“ከአንተ የሚያጽናና ቃል እፈልጋለሁ”
● በሜክሲኮ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ፣ የአካል ጉዳተኛና የአእምሮ ሕሙማን ለሆኑ ልጆች ልዩ ትኩረት በሚሰጥ አንድ ትምህርት ቤት ከምትሠራ አንዲት ሴት ደብዳቤ ደረሰው። ደብዳቤው እንዲህ ይላል፦ “ውዷ እናቴ ግንቦት 9 ቀን በሞት ተለየችኝ። የተሰማኝን ሐዘን በቃላት መግለጽ ያስቸግረኛል። ከመሞቷ ከጥቂት ወራት በፊት ከሥራዬ ጋር በተያያዘ ስለ ሞትና ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ አንድ ጥናት አድርጌ ነበር። ያደረግኩት ምርምር እኔንም የሚረዳኝ መስሎኝ ነበር፤ ግን ሊረዳኝ አልቻለም።”
ይህች ሴት አንድ ቀን ሐዘኑ ሲብስባት “ከአንተ የሚያጽናና ቃል እፈልጋለሁ” በማለት ወደ አምላክ ጸለየች። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ያን ዕለት ማታ የምትወዱት ሰው ሲሞት የተሰኘውን ብሮሹር አነበብኩ። ልክ ለእኔ ተብሎ የተጻፈ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። ብሮሹሩ፣ ማልቀስ ምንም ስህተት እንደሌለው ይናገራል። ‘ከሐዘኔ ልጽናና የምችለው እንዴት ነው?’ በሚለው ምዕራፍ ላይ የሚከተለው ሐሳብ ይገኛል፦ ‘ጸሎት ያለውን ጥቅም አቅልላችሁ አትመልከቱ። . . . አምላክ የሚሰጠው እርዳታ በስሜታችሁ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። . . . መለኮታዊው እርዳታ በሐዘናችሁ ምክንያት የሚሰማችሁን ሥቃይ ባያስወግድላችሁም ለመሸከም የማትችሉት ሐዘን እንዳይሆንባችሁ ይረዳችኋል። ይህ ሲባል ግን ማልቀሳችሁን ታቆማላችሁ ወይም የምትወዱትን ሰው ፈጽሞ ትረሱታላችሁ ማለት አይደለም፤ ሆኖም ከሐዘናችሁ ልትጽናኑ ትችላላችሁ።’ ይህ ሐሳብ ከሐዘኔ እንድጽናና ረድቶኛል።”
የምትወዱትን ሰው በሞት አጥታችሁ ከሆነና የሚያጽናና ቃል እንደሚያስፈልጋችሁ ከተሰማችሁ እናንተ ራሳችሁ አሊያም አንድ ሌላ የምታውቁት ሰው የምትወዱት ሰው ሲሞት የተሰኘውን ባለ 32 ገጽ ብሮሹር በማንበብ ማጽናኛ ማግኘት ትችሉ ይሆናል።
ይህን ብሮሹር ማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ ከታች ያለውን ቅጽ ሞልተው በቅጹ ላይ ወዳለው አድራሻ ወይም በዚህ መጽሔት በገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መላክ ይችላሉ።
□ እዚህ ላይ የሚታየውን ብሮሹር ላኩልኝ።
□ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስለምፈልግ እባካችሁ አነጋግሩኝ።