ ሰው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር በግዞት ከወሰደው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን*+ ጋር ከኢየሩሳሌም በግዞት ከተወሰዱት ሰዎች አንዱ ነበር። 7 እሱም የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነችው የሃዳሳ* ማለትም የአስቴር አሳዳጊ* ነበር፤+ አስቴር አባትም ሆነ እናት አልነበራትም። ወጣቷ ቁመናዋ ያማረ፣ መልኳም ቆንጆ ነበር፤ መርዶክዮስም አባትና እናቷ ሲሞቱ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰዳት። 8 የንጉሡ ቃልና ያወጣው ሕግ ታውጆ በርካታ ወጣት ሴቶች በሄጌ+ ኃላፊነት ሥር እንዲሆኑ በሹሻን* ግንብ* ሲሰበሰቡ አስቴርም ወደ ንጉሡ ቤት* ተወስዳ የሴቶች ጠባቂ በሆነው በሄጌ ኃላፊነት ሥር እንድትሆን ተደረገ።
9 እሱም በወጣቷ ደስ ተሰኘባት፤ እንዲሁም በእሱ ዘንድ ሞገስ አገኘች፤* በመሆኑም የውበት እንክብካቤ እንዲደረግላትና*+ የተለየ ምግብ እንዲሰጣት ወዲያውኑ ዝግጅት አደረገ፤ ከንጉሡም ቤት የተመረጡ ሰባት ወጣት ሴቶች መደበላት። በተጨማሪም እሷንና የተመደቡላትን ሴቶች በሴቶቹ ቤት* ውስጥ ወደሚገኘው ምርጥ ወደሆነው ቦታ አዛወራቸው። 10 መርዶክዮስ+ ለማንም እንዳትናገር አዟት ስለነበር+ አስቴር ስለ ሕዝቦቿም+ ሆነ ስለ ዘመዶቿ ምንም አልተናገረችም። 11 መርዶክዮስ ስለ አስቴር ደህንነትና ስላለችበት ሁኔታ ለማወቅ በሴቶቹ ቤት* ግቢ ፊት ለፊት በየዕለቱ ይመላለስ ነበር።
12 እያንዳንዷ ወጣት ለሴቶቹ በታዘዘው መሠረት 12 ወር የሚፈጅ እንክብካቤ ከተደረገላት በኋላ ተራዋ ደርሶ ወደ ንጉሥ አሐሽዌሮስ ትገባ ነበር፤ የውበት እንክብካቤው* በተሟላ ሁኔታ የሚከናወንላቸው በዚህ መንገድ ነበርና፤ ስድስት ወር በከርቤ+ ዘይት፣ ስድስት ወር ደግሞ በበለሳን ዘይት+ እንዲሁም በተለያዩ ቅባቶች የውበት እንክብካቤ ይደረግላቸው ነበር።* 13 ከዚያም ወጣቷ ወደ ንጉሡ ለመግባት ዝግጁ ትሆናለች፤ ከሴቶቹ ቤት* ወደ ንጉሡ ቤት በምትሄድበት ጊዜም የምትጠይቀው ነገር ሁሉ ይሰጣት ነበር። 14 ምሽት ላይ ትገባለች፤ ጠዋት ላይ ደግሞ የቁባቶች ጠባቂ በሆነው በንጉሡ ጃንደረባ+ በሻአሽጋዝ ኃላፊነት ሥር ወዳለው ወደ ሁለተኛው የሴቶች ቤት* ትመለሳለች። ንጉሡ በጣም ካልተደሰተባትና በስም ጠቅሶ ካላስጠራት በስተቀር ዳግመኛ ወደ ንጉሡ አትገባም።+
15 መርዶክዮስ እንደ ልጁ አድርጎ የወሰዳት+ የአጎቱ የአቢሃይል ልጅ አስቴር ወደ ንጉሡ የምትገባበት ተራ ሲደርስ የሴቶች ጠባቂ የሆነው የንጉሡ ጃንደረባ ሄጌ እንድትጠይቅ ከነገራት ነገር በስተቀር ምንም አልጠየቀችም። (በዚህ ሁሉ ጊዜ አስቴር ባዩአት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አግኝታ ነበር።) 16 አስቴር ንጉሥ አሐሽዌሮስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት+ ቴቤት* ተብሎ በሚጠራው አሥረኛ ወር ወደ ንጉሡ ቤት ተወሰደች። 17 ንጉሡም ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይበልጥ አስቴርን ወደዳት፤ ከሌሎቹም ደናግል ሁሉ ይበልጥ በእሱ ዘንድ ሞገስና ተቀባይነት አገኘች።* በመሆኑም በራሷ ላይ የንግሥትነት አክሊል* አደረገላት፤ በአስጢንም+ ፋንታ ንግሥት አደረጋት።+ 18 ንጉሡም ለመኳንንቱ ሁሉና ለአገልጋዮቹ በሙሉ እጅግ ታላቅ ግብዣ አዘጋጀ፤ ይህን ታላቅ ግብዣ ያዘጋጀው ለአስቴር ክብር ሲል ነው። ከዚያም በአውራጃዎቹ ውስጥ ለሚኖሩ ምሕረት አደረገ፤ ንጉሡም ካለው ብልጽግና የተነሳ ስጦታዎችን ይሰጥ ነበር።
19 ደናግሉ*+ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሰበሰቡ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ነበር። 20 መርዶክዮስ ባዘዛት መሠረት አስቴር ስለ ዘመዶቿም ሆነ ስለ ሕዝቦቿ ምንም አልተናገረችም፤+ አስቴር ከመርዶክዮስ ጋር በነበረችበት ጊዜ ታደርግ እንደነበረው ሁሉ አሁንም እሱ የሚለውን ትታዘዝ ነበር።+
21 በዚያን ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ሳለ በር ጠባቂዎች የሆኑት ቢግታን እና ቴሬሽ የተባሉ የንጉሡ ሁለት የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ተቆጡ፤ ንጉሥ አሐሽዌሮስንም ለመግደል* አሴሩ። 22 ሆኖም መርዶክዮስ ይህን ጉዳይ አወቀ፤ ወዲያውኑም ለንግሥት አስቴር ነገራት። ከዚያም አስቴር ጉዳዩን በመርዶክዮስ ስም* ለንጉሡ ነገረችው። 23 በመሆኑም ሁኔታው ሲጣራ እውነት ሆኖ ተገኘ፤ ከዚያም ሁለቱ ሰዎች እንጨት ላይ ተሰቀሉ፤ ይህ ሁኔታም በዘመኑ በነበረው የታሪክ መጽሐፍ ላይ በንጉሡ ፊት ተጻፈ።+