ምዕራፍ 83
ግብዣ—አምላክ የሚጋብዘው እነማንን ነው?
ስለ ትሕትና የተሰጠ ትምህርት
የተጋበዙት እንግዶች ሰበብ አቀረቡ
ኢየሱስ፣ ሰውነት የሚያሳብጥ በሽታ ይዞት የነበረውን ሰው ከፈወሰ በኋላ አሁንም ፈሪሳዊው ቤት ነው። በግብዣው ላይ ሌሎቹ እንግዶች ለራሳቸው የክብር ቦታ ሲመርጡ ስለተመለከተ ይህን አጋጣሚ ስለ ትሕትና ትምህርት ለመስጠት ተጠቀመበት።
ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ወደ ሠርግ ሲጠራህ በክብር ቦታ አትቀመጥ። ምናልባት ከአንተ የበለጠ የተከበረ ሰው ተጠርቶ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ሁለታችሁንም የጋበዘው ሰው መጥቶ ‘ቦታውን ለዚህ ሰው ልቀቅለት’ ይልሃል። በዚህ ጊዜ እያፈርክ ወደ ዝቅተኛው ቦታ ትሄዳለህ።”—ሉቃስ 14:8, 9
ቀጥሎም እንዲህ አለ፦ “አንተ ግን ስትጋበዝ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ የጋበዘህም ሰው ሲመጣ ‘ወዳጄ ሆይ፣ ወደ ላይ ከፍ በል’ ይልሃል። በዚህ ጊዜ አብረውህ በተጋበዙት ሰዎች ሁሉ ፊት ክብር ታገኛለህ።” ይህን የምናደርገው መልካም ምግባር ለማሳየት ብለን ብቻ አይደለም። ኢየሱስ “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋልና፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል” በማለት አብራርቷል። (ሉቃስ 14:10, 11) አዎን፣ ኢየሱስ አድማጮቹ ትሕትናን እንዲያዳብሩ እያበረታታ ነው።
ከዚህ በመቀጠል ኢየሱስ በአምላክ ዘንድ እውነተኛ ዋጋ ያለው ግብዣ ማዘጋጀት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለጋበዘው ፈሪሳዊ ነገረው። “የምሳ ወይም የራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ጓደኞችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ሀብታም ጎረቤቶችህን አትጥራ። አለዚያ እነሱም ሊጋብዙህና ብድር ሊመልሱልህ ይችላሉ። ሆኖም ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ አንካሶችንና ዓይነ ስውራንን ጥራ፤ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ ደስተኛ ትሆናለህ።”—ሉቃስ 14:12-14
ጓደኞቻችንን፣ ዘመዶቻችንን ወይም ጎረቤቶቻችንን መጋበዝ የተለመደ ነገር ነው፤ ኢየሱስም ቢሆን ይህን ማድረግ ስህተት መሆኑን እየገለጸ አይደለም። ሆኖም የተቸገሩትን ይኸውም ድሆችን፣ ሽባዎችን ወይም ዓይነ ስውራንን ማብላት የላቀ በረከት እንደሚያስገኝ ማጉላቱ ነው። ኢየሱስ ይህን ያለበትን ምክንያት ለጋበዘው ሰው ሲነግረው “በጻድቃን ትንሣኤ ብድራት ይመለስልሃል” ብሏል። ከተጋበዙት መካከል አንዱ ኢየሱስ በተናገረው ሐሳብ መስማማቱን ሲገልጽ “በአምላክ መንግሥት፣ ከማዕድ የሚበላ ደስተኛ ነው” አለ። (ሉቃስ 14:15) ግለሰቡ ይህ ታላቅ መብት መሆኑ ገብቶታል። ይሁንና ኢየሱስ ቀጥሎ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንዳጎላው እንዲህ ዓይነት አድናቆት ያለው ሁሉም ሰው አይደለም።
“አንድ ሰው ትልቅ የራት ግብዣ አዘጋጅቶ ብዙ ሰዎች ጠራ። . . . የተጋበዙትን ሰዎች ‘አሁን ሁሉም ነገር ስለተዘጋጀ ኑ’ ብሎ እንዲጠራቸው ባሪያውን ላከ። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰበብ ያቀርቡ ጀመር። የመጀመሪያው ‘እርሻ ስለገዛሁ ሄጄ ማየት አለብኝ፤ ስለዚህ እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለው። ሌላውም ‘አምስት ጥማድ በሬዎች ገዝቻለሁ፤ ልፈትናቸው ስለሆነ እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለ። ሌላኛው ደግሞ ‘ገና ማግባቴ ስለሆነ መምጣት አልችልም’ አለ።”—ሉቃስ 14:16-20
እነዚህ የማይረቡ ሰበቦች ናቸው! አንድ ሰው እርሻም ሆነ ከብቶች ከመግዛቱ በፊት በደንብ እንደሚያያቸው የታወቀ ነው፤ በመሆኑም እነዚህን ነገሮች ከገዛ በኋላ መመልከቱ አጣዳፊ አይደለም። ሦስተኛው ሰው ደግሞ ለማግባት እየተዘጋጀ አይደለም። የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ አልፏል፤ ስለዚህ ማግባቱ አንድን ትልቅ ግብዣ ከመቀበል ሊያግደው አይገባም። ጌታው ሰዎቹ የሰጡትን ሰበብ ሲሰማ ተናደደና ባሪያውን እንዲህ ሲል አዘዘው፦
“ፈጥነህ ወደ ከተማው አውራ ጎዳናዎችና ስላች መንገዶች ሄደህ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ ዓይነ ስውራንንና አንካሶችን ወደዚህ አምጣቸው።” ባሪያው የተባለውን ካደረገ በኋላም ቤቱ አልሞላም። በመሆኑም ጌታው ባሪያውን እንዲህ አለው፦ “ቤቴ እንዲሞላ ወደ ጎዳናዎችና ወደ ስላች መንገዶች ሄደህ ያገኘሃቸውን ሰዎች በግድ አምጥተህ አስገባ። እላችኋለሁ፣ ከእነዚያ ከተጋበዙት ሰዎች መካከል አንዳቸውም ያዘጋጀሁትን ራት አይቀምሱም።”—ሉቃስ 14:21-24
ይህ ምሳሌ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰዎች መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንዲችሉ ግብዣ የሚያቀርቡት እንዴት እንደሆነ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። መጀመሪያ ግብዣ የቀረበላቸው፣ አይሁዳውያን በተለይም የሃይማኖት መሪዎቹ ናቸው። ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ጊዜያት ሁሉ የቀረበላቸውን ግብዣ በጥቅሉ ሲታይ አልተቀበሉም። ይሁን እንጂ ግብዣው የቀረበው ለእነሱ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ፣ በአይሁድ ሕዝብ መካከል ለሚገኙት ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሰዎችና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ግለሰቦች ወደፊት ግብዣው ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚቀርብ እየጠቆመ መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚያ በኋላ፣ አይሁዳውያን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው ለሚያስቧቸው ሰዎች ሦስተኛና የመጨረሻ ግብዣ ይቀርባል።—የሐዋርያት ሥራ 10:28-48
በእርግጥም የኢየሱስ ምሳሌ ከእንግዶቹ አንዱ “በአምላክ መንግሥት፣ ከማዕድ የሚበላ ደስተኛ ነው” በማለት የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል።