ምዕራፍ 97
የወይኑ እርሻ ሠራተኞች ምሳሌ
በወይኑ እርሻ ላይ ‘ኋለኛ’ የሆኑት ሠራተኞች “ፊተኞች” ሆኑ
ኢየሱስ በፔሪያ ለሚገኙ አድማጮቹ “ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑ ደግሞ ፊተኞች” እንደሚሆኑ ተናግሮ መጨረሱ ነው። (ማቴዎስ 19:30) ይህን ሐሳብ ለማጠናከር በወይን እርሻ ላይ ስለሚሠሩ ሰዎች አንድ ምሳሌ ተናገረ፦
“መንግሥተ ሰማያት በወይን እርሻው ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር ማልዶ ከወጣ የእርሻ ባለቤት ጋር ይመሳሰላል። በቀን አንድ ዲናር ሊከፍላቸው ከተዋዋለ በኋላ ሠራተኞቹን ወደ ወይን እርሻው ላካቸው። በሦስት ሰዓት ገደማም ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈተው የቆሙ ሌሎች ሰዎች አየ፤ እነዚህንም ሰዎች ‘እናንተም ወደ ወይኑ እርሻ ሂዱ፤ ተገቢውንም ክፍያ እከፍላችኋለሁ’ አላቸው። እነሱም ሄዱ። ዳግመኛም በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። በመጨረሻም በ11 ሰዓት ገደማ ወጥቶ ቆመው የነበሩ ሌሎች ሰዎች አገኘና ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው?’ አላቸው። እነሱም ‘የሚቀጥረን ሰው ስላጣን ነው’ ሲሉ መለሱለት። እሱም ‘እናንተም ወደ ወይኑ እርሻ ሄዳችሁ ሥሩ’ አላቸው።”—ማቴዎስ 20:1-7
የኢየሱስ አድማጮች “መንግሥተ ሰማያት” እና “የእርሻ ባለቤት” የሚሉትን አገላለጾች ሲሰሙ ይሖዋ አምላክን ሳያስቡ አይቀሩም። ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋን የወይን እርሻ ባለቤት እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል፤ በወይን እርሻ የተመሰለው ደግሞ የእስራኤል ብሔር ነው። (መዝሙር 80:8, 9፤ ኢሳይያስ 5:3, 4) በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ሰዎች በወይኑ እርሻ ሠራተኞች ተመስለዋል። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ግን ያለፈውን ጊዜ ሳይሆን አሁን በእሱ ዘመን ያለውን ሁኔታ ለማመልከት ነው።
ከጥቂት ጊዜ በፊት፣ ከፍቺ ጋር በተያያዘ ሊፈትኑት እንደሞከሩት ፈሪሳውያን ያሉ የሃይማኖት መሪዎች በአምላክ አገልግሎት ሁልጊዜ እንደተጠመዱ ተደርገው ይቆጠራሉ። ሙሉ ክፍያ ማለትም በቀን አንድ ዲናር እንደሚጠብቁ የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች ናቸው።
በዚህ ቡድን ውስጥ የተካተቱ ካህናትና ሌሎች ሰዎች፣ ተራውን ሕዝብ በአምላክ የወይን እርሻ ላይ የተወሰነ ሰዓት ብቻ እንደሚሠራ ይኸውም አምላክን ከእነሱ ባነሰ መንገድ እንደሚያገለግል አድርገው ይመለከቱታል። ተራው ሕዝብ፣ በኢየሱስ ምሳሌ ላይ “በሦስት ሰዓት ገደማ” እንዲሁም በቀኑ ውስጥ በኋላ ላይ ይኸውም በስድስት፣ በዘጠኝና በመጨረሻም በአሥራ አንድ ሰዓት ከተቀጠሩት ሠራተኞች ጋር ይመሳሰላል።
የኢየሱስ ተከታይ የሆኑት ወንዶችና ሴቶች የሚታዩት ‘እንደተረገመ ሕዝብ’ ተደርገው ነው። (ዮሐንስ 7:49) አብዛኛውን የሕይወት ዘመናቸውን ያሳለፉት በዓሣ አጥማጅነት ወይም በሌላ የጉልበት ሥራ ነው። ከዚያም በ29 ዓ.ም. “የወይኑ እርሻ ባለቤት” እነዚህን ትሑት ሰዎች፣ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነው ለአምላክ እንዲሠሩ እንዲጠራቸው ኢየሱስን ላከው። ኢየሱስ የጠቀሳቸው “ኋለኞች” ይኸውም በ11ኛው ሰዓት የመጡት የወይኑ እርሻ ሠራተኞች እነሱ ናቸው።
ኢየሱስ፣ የሥራው ቀን ሲያበቃ ምን እንደተከናወነ በመግለጽ ምሳሌውን ደመደመ፦ “በመሸም ጊዜ የወይኑ እርሻ ባለቤት የሠራተኞቹን ተቆጣጣሪ ‘ሠራተኞቹን ጠርተህ በመጨረሻ ከተቀጠሩት አንስቶ በመጀመሪያ እስከተቀጠሩት ድረስ ደሞዛቸውን ክፈላቸው’ አለው። በ11 ሰዓት የተቀጠሩት ሰዎች መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። በመሆኑም በመጀመሪያ የተቀጠሩት ሲመጡ እነሱ የበለጠ የሚከፈላቸው መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን እነሱም የተከፈላቸው አንድ አንድ ዲናር ነበር። ክፍያውን ሲቀበሉ በእርሻው ባለቤት ላይ ማጉረምረም ጀመሩ፤ እንዲህም አሉት፦ ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት ሰዎች አንድ ሰዓት ብቻ ነው የሠሩት፤ ያም ሆኖ አንተ ቀኑን ሙሉ ስንደክምና በፀሐይ ስንቃጠል ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግካቸው!’ እሱ ግን ከመካከላቸው ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ‘የኔ ወንድም፣ ምንም የበደልኩህ ነገር የለም። የተስማማነው አንድ ዲናር እንድከፍልህ ነው፣ አይደለም እንዴ? ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ። በመጨረሻ ለተቀጠሩት ለእነዚህ ሰዎችም ለአንተ የሰጠሁትን ያህል መስጠት ፈለግኩ። በገዛ ገንዘቤ የፈለግኩትን የማድረግ መብት የለኝም? ወይስ እኔ ደግ በመሆኔ ዓይንህ ተመቀኘ?’ ስለሆነም ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞች ደግሞ ኋለኞች ይሆናሉ።”—ማቴዎስ 20:8-16
ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስ ምሳሌ የመጨረሻ ክፍል አስገርሟቸው ይሆናል። ራሳቸውን “ፊተኞች” አድርገው የሚቆጥሩት የሃይማኖት መሪዎች “ኋለኞች” የሚሆኑት እንዴት ነው? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትስ “ፊተኞች” የሚሆኑት እንዴት ነው?
ፈሪሳውያንና ሌሎች ሰዎች እንደ “ኋለኞች” የሚቆጥሯቸው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ፊተኞች” በመሆን ሙሉ ክፍያ ያገኛሉ። ኢየሱስ ሲሞት ምድራዊቷ ኢየሩሳሌም የተተወች ትሆናለች፤ ከዚያ በኋላ አምላክ አዲስ ብሔር ይኸውም ‘የአምላክ እስራኤልን’ ይመርጣል። (ገላትያ 6:16፤ ማቴዎስ 23:38) መጥምቁ ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ ስለ መጠመቅ በተናገረበት ወቅት ስለ እነዚህ ሰዎች ገልጿል። “ኋለኞች” ሆነው የቆዩት ሰዎች፣ እንዲህ ዓይነት ጥምቀት ለመጠመቅና “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ስለ ኢየሱስ የመመሥከር መብት ለማግኘት የመጀመሪያዎቹ ይሆናሉ። (የሐዋርያት ሥራ 1:5, 8፤ ማቴዎስ 3:11) ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እየጠቆመ ያለው አስገራሚ ለውጥ ከገባቸው፣ “ኋለኞች” የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች ወደፊት በጣም ቅር እንደሚሰኙ ሊያስተውሉ ይችላሉ።