ትምህርት 47
ይሖዋ ኤልያስን አበረታታው
ኤልዛቤል በባአል ነቢያት ላይ የደረሰውን ነገር ስትሰማ በጣም ተናደደች። ከዚያም ‘ነገ አንተም እንደነዚያ የባአል ነቢያት ትገደላለህ’ ብሎ ለኤልያስ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከችበት። ኤልያስ በጣም ስለፈራ ወደ በረሃ ሸሸ። ከዚያም ‘ይሖዋ፣ አሁንስ በቅቶኛል። ብሞት ይሻለኛል’ በማለት ወደ ይሖዋ ጸለየ። ኤልያስ በጣም ስለደከመው አንድ ዛፍ ሥር ተኛ።
ከዚያም አንድ መልአክ ቀሰቀሰውና ‘ተነስና ብላ’ አለው። ኤልያስም በጋሉ ድንጋዮች ላይ የተቀመጠ ዳቦና ውኃ የያዘ ዕቃ አየ። ከበላና ከጠጣ በኋላ ተመልሶ ተኛ። መልአኩ በድጋሚ ቀሰቀሰውና ‘ብላ። ረጅም መንገድ ስለምትሄድ ኃይል ይሰጥሃል’ አለው። ስለዚህ ኤልያስ እንደገና በላ። ከዚያም 40 ቀንና 40 ሌሊት ተጉዞ ወደ ኮሬብ ተራራ ደረሰ። በዚያም ኤልያስ አንድ ዋሻ ውስጥ ገብቶ ተኛ። ከዚያም ይሖዋ አነጋገረው። ‘ኤልያስ፣ እዚህ ምን ታደርጋለህ?’ አለው። ኤልያስም እንዲህ በማለት መለሰ፦ ‘እስራኤላውያን ለአንተ የገቡትን ቃል ትተዋል። መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም ገድለዋል። አሁን ደግሞ እኔንም ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ።’
ይሖዋም ‘ውጣና ተራራው ላይ ቁም’ አለው። በመጀመሪያ ኃይለኛ ነፋስ ነፈሰ። ከዚያም የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ፤ በኋላም እሳት ተነሳ። በመጨረሻ ኤልያስ ዝግ ያለና ለስለስ ያለ ድምፅ ሰማ። በዚህ ጊዜ ኤልያስ ፊቱን በልብሱ ሸፍኖ ከዋሻው ውጭ ቆመ። ከዚያም ይሖዋ ኤልያስ የሸሸው ለምን እንደሆነ ጠየቀው። ኤልያስም ‘የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ’ አለው። ይሖዋ ግን እንዲህ አለው፦ ‘ብቻህን አይደለህም። በእስራኤል ውስጥ እኔን የሚያመልኩ 7,000 ሰዎች አሉ። ሂድና ኤልሳዕን በአንተ ፋንታ ነቢይ እንዲሆን ሹመው።’ ኤልያስ ወዲያውኑ ሄዶ ይሖዋ ያዘዘውን አደረገ። ይሖዋ እንድታደርግ የሚፈልግብህን ነገር ስታደርግ ይሖዋ አንተንም እንደሚረዳህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። እስቲ ቀጥሎ ደግሞ በድርቁ ወቅት የተፈጸመ አንድ ሁኔታ እንመልከት።
“ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።”—ፊልጵስዩስ 4:6