ምዕራፍ 52
በጥቂት ዳቦና ዓሣ ሺዎችን መመገብ
ማቴዎስ 14:13-21 ማርቆስ 6:30-44 ሉቃስ 9:10-17 ዮሐንስ 6:1-13
ኢየሱስ 5,000 ወንዶችን መገበ
አሥራ ሁለቱ የኢየሱስ ሐዋርያት በመላዋ ገሊላ አስደናቂ የስብከት ዘመቻ አደረጉ፤ ከዚያም “ያደረጉትንና ያስተማሩትን ነገር ሁሉ ነገሩት።” አሁን ደክሟቸው እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ያም ቢሆን ብዙዎች ይመጡና ይሄዱ ስለነበር ምግብ ለመብላት እንኳ ፋታ አላገኙም። ስለዚህ ኢየሱስ “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ” አላቸው።—ማርቆስ 6:30, 31
ከቅፍርናሆም አቅራቢያ ሳይሆን አይቀርም ጀልባ ተሳፈሩና ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ፣ ከቤተሳይዳ ባሻገር ወደሚገኝ ገለልተኛ ቦታ ሄዱ። ይሁንና ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አዩአቸው፤ ሌሎችም መሄዳቸውን አወቁ። ከዚያም ሰዎቹ በባሕሩ ዳር ዳር እየሮጡ ወደዚያው ሄዱ፤ በመሆኑም ጀልባዋ ዳርቻው ላይ ስትደርስ ቀድመው ጠበቋቸው።
ኢየሱስ ከጀልባዋ ሲወርድ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተመለከተ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለሆኑም በጣም አዘነላቸው። በመሆኑም ስለ መንግሥቱ ‘ብዙ ነገር ያስተምራቸው ጀመር።’ (ማርቆስ 6:34) “ፈውስ የሚያስፈልጋቸውንም ፈወሳቸው።” (ሉቃስ 9:11) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ደቀ መዛሙርቱ “ቦታው ገለል ያለ ነው፤ ሰዓቱ ደግሞ ገፍቷል፤ ስለዚህ ሕዝቡ ወደ መንደሮቹ ሄደው ምግብ እንዲገዙ አሰናብታቸው” አሉት።—ማቴዎስ 14:15
ኢየሱስ ግን “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉት ነገር ስጧቸው” አለ። (ማቴዎስ 14:16) ኢየሱስ ሊያደርገው ያሰበውን ቢያውቅም ፊልጶስን ለመፈተን “እነዚህ ሰዎች የሚበሉት ዳቦ ከየት ብንገዛ ይሻላል?” አለው። ፊልጶስ የመጣው ከቤተሳይዳ አቅራቢያ በመሆኑ ጥያቄው ለእሱ መቅረቡ ተገቢ ነው። ያም ቢሆን ዳቦ መግዛት የሚያዋጣ ነገር አይደለም። በቦታው 5,000 ያህል ወንዶች አሉ። ሴቶችና ልጆች ሲደመሩ ደግሞ ቁጥሩ እጥፍ ሊሆን ይችላል! በመሆኑም ፊልጶስ “እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ እንዲደርሰው ለማድረግ እንኳ የ200 ዲናር [አንድ ዲናር የአንድ ቀን ደሞዝ ነው] ዳቦ አይበቃም” ሲል መለሰለት።—ዮሐንስ 6:5-7
እንድርያስም ቀበል አድርጎ “አምስት የገብስ ዳቦና ሁለት ትናንሽ ዓሣ የያዘ አንድ ትንሽ ልጅ እዚህ አለ። ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይበቃል?” አለ። እንዲህ ያለው ይህን ሁሉ ሰው መመገብ የማይቻል መሆኑን ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም።—ዮሐንስ 6:9
ጊዜው በ32 ዓ.ም. ከሚከበረው የፋሲካ በዓል ጥቂት ቀደም ብሎ ነው፤ የጸደይ ወቅት በመሆኑ ሜዳው በለምለም ሣር ተሸፍኗል። ኢየሱስ ሰዎቹን ሃምሳ ሃምሳና መቶ መቶ እያደረጉ ሣሩ ላይ በቡድን እንዲያስቀምጧቸው ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። አምስቱን ዳቦና ሁለቱን ዓሣ ይዞ አምላክን አመሰገነ። ቀጥሎም ዳቦውን ከቆረሰና ዓሣውን ከቆራረጠ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ለሕዝቡ እንዲያከፋፍሉ ሰጣቸው። የሚገርመው ነገር ሰዎቹ ሁሉ እስኪጠግቡ ድረስ በሉ!
ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ምንም እንዳይባክን የተረፈውን ቁርስራሽ ሁሉ ሰብስቡ” አላቸው። (ዮሐንስ 6:12) ደቀ መዛሙርቱ እንደተባሉት ሲያደርጉ የተረፈው ቁርስራሽ 12 ቅርጫት ሞላ!