በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ልዩ ትርጉም ያላቸው ጽሕፈቶች
“ይሖዋ ሲት ቴቤ ኩስቶስ”
በምሥራቅ ስዊዘርላንድ፣ ሴሌሪና በተባለች መንደር ውስጥ በሚገኝ በ17ኛው መቶ ዘመን በተሠራ አንድ ቤት የፊት ግድግዳ ላይ የተቀረጹት እነዚህ ቃላት “ይሖዋ ጠባቂህ ይሁን” የሚል ትርጉም አላቸው። ተራራማ በሆነው በዚህ አካባቢ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በተሠሩ ቤቶች፣ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ግድግዳ ላይ የአምላክ ስም ተቀርጾ ወይም በልዩ ልዩ ቀለማት ተጽፎ ማግኘት ያልተለመደ ነገር አይደለም። ግን ይሖዋ የተባለው የአምላክ ስም እንዴት ይህን ያህል ታዋቂ ሊሆን ቻለ?
በ15ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የጥንቷ ሪኤሺያ (አሁን ደቡብ ምሥራቅ ጀርመን፣ ኦስትሪያና ምሥራቃዊ ስዊዘርላንድ ያሉበትን ቦታ በሙሉ የምታካልል ነበረች) ከሮም ክፍላተ ሃገር አንዷ ሆነች። ነዋሪዎቿም ላቲን የወለደው፣ በኋላም ወደ ብዙ የቋንቋ ቤተሰቦች የተከፋፈለው የሮማይስጥ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሆኑ። ይህ ቋንቋ በስዊዘርላድ በሚገኙት የአፕስ ሸለቆዎች ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች እንዲሁም በሰሜን ኢጣሊያ ውስጥ እስካሁን ይነገራል።
ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ በከፊል ወደ ሮማይስጥ ቋንቋ ተተረጎመ። አንዱ እትም ቢብሊያ ፒትሽና የተባለ ሲሆን መዝሙርንና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን የያዘ ነው። በ1666 በታተመው በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የሚለው ስም በመዝሙር ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። በብዙ ቤቶች ውስጥ ዋናው የሚነበብ ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ እንደመሆኑ መጠን ቢብሊያ ፒትሽና ን የሚያነቡ ሁሉ የፈጣሪን ስም ሊያውቁት ቻሉ።
ይሁን እንጂ ቀጣዮቹ ትውልዶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለሆኑ ጉዳዮች ደንታ የሌላቸው ሆኑ። ብዙዎች “ይሖዋ” የሚለውን ቃል ትርጉም ለማወቅ ምንም አልተጨነቁም፤ ካህናቱም ቢሆኑ ምንነቱን ለማስረዳት ምንም ያህል አልጣሩም። በዚህ ምክንያት እነዚህ በግድግዳ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች ካለፈው ዘመን የተገኙ የጌጥ ቅርሶች ብቻ ሆነው ቀሩ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ሕዝቡን ለማስተማር ጉልህ ጥረት እየተደረገ ነው። የዕረፍት ጊዜያቸውን በነዚያ ውብ ሸለቆዎች ለማሳለፍ የሚመጡ በአገሪቱ ቆላማ ቦታዎች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች ስሙ ይሖዋ ስለሆነው አምላክ ለማስተማር ለየት ያለ ጥረት እያደረጉ ናቸው። እንዲያውም አንዳንድ ምሥክሮች ፈጣሪ ለምድርና ለሰው ልጆች ስላለው አስደናቂ ዓላማ ለሰዎች በይበልጥ ለመናገር ይችሉ ዘንድ በዚህ አካባቢ ለመኖር መርጠዋል። በዚህ ምክንያት ሰዎቹ ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋ የበለጠ እያወቁ ሲሄዱ እነዚህ ጥንታዊ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ የሮማይስጥ ጽሑፎች ያዘሉትን ጥልቅ ትርጉም ይበልጥ እየተረዱት ሄደዋል።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ፖርትዮ ሜያ ይሖዋ ክፍሌ ነው።—መዝሙር 119:57 ን [አዓት] ተመልከት።