የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቤተሰብን አንድ ያደርጋል
ዛሬ በአብዛኛው የዓለም ክፍል የቤተሰብ አንድነት የተረሳ ነገር ሆኗል ለማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብ አንድነት የሚገኝበት ምሥጢር ምን እንደሆነ ይገልጻል። ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ልብ ብለህ ተመልከታቸው፦ “ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል።” (ማቴዎስ 7:24) ከይሖዋ ምስክሮች መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች እነዚህን ቃላት በሥራ ላይ በማዋላቸውና ጠንካራ ቤተሰብ ለመገንባት መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መሠረት አድርገው በመጠቀማቸው አንድነት አግኝተዋል። ቀጥሎ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው ሌሎችም እንዲህ ያለውን አንድነት እያገኙ ነው።
ዳንኤል በፈረንሳይ የጦር ሠራዊት ውስጥ በማገልገል ላይ እያለ የጦር ሠራዊቱ የነፍስ አባት ዳንኤል መጽሐፍ ቅዱስ እንዲገዛ ሐሳብ አቀረበለት። ዳንኤልም እንደተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ገዛና ሳያቋርጥ ማንበብ ጀመረ። ቆይቶም ወደ ታሂቲ ተቀየረ። የዳንኤል ባልደረቦች ከነበሩት ወታደሮች አንዳንዶቹ የሰባተኛው ቀን አክባሪዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ሞርሞን የሚባል ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው። ብዙውን ጊዜ ስለ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ይጨዋወቱ ነበር። አንድ ቀን አንድ የሃምሳ አለቃ ዳንኤልን የይሖዋ ምስክር ከሆነችው ባለቤቱ ጋር አስተዋወቀው። እርሷም አንድ ሙሉ ቀን ዳንኤል ለሚጠይቃቸው ብዙ ጥያቄዎች መልስ ስትሰጥ ዋለች። ከዚያም በታሂቲ ከሚገኙት የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች መካከል ከአንደኛው ጋር እንዲገናኝ አደረገች። ወዲያው ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ።
በፈረንሳይ አገር የሚኖሩት የዳንኤል ወላጆች ጥብቅ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች ነበሩ። አባቱ የተማሪዎች አማካሪና በአንድ የካቶሊክ ትምህርት ቤት የሃይማኖታዊ ትምህርት ኃላፊ ነበር። ዳንኤል የሚማረውን የላቀና ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ትምህርት ለወላጆቹ ማካፈል ፈለገ። ለወላጆቹ በሚጽፈው ደብዳቤ ውስጥ ቀስ እያለ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን መጨመር ጀመረ።
መጀመሪያ ላይ የዳንኤል እናት ደስ ብሏት ነበር፤ ከልጅዋ ደብዳቤዎች በአንደኛው ላይ ይሖዋ የሚለውን ስም ስታነብ ግን በጣም ደነገጠች። ጥቂት ቀናት ቆይቶ የይሖዋ ምስክሮች “አደገኛ ሃይማኖታዊ ቡድኖች” እንደሆኑ የሚናገር የሬዲዮ ፕሮግራም አዳመጠች። እርሷም ዳንኤል ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ሁሉ በአስቸኳይ እንዲያቋርጥ እንደምትፈልግ የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፈች። ይሁን እንጂ ዳንኤል በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ቀጠለበትና እድገት አሳየ፤ ብዙም ሳይቆይ ከጦር ሠራዊቱ ወጥቶ ወደ ፈረንሳይ ለመመለስ ዝግጅት አደረገ።
ዳንኤል ከወላጆቹ ጋር መኖር እንደጀመረ ወዲያው በየምሽቱ አንዳንዴም እስከ ሌሊት በመቆየት ከእናቱ ጋር ረዘም ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ማድረግ ጀመረ። በመጨረሻም ከዳንኤል ጋር ወደ መንግሥት አዳራሽ ለመሄድ ተስማማች። በስብሰባ በተገኘችበት የመጀመሪያው ቀን ልቧ በጣም ስለ ተነካ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች። ወዲያው ፈጣን እድገት አደረገችና ተጠመቀች።
የዳንኤል አባት ተቃዋሚ ባይሆንም ለሙያውና ለሃይማኖታዊ ሥራው ከፍተኛ ፍቅር ነበረው። ሆኖም በአንድ ወቅት ባለቤቱንና ዳንኤልን የወረዳ ስብሰባ ወደሚደረግበት ቦታ በመኪና አደረሳቸው። ዕለቱ ሐምሌ 14 ነበር። በከተማው ለባስቲል ቀን መታሰቢያ የሚደረገውን ሰልፍ ለማየት አስቦ ነበር። የሰልፉ ጊዜ እስኪደርስ እየጠበቀ እያለ የማወቅ ጉጉት አደረበትና ወደ ስብሰባ አዳራሹ ገብቶ የሚደረገውን ለማየት ወሰነ። በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ባየው ሥነ ሥርዓትና ሰላም ተነካ። የተለያዩትን የስብሰባ ክፍሎች እየተዘዋወረ ሲመለከት ሁሉም “ወንድም” እያሉ ይጠሩት ነበር። ስለ ባስቲል ቀን የሚደረገውን ሰልፍ ረሳና ስብሰባው እስኪያልቅ ድረስ ቆየ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት ጠየቀ። ስለ እውነት ባለው እውቀት ፈጣን እድገት አሳየ። ይሁን እንጂ ብዙ ባወቀ መጠን ሥራውን እየጠላ መጣ። ስለዚህ በ58 ዓመቱ ሥራውን ለቀቀ። አሁን በቤተሰቡ ውስጥ ያሉት ሦስቱም ራሳቸውን ወስነውና ተጠምቀው ይሖዋን በአንድነት ያገለግላሉ።
የዳንኤልን ቤተሰብ አንድ ያደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው። ሌሎች ቤተሰቦችም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከተማሩና ከልብ ከሠሩበት አንድ ሊያደርጋቸው ይችላል።