ምዕራፍ 15
የእኩዮቼን ተጽዕኖ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
“በትምህርት ቤት የሚያጋጥመን ተጽዕኖ በጣም ብዙ ነው፤ ሲጋራ እንድናጨስ፣ ዕፅ እንድንወስድና የፆታ ግንኙነት እንድንፈጽም ግፊት ይደረግብናል። ልጆቹ እንድናደርግ የሚፈልጉት ነገር መጥፎ እንደሆነ እናውቃለን። የሆነ ደረጃ ላይ ስንደርስ ግን ተጽዕኖውን መቋቋም ይከብደናል።”—ኢቭ
በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መፈለግ ያለ ነገር ነው። የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገውም ይህ ፍላጎታችን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆችህ ክርስቲያኖች ከሆኑ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት እንደ መፈጸምና ከመጠን በላይ እንደ መጠጣት ያሉት ነገሮች ስህተት እንደሆኑ ታውቃለህ። (ገላትያ 5:19-21) ይሁንና ከእኩዮችህ መካከል አብዛኞቹ እነዚህን ድርጊቶች እንድትፈጽም ይገፋፉሃል። እነዚህ ወጣቶች እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙት በጉዳዩ ላይ አስበውበት የራሳቸውን ምርጫ ስላደረጉ ነው? በአብዛኛው ይህን የሚያደርጉት በሌሎች ተጽዕኖ ተሸንፈው ነው። በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስለሚፈልጉ አመለካከታቸውን እኩዮቻቸው እንዲቀርጹት ይፈቅዳሉ። አንተስ እንዲህ ታደርጋለህ? ወይስ ለምታምንበት ነገር በድፍረት አቋም ትወስዳለህ?
የሙሴ ወንድም የሆነው አሮን ቢያንስ በአንድ አጋጣሚ ለሌሎች ተጽዕኖ ተሸንፎ ነበር። እስራኤላውያን ወደ እሱ መጥተው ጣዖት እንዲሠራላቸው ሲወተውቱት ልክ እንዳሉት አድርጎላቸዋል! (ዘፀአት 32:1-4) እስቲ አስበው፣ ይህ ሰው በአንድ ወቅት የአምላክን መልእክት ለፈርዖን በድፍረት ተናግሮ ነበር። (ዘፀአት 7:1, 2, 16) ሆኖም ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያን ጠንከር ያለ ግፊት ሲያደርጉበት አሮን በተጽዕኖው ተሸነፈ። ከሁኔታው መመልከት እንደሚቻለው የወገኖቹን ተጽዕኖ መቋቋም የግብፁን ንጉሥ ፈርዖንን ከመጋፈጥ ይበልጥ ከብዶት ነበር!
አንተስ? ትክክል እንደሆነ ላመንክበት ነገር አቋም መውሰድ ይከብድሃል? ሳትጨነቅና ሳትፈራ የእኩዮችህን ተጽዕኖ መቋቋም ትፈልጋለህ? በእርግጥ መቋቋም ትችላለህ! ቁልፉ የሚያጋጥምህን ተጽዕኖ አስቀድመህ ማስተዋልና የምትሰጠውን መልስ ማዘጋጀት ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት አራት ነጥቦች ይህን ለማድረግ ይረዱሃል።
1. አስቀድመህ አስብ። (ምሳሌ 22:3) አብዛኛውን ጊዜ ሊገጥምህ የሚችለውን ችግር አስቀድመህ መገመት ትችላለህ። ለምሳሌ፣ አብረውህ የሚማሩ ልጆች ወደ አንተ አቅጣጫ እየመጡ ነው እንበል፤ ሲጋራ እያጨሱ እንደሆነ ይታይሃል። እንድታጨስ የሚጋብዙህ ይመስልሃል? ሊያጋጥምህ የሚችለውን ሁኔታ አስቀድመህ በማሰብ ከችግሩ ለመሸሽ ወይም ችግሩን ለመጋፈጥ ራስህን ልታዘጋጅ ትችላለህ።
2. አመዛዝን። (ዕብራውያን 5:14) ‘አብዛኛው ሰው የሚያደርገውን ነገር ብፈጽም ወደፊት ምን ሊሰማኝ ይችላል?’ በማለት ራስህን መጠየቅ ትችላለህ። እውነት ነው፣ ለጊዜው በእኩዮችህ ዘንድ ተቀባይነት ታገኝ ይሆናል። ይሁንና በኋላ ላይ ከወላጆችህ ወይም ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ስትሆን ምን የሚሰማህ ይመስልሃል? አብረውህ የሚማሩትን ልጆች ለማስደሰት ስትል በአምላክ ፊት ያለህን ንጹሕ አቋም ማጣት ትፈልጋለህ?
