ምዕራፍ 94
የጸሎትና የትሕትና አስፈላጊነት
ቀደም ሲል ኢየሱስ በይሁዳ በነበረበት ጊዜ በጸሎት የመጽናትን አስፈላጊነት በተመለከተ አንድ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። አሁን ወደ ኢየሩሳሌም ባደረገው የመጨረሻ ጉዞ ላይ ደግሞ ሳይታክቱ የመጸለይን አስፈላጊነት እንደገና ጎላ አድርጎ ገለጸ። ኢየሱስ ይህን ተጨማሪ ምሳሌ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው በሰማርያ አለዚያም በገሊላ ሳለ ሳይሆን አይቀርም:-
“በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ። በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፣ ወደ እርሱም እየመጣች:- ከባላጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር። አያሌ ቀንም አልወደደም፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ:- ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፣ ይህች መበለት ስለምታደክመኝ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ አለ።”
ከዚያም ኢየሱስ ታሪኩ ያዘለውን ቁም ነገር እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ዓመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?”
ኢየሱስ ይህን የተናገረው ዓመፀኛውን ዳኛ በምንም መንገድ ከይሖዋ አምላክ ጋር ለማመሳሰል ፈልጎ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ዓመፀኛ ዳኛ እንኳ ያለ ማቋረጥ ለሚቀርብለት ልመና ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ ፍጹም ጻድቅና ጥሩ የሆነው አምላክ ሕዝቦቹ ያለመታከት ወደርሱ ከጸለዩ መልስ እንደሚሰጣቸው ምንም አያጠያይቅም። ስለዚህ ኢየሱስ በመቀጠል “እላችኋለሁ፣ [አምላክ] ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል” ብሏል።
ብዙውን ጊዜ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችና ድሆች ፍትህ አያገኙም፤ ታላላቅና ሀብታም ለሆኑ ሰዎች ግን አብዛኛውን ጊዜ አድልዎ ይደረጋል። ይሁን እንጂ አምላክ ክፉዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ብቻ ሳይሆን አገልጋዮቹም የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ በማድረግ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲያዙ ያደርጋል። ሆኖም አምላክ ፈጥኖ የፍትሕ እርምጃ እንደሚወስድ ጽኑ እምነት ያላቸው ሰዎች ምን ያህል ናቸው?
ኢየሱስ በተለይ ከጸሎት ኃይል ጋር ዝምድና ያለውን እምነት በመጥቀስ “የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆንን?” ሲል ጠይቋል። ምንም እንኳ ጥያቄው መልስ ሳይሰጥበት በእንጥልጥል የተተወ ቢሆንም አንድምታው ክርስቶስ በመንግሥቱ ሥልጣን በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት እምነት በብዛት እንደማይገኝ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ኢየሱስን እያዳመጡ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እምነት አለን በማለት የሚመኩ ነበሩ። ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው በመቁጠር በራሳቸው ይተማመኑ ነበር፤ ሌሎችን ደግሞ ዝቅ አድርገው ይመለከቱ ነበር። ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከልም አንዳንዶቹ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ኢየሱስ ለእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች የሚከተለውን ምሳሌ ተናገረ:-
“ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፣ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ። ፈሪሳዊው ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ:- እግዚአብሔር ሆይ፣ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፣ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፣ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፣ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ።”
ፈሪሳውያን በሌሎች ለመደነቅ በአደባባይ በሚያሳዩት የጽድቅ ትዕይንት የታወቁ ናቸው። ራሳቸው ያወጡትን የጾም ሥርዓት ያከናውኑ የነበረው ሰኞና ሐሙስ ነበር። ለቅመምነት ከሚያገለግሉ ትንንሽ ተክሎች እንኳ ሳይቀር ምንም ሳያጓድሉ አሥራት ይከፍሉ ነበር። ከጥቂት ወራት በፊት የዳስ በዓል ይከበር በነበረበት ወቅት “ሕግን [ፈሪሳውያን ለሕጉ የሰጡትን ፍቺ ማለት ነው] የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው” በማለት ለተራው ሕዝብ ያላቸውን ንቀት ገልጸዋል።
ኢየሱስ ምሳሌውን በመቀጠል “ርጉም” ብለው ከጠሯቸው ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ስለሆነ ሰው እንዲህ አለ:- “ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፣ ነገር ግን:- አምላክ ሆይ፣ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።” ቀራጩ የፈጸማቸውን ስህተቶች በትሕትና አምኖ በመቀበሉ ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “እላችኋለሁ፣ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፣ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።”
በዚህ መንገድ ኢየሱስ ትሑት የመሆንን አስፈላጊነት በድጋሚ ጎላ አድርጎ ገልጿል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ ራሳቸውን የሚያመጻድቁት ፈሪሳውያን ከፍተኛ ተጽዕኖ በሚያሳድሩበትና ሥልጣንና ማዕረግ ዘወትር ከፍ ተደርገው በሚታዩበት ኅብረተሰብ ውስጥ ያደጉ በመሆኑ ይህ መንፈስ በእነሱም ላይ ማደሩ ምንም አያስደንቅም። ሆኖም ኢየሱስ ስለ ትሕትና ግሩም ትምህርት ሰጥቷል! ሉቃስ 18:1-14፤ ዮሐንስ 7:49
▪ ዓመፀኛው ዳኛ የመበለቷን ልመና ሰምቶ የፈረደላት ለምንድን ነው? ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ የሚያስተላልፈው ትምህርትስ ምንድን ነው?
▪ ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ ምን ዓይነት እምነት መኖሩን ለማረጋገጥ ይመረምራል?
▪ ኢየሱስ ስለ ፈሪሳዊውና ስለ ቀራጩ የሚገልጸውን ምሳሌ የተናገረው ለእነማን ነው?
▪ ሊወገድ የሚገባው የፈሪሳውያን አመለካከት የትኛው ነው?