“በእምነታቸው ምክንያት ታሰሩ”
ፖላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
አርቢት ማክት ፍሪ (ሥራ አርነት ያወጣል) የሚሉት ቃላት ከቼክ ጠረፍ 60 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በደቡብ ፖላንድ በሚገኘው የኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ የብረት በሮች ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ተጽፈው ይገኛሉ።a ይሁንና እነዚህ ቃላት ከ1940 እስከ 1945 ባሉት ዓመታት ውስጥ የብረት በሮቹን አልፈው በገቡት በአብዛኞቹ እስረኞች ላይ ከደረሰው ሁኔታ ጋር ይቃረናሉ። በእነዚያ ዓመታት ውስጥ በኦሽዊትዝ የነበሩ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በናዚዎች ተገድለዋል። ሆኖም በእስር ቤት ውስጥ ከነበሩት መካከል የአንድ ቡድን አባላት በማንኛውም ጊዜ ነፃነታቸውን ማግኘት ይችሉ ነበር።
እነዚህ ሰዎች ለነፃነታቸው የሚከፍሉት ዋጋ ምን ነበር? የይሖዋ ምሥክር የነበረ ማንኛውም እስረኛ ‘ከአሁን በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆኜ አላገለግልም’ በሚል ሰነድ ላይ እስከፈረመ ድረስ በነፃ ይለቀቃል። አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ውሳኔያቸው ምን ነበር? ኢሽትቫን ዲክ የተባሉ ታሪክ ጸሐፊ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች “የሮማ ንጉሠ ነገሥት ባቆመው መሠዊያ ላይ አነስተኛ መሥዋዕት ከሚያቀርቡ ይልቅ በአንበሶች ቢበሉ ይመርጡ ከነበሩት የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ጋር ይመሳሰላሉ” ብለዋል። እንዲህ ዓይነቱ አቋም ሊታወስ የሚገባው መሆኑ ምንም አያጠራጥርም፤ እንዲታሰብም እየተደረገ ነው።
ከመስከረም 21, 2004 ጀምሮ በኦሽዊትዝ ቢርከናው ብሔራዊ ሙዚየም ዋና አዳራሽ ውስጥ ለይሖዋ ምሥክሮቹ መታሰቢያ እንዲሆን ለሁለት ወራት የቆየ ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቶ ነበር። ኤግዚቢሽኑ “በእምነታቸው ምክንያት ታሰሩ—የይሖዋ ምሥክሮችና የናዚ አገዛዝ” የሚል ተስማሚ ጭብጥ ነበረው። በአዳራሹ ውስጥ የተቀመጡት 27 ሰሌዳዎች የይሖዋ ምሥክሮቹ በናዚ አገዛዝ ወቅት ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን ለመጠበቅ ያደረጉትን ቁርጥ አቋም ያሳያሉ።
ብዙ ጎብኚዎች ዴሊያና ሬድማክርስ የተባለች ሆላንዳዊት እህት ከእስር ቤት በላከችው ደብዳቤ ልባቸው ተነክቷል። ለቤተሰቦቿ የጻፈችው ደብዳቤ እንዲህ ይላል:- “የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ቃል ገብቻለሁ። . . . ቆራጥ እንዲሁም ደፋሮች ሁኑ። ይሖዋ ከእኛ ጋር ነው።” ዴሊያና በ1942 ወደ ኦሽዊትዝ ከተወሰደች በኋላ ሦስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተገድላለች።
ኦሽዊትዝ ውስጥ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በጠቅላላው ወደ 400 ይጠጋል። በሕይወት ከተረፉት መካከል ሦስቱ በኤግዚቢሽኑ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ያሳለፉትን ተሞክሮ የተናገሩ ሲሆን ጋዜጠኞች ላቀረቡላቸው ጥያቄዎችም መልስ ሰጥተዋል። ካምፕ ውስጥ እያሉ የደረሰባቸውን ሁኔታ እንዲቋቋሙ ያስቻላቸው ጥንካሬ በዚህ ወቅትም ፊታቸው ላይ ይነበባል።
የመንግሥት ሙዚየም ባልደረባና ተመራማሪ የሆኑት ቴሬዛ ቮንተር ሲሂ ኢምፕሪዝንድ ፎር ዜር ፌዝ—ጂሆቫስ ዊትነስስ ኢን ኦሽዊትዝ ኮንሰንትሬሽን ካምፕ (በእምነታቸው ምክንያት ታሰሩ—የይሖዋ ምሥክሮች በኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ) በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ይህ አነስተኛ ቡድን ያሳየው አቋም በሌሎች እስረኞች ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ሌሎቹ [እስረኞች፣ የይሖዋ ምሥክሮቹ] በየዕለቱ የሚደርስባቸውን ፈተና ተቋቁመው ለመጽናት ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ መመልከታቸው ሰዎች በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ሥር ለእምነታቸው ታማኝ ሆነው መቀጠል እንደሚችሉ እምነት እንዲያድርባቸው አድርጓቸዋል።”
ለነገሩ ለክርስቶስ ተከታዮች መታሰርም ሆነ መሞት አዲስ ነገር አይደለም። ምክንያቱም ኢየሱስ ራሱ ለእምነቱ ሲል ታስሯል እንዲሁም ተገድሏል። (ሉቃስ 22:54፤ 23:32, 33) የኢየሱስ ሐዋርያ የሆነው ያዕቆብም ተገድሏል። ሐዋርያው ጴጥሮስ በእስር ሲንገላታ ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ብዙ ጊዜ ተደብድቧል እንዲሁም ታስሯል።—የሐዋርያት ሥራ 12:2, 5፤ 16:22-25፤ 2 ቆሮንቶስ 11:23
በተመሳሳይም በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት በአውሮፓ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ላይ እምነት በማሳደር ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። እነዚህ ሰዎች ያሳዩት እምነት በኦሽዊትዝ እንዲታሰብ መደረጉ ተገቢ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኦሽዊትዝ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን ያቀፈ ነበር። እነዚህም ኦሽዊትዝ I (ዋናው ካምፕ)፣ ኦሽዊትዝ II (ቢርከናው) እና ኦሽዊትዝ III (ሞኖቪትስ) ይባላሉ። በአሰቃቂነቱ የሚታወቀው ቢርከናው ነው።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከኦሽዊትዝ የተረፉ ሦስት ወንድሞች የኤግዚቢሽኑ ጭብጥ የተጻፈበትን ሰሌዳ ይዘው
[በገጽ 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዴሊያና ሬድማክርስና እስር ቤት ሆና የጻፈችው ደብዳቤ
[ምንጭ]
ትንንሾቹ ፎቶግራፎች:- Zdjęcie: Archiwum Państwowego Muzeum Auschwitz-Birkenau
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ማማ:- Dzięki uprzejmości Państwowego Muzeum Auschwitz-Birkenau