3. ወስን። (ዘዳግም 30:19) ይዋል ይደር እንጂ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ታማኝነታቸውን መጠበቅ የሚያስገኘውን በረከት ለማጨድ አሊያም ታማኝነታቸውን ማጉደል የሚያስከትለውን መራራ ጽዋ ለመጎንጨት መምረጥ ይኖርባቸዋል። እንደ ዮሴፍ፣ ኢዮብና ኢየሱስ ያሉት የአምላክ አገልጋዮች ትክክለኛ ምርጫ ያደረጉ ሲሆን እንደ ቃየን፣ ኤሳውና ይሁዳ ያሉት ደግሞ መጥፎ ምርጫ አድርገዋል። አንተም ውሳኔ ማድረግ ይኖርብሃል። ታዲያ ምርጫህ ምንድን ነው?
4. እርምጃ ውሰድ። ከሁሉ የሚከብደው ይህ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና እንደምታስበው ከባድ አይደለም! ለተጽዕኖው የምትሰጠው ምላሽ የሚያስከትለውን ውጤት አስቀድመህ ካመዛዘንክና ውሳኔ ካደረግህ፣ አቋምህን መግለጽ ከምታስበው በላይ ቀላል አልፎ ተርፎም የሚክስ ነው። (ምሳሌ 15:23) አቋምህን ትገልጻለህ ሲባል ግን ለእኩዮችህ መስበክ አለብህ ማለት አይደለም። በአጭሩ ሆኖም ጠንከር ባለ መንገድ እንቢታህን መግለጽ በቂ ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ አቋምህ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ግልጽ ለማድረግ እንዲህ ማለት ትችላለህ፦
“አይ፣ እኔን ይለፈኝ!”
“እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር አላደርግም!”
“አሁን እኔ እንደዚህ እንደማላደርግ ጠፍቶህ ነው?”
ዋናው ነገር፣ ሳታንገራግር በልበ ሙሉነት መልስ መስጠትህ ነው። እንዲህ ካደረግህ እኩዮችህ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ካሰብከው በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያቆማል! ይሁን እንጂ እኩዮችህ በአንተ ላይ ማሾፍ ቢጀምሩስ? “ምነው ፈራህ እንዴ?” ቢሉህስ? እንዲህ የሚያደርጉበት ዓላማ ሊገባህ ይገባል፤ ፍላጎታቸው በአንተ ላይ ጫና ማድረግ ነው። በዚህ ጊዜ ምን ምላሽ መስጠት ትችላለህ? ቢያንስ ሦስት አማራጮች አሉህ።
● የሚደረግብህን ጫና መቀበል ትችላለህ። (“አዎ፣ እፈራለሁ!” ካልክ በኋላ ምክንያትህን በአጭሩ ተናገር።)
● ክርክር ውስጥ መግባት ሳያስፈልግህ አቋምህን በመግለጽ የተጽዕኖውን አቅጣጫ ማስቀየስ ትችላለህ።
● ተጽዕኖውን ወደ እኩዮችህ ማዞር ትችላለህ። ድርጊቱን የማትፈጽምበትን ምክንያት ከገለጽክ በኋላ አእምሮውን የሚያሠራ ነገር ተናገር። (“አንተም ማጨስህ አስገርሞኛል! ብልጥ ትመስለኝ ነበር!”)
እኩዮችህ ማሾፋቸውን ከቀጠሉ ትተሃቸው ሂድ! አብረሃቸው በቆየህ መጠን ጫናውም እየበረታ ይመጣል። ትተሃቸው መሄድ ቢኖርብህም እንኳ ልትዘነጋው የማይገባ ነገር አለ፦ ሁኔታውን በሚገባ ተወጥተኸዋል። እኩዮችህ በራሳቸው መንገድ እንዲቀርጹህ አልፈቀድክም!
አንዳንድ እኩዮችህ የምትመራው በራስህ ጭንቅላት እንዳልሆነ በመግለጽ ያሾፉብህ ይሆናል። ሐቁ ግን እንደዚያ አይደለም! ይሖዋ፣ የእሱን ፈቃድ ማድረግ ከሁሉ የተሻለ አካሄድ መሆኑን ለራስህ እንድታረጋግጥ ይፈልጋል። (ሮም 12:2) ታዲያ እኩዮችህ እንደ አሻንጉሊት እንዲጫወቱብህ ለምን ትፈቅዳለህ? (ሮም 6:16) ትክክል እንደሆነ ላመንክበት ነገር አቋም ውሰድ!
ከእኩዮችህ ግፊት ማምለጥ እንደማትችል እሙን ነው። ሆኖም ፍላጎትህን ማወቅ፣ አቋምህን መግለጽና ሁኔታውን በሚገባ መወጣት ትችላለህ። ዞሮ ዞሮ ምርጫው የአንተ ነው!—ኢያሱ 24:15
ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 9 ተመልከት
ሁለት ዓይነት ሕይወት እየመራህ ነው? ወላጆችህ ይህን ማወቃቸው የሚያመጣው ጥቅም ይኖራል?
ቁልፍ ጥቅስ
“ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።”—ምሳሌ 13:20
ጠቃሚ ምክር
የበለጠ ድፍረት ማግኘት እንድትችል ትክክል ለሆነው ነገር አቋም የወሰዱ ዘመናዊ የይሖዋ አገልጋዮችን ተሞክሮዎች አንብብ።
ይህን ታውቅ ነበር?
ትምህርት ከጨረስክ ከአንድ ዓመት በኋላ አብረውህ ከተማሩት ልጆች መካከል ከአብዛኞቹ ጋር አትገናኝም። እንዲያውም ብዙዎቹ ስምህ እንኳ ትዝ ላይላቸው ይችላል። ቤተሰብህ ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ አምላክ ግን የአንተ ደህንነት ምንጊዜም ያሳስባቸዋል።—መዝሙር 37:23-25
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
የእኩዮቼን ተጽዕኖ ለመቋቋም ዝግጁ እንድሆን እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
እኩዮቼ መጥፎ ነገር እንድፈጽም ግፊት የሚያደርጉብኝ ከሆነ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● በዚህ ምዕራፍ ላይ የቀረቡትን አራት ነጥቦች ምን ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ ልትጠቀምባቸው ትችላለህ?
● ለእኩዮችህ ተጽዕኖ ብትሸነፍ ውጤቱ ምን ይሆናል?
● የእኩዮችህን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚረዱህ አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
[በገጽ 131 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አብዛኞቹ ወጣቶች የይሖዋ ምሥክር መሆኔን የሚያውቁ ሲሆን ለእኔ አክብሮት አላቸው። መጥፎ ነገር ሊያወሩ ሲፈልጉ ‘ማይክ፣ ያን ወሬ ልንጀምረው ስለሆነ ብትሄድ ሳይሻል አይቀርም’ ይሉኛል።”—ማይክ
[በገጽ 132 እና 133 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የመልመጃ ሣጥን
የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም
ናሙና
1 አስቀድመህ አስብ
ፈተናው ምንድን ነው? ሲጋራ ማጨስ።
እንዲህ ያለው ተጽዕኖ ሊያጋጥመኝ የሚችለው መቼ ነው? በእረፍት ሰዓት።
2 አመዛዝን
ለተጽዕኖው ብሸነፍ ውጤቱ ምን ይሆናል?
ይሖዋና ወላጆቼ ያዝኑብኛል። ሕሊናዬ ይቆሽሻል። ሌላ ጊዜ እንቢ ለማለት ይከብደኛል።
ተጽዕኖውን ብቋቋም ውጤቱ ምን ይሆናል?
ሊሾፍብኝ ወይም ቅጽል ስም ሊሰጠኝ ይችላል። አንዳንዶቹ ልጆች ሊያገሉኝ ይችላሉ። ሆኖም ይሖዋን ደስ አሰኘዋለሁ፤ እንዲሁም ይበልጥ ጠንካራ አቋም አዳብራለሁ።
3 ወስን
ተጽዕኖውን የምቋቋምበት ምክንያት
ማጨስ ይሖዋን እንደሚያሳዝንና ለጤናዬም ጎጂ እንደሆነ አውቃለሁ።
ለተጽዕኖው ከተሸነፍኩ ምክንያቱ
የእኩዮቼን ተጽዕኖ ለመቋቋም በቂ ዝግጅት አላደረግኩም። በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘት ይበልጥ የሚያሳስበኝ በእኩዮቼ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ነው።
4 እርምጃ ውሰድ
እንዲህ አደርጋለሁ፦
እንቢ ብዬ ትቻቸው እሄዳለሁ።
እኩዮችህ ሲያሾፉብህ
አንድ ልጅ እንዲህ ቢለኝ፦ “ለምን አታጨስም? ትፈራለህ እንዴ?”
ተጽዕኖውን ለመቋቋም እንዲህ ማድረግ እችላለሁ
ጫናውን መቀበል
“አዎ፣ ሲጋራ ማጨስ ያስፈራኛል። የሳንባ ካንሰር እንዲይዘኝ አልፈልግም።”
አቅጣጫውን ማስቀየስ
“ሲጋራህን ባታባክነው ጥሩ አይመስልህም?”
ወደ እኩዮቼ ማዞር
“አመሰግናለሁ አልፈልግም። አንተም ማጨስህ አስገርሞኛል! ብልጥ ትመስለኝ ነበር!”
ማስታወሻ፦ እኩዮችህ በአንተ ላይ ጫና ማድረጋቸውን ከቀጠሉ ቶሎ ትተሃቸው ሂድ። ብዙ ከቆየህ አሻንጉሊታቸው ያደርጉሃል። አሁን ደግሞ በሚቀጥለው ገጽ ላይ ያለውን ሣጥን አንተ ሙላው።
የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም
ፎቶ ኮፒ አድርገው!
1 አስቀድመህ አስብ
ፈተናው ምንድን ነው? ․․․․․
እንዲህ ያለው ተጽዕኖ ሊያጋጥመኝ የሚችለው መቼ ነው? ․․․․․
2 አመዛዝን
ለተጽዕኖው ብሸነፍ ውጤቱ ምን ይሆናል?
․․․․․
ተጽዕኖውን ብቋቋም ውጤቱ ምን ይሆናል?
․․․․․
3 ወስን
ተጽዕኖውን የምቋቋምበት ምክንያት . . .
․․․․․
ለተጽዕኖው ከተሸነፍኩ ምክንያቱ . . .
․․․․․
4 እርምጃ ውሰድ
․․․․․
እንዲህ አደርጋለሁ፦
․․․․․
እኩዮችህ ሲያሾፉብህ
አንድ ልጅ እንዲህ ቢለኝ፦ ․․․․․
ተጽዕኖውን ለመቋቋም እንዲህ ማድረግ እችላለሁ
ጫናውን መቀበል
․․․․․
አቅጣጫውን ማስቀየስ
․․․․․
ወደ እኩዮቼ ማዞር
․․․․․
የምትሰጠውን መልስ ከወላጆችህ ወይም ከአንድ የጎለመሰ ጓደኛህ ጋር ሆነህ ተለማመድ።
[በገጽ 135 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለእኩዮችህ ተጽዕኖ ከተሸነፍክ እንደ አሻንጉሊት ይጫወቱብሃል