ምዕራፍ 118
ታላቅ መሆንን በተመለከተ ክርክር ተነሳ
ማቴዎስ 26:31-35 ማርቆስ 14:27-31 ሉቃስ 22:24-38 ዮሐንስ 13:31-38
ኢየሱስ ሥልጣንን አስመልክቶ ምክር ሰጠ
ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደሚክደው አስቀድሞ ተነገረ
የኢየሱስ ተከታዮች መለያ ፍቅር ነው
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ እግራቸውን በማጠብ፣ ትሑት ሆኖ ማገልገልን በተመለከተ ግሩም ትምህርት ሰጥቷቸዋል። እንዲህ ማድረጉ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ድክመት ስላለባቸው ነው። እነዚህ ሰዎች ለአምላክ ያደሩ ቢሆኑም ‘ከመካከላችን ማን ታላቅ ነው?’ የሚለው ጉዳይ አሁንም ያሳስባቸዋል። (ማርቆስ 9:33, 34፤ 10:35-37) ይህ ድክመታቸው በዚህ ምሽት እንደገና ታየ።
“‘ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?’ በሚል በመካከላቸው የጦፈ ክርክር ተነሳ።” (ሉቃስ 22:24) ኢየሱስ በማይረባ ነገር እንደገና እየተጨቃጨቁ መሆኑን ሲያይ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ታዲያ ምን አደረገ?
ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ እንዲህ ያለ ዝንባሌና ባሕርይ በማሳየታቸው ከመቆጣት ይልቅ በትዕግሥት የሚከተለውን አሳማኝ ሐሳብ አቀረበላቸው፦ “የአሕዛብ ነገሥታት በእነሱ ላይ ሥልጣናቸውን ያሳያሉ፤ እንዲሁም በሕዝባቸው ላይ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ። . . . ለመሆኑ በማዕድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያገለግል ማን ይበልጣል?” ከዚያም “እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አገልጋይ ሆኜ ነው” በማለት እሱ በተደጋጋሚ የተወላቸውን ምሳሌ አስታወሳቸው።—ሉቃስ 22:25-27
ሐዋርያቱ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ኢየሱስ በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ከጎኑ ሳይለዩ ቆይተዋል። በመሆኑም “አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ ሁሉ እኔም ከእናንተ ጋር ለመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ” አለ። (ሉቃስ 22:29) እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች ናቸው። ከእነሱ ጋር የገባው ቃል ኪዳን በመንግሥቱ ከእሱ ጋር እንዲሆኑና አብረውት እንዲነግሡ መንገድ እንደሚከፍት አረጋገጠላቸው።
ሐዋርያቱ እንዲህ ዓይነት ግሩም ተስፋ የተዘረጋላቸው ቢሆንም አሁንም ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ “ሰይጣን ሁላችሁንም እንደ ስንዴ ያበጥራችሁ ዘንድ ጥያቄ አቅርቧል” አላቸው፤ ስንዴ ሲበጠር ይበተናል። (ሉቃስ 22:31) ኢየሱስ “‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ስለተጻፈ በዚህች ሌሊት ሁላችሁም በእኔ ላይ በሚደርሰው ነገር የተነሳ ትሰናከላላችሁ” በማለትም አስጠነቀቃቸው።—ማቴዎስ 26:31፤ ዘካርያስ 13:7
ይሁንና ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ በአንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልሰናከልም!” ሲል በልበ ሙሉነት ተናገረ። (ማቴዎስ 26:33) ኢየሱስም በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ እንደሚክደው ለጴጥሮስ ነገረው። ሆኖም ኢየሱስ አክሎ “እኔ . . . እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ምልጃ አቀረብኩ፤ አንተም በተመለስክ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ” አለው። (ሉቃስ 22:32) ጴጥሮስ ግን “አብሬህ መሞት ቢያስፈልገኝ እንኳ በምንም ዓይነት አልክድህም” በማለት አስረግጦ ተናገረ። (ማቴዎስ 26:35) ሌሎቹ ሐዋርያትም እንደዚሁ አሉ።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ። እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁዳውያን ‘ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኳቸው ሁሉ አሁን ደግሞ ለእናንተ ይህንኑ እላችኋለሁ” አላቸው። ከዚያም “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” አለ።—ዮሐንስ 13:33-35
ኢየሱስ ከእነሱ ጋር የሚቆየው ጥቂት ጊዜ እንደሆነ ሲናገር ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ወዴት ልትሄድ ነው?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም “እኔ ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ በኋላ ግን ትከተለኛለህ” ሲል መለሰ። ጴጥሮስ ግራ ስለተጋባ “ጌታ ሆይ፣ አሁን ልከተልህ የማልችለው ለምንድን ነው? ሕይወቴን ስለ አንተ አሳልፌ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ” አለው።—ዮሐንስ 13:36, 37
ቀጥሎ ደግሞ ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱን የገንዘብ ኮሮጆም ሆነ የምግብ ከረጢት ሳይዙ በገሊላ እየዞሩ እንዲሰብኩ ልኳቸው የነበረበትን ጊዜ ጠቀሰ። (ማቴዎስ 10:5, 9, 10) ከዚያም “የጎደለባችሁ ነገር ነበር?” በማለት ጠየቃቸው። እነሱም “ምንም አልጎደለብንም” አሉ። ይሁንና ወደፊትስ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ኢየሱስ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፦ “የገንዘብ ኮሮጆ ያለው ኮሮጆውን ይያዝ፤ የምግብ ከረጢት ያለውም እንዲሁ፤ ሰይፍ የሌለው ደግሞ መደረቢያውን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። ይህን የምላችሁ ‘ከዓመፀኞች ጋር ተቆጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ላይ መፈጸም ስላለበት ነው። ስለ እኔ የተነገረው ነገር ፍጻሜውን እያገኘ ነውና።”—ሉቃስ 22:35-37
ኢየሱስ ይህን ሲል ከክፉ አድራጊዎች ወይም ከዓመፀኞች ጋር በእንጨት ላይ የሚሰቀልበትን ጊዜ መጥቀሱ ነው። ከዚያ በኋላ ተከታዮቹ ከባድ ስደት ይደርስባቸዋል። ሐዋርያቱ ለሚመጣው ነገር ዝግጁ እንደሆኑ ስለተሰማቸው “ጌታ ሆይ፣ ይኸው ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉት። እሱም “በቂ ነው” አላቸው። (ሉቃስ 22:38) ሁለት ሰይፍ መያዛቸው ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ሌላ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት እንዲሰጣቸው አጋጣሚ ይፈጥራል።