የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሰደዳሉ
ከአቤል ዘመን ጀምሮ አያሌ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ስደት ደርሶባቸዋል። (ሉቃስ 11:49–51) መጽሐፍ ቅዱስ “በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” በማለት ማስጠንቀቁ አያስደንቅም! (2 ጢሞቴዎስ 3:12) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ከ25 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በእገዳ ሥር ከመሆናቸውም በላይ ስደት የሚደርስባቸው ለዚህ ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸው ከመታገድ አልፎ ከሃይማኖተኞች ስደት በሚደርስባቸው በአንድ አገር ውስጥ ከ12,000 የሚበልጡት የምሥራቹ አስፋፊዎች ከ15,000 በላይ የሆኑ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት በቅንዓት መሥራታቸውን ቀጥለዋል። እርግጥ ነው፣ የስብከት ሥራቸው የሚከናወነው በብልሃት ነው። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸውን የሚያከናውኑት በግል ቤቶች ውስጥ ሲሆን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ወደ እነዚህ ስብሰባዎች ሲጋብዙ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።
በቅርቡ የአገሪቱ መንግሥት ለምሥክሮቹ ያለውን አመለካከት በማላላቱ መንግሥት ጣልቃ ሳይገባባቸው ሥራቸውን እያከናወኑ ነው። ነገር ግን የተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖች ያላቸውን ተሰሚነት አለመግባባት ለመፍጠር እየተጠቀሙበት ነው።
በአንድ ከተማ በቁጣ የገነፈሉ ወደ 200 የሚጠጉ ሃይማኖታዊ አክራሪ ረብሸኞች 50 የሚያክሉ የይሖዋ ምሥክሮች የጉባኤ ስብሰባ እያደረጉበት ወደነበረው ቤት እየገሰገሱ ሄዱ። አንዳንዶቹ ረብሸኞች ድንጋይ የያዙ ሲሆን ሃይማኖታዊ መፈክሮች ያሰሙ ነበር። ዓላማቸው ምሥክሮቹን መደብደብና በቤቱ ላይ ጉዳት ማድረስ ነበር። ሃይማኖታዊ መሪዎቹ የስብሰባውን ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ተከታትለው ጥቃት ለመሰንዘር አመቺ የሆነውን ጊዜ ሲጠባበቁ ነበር። ረብሸኞቹ ወደ ቤቱ ሊገቡ ትንሽ ሲቀራቸው 15 ፖሊሶች ደርሰው እንዲበታተኑ አደረጓቸው። ከወንድሞች መካከል የደወለና ለፖሊስ ያሳወቀ ስላልነበረ ይህ ሁኔታ ምሥክሮቹን አስደንቋቸዋል።
በሌላ ጊዜያት ግን ተቃዋሚዎቹ ተሳክቶላቸው ነበር። ብዙ ወንድሞች ፍርድ ቤት ቀርበው እስራት ተፈርዶባቸዋል። አንድ በፍርድ ቤት የሚታይ ጉዳይ ለረዥም ዓመታት ተንዛዝቶ ስለነበር አቃቤ ሕግ በጉዳዩ የተሰላቸ ይመስል ነበር። ቢሆንም በአካባቢው ቄስ ጎትጓችነት ጉዳዩ እንደገና ለፍርድ ቀረበና የተከሰሰው የይሖዋ ምሥክር እንዲታሰር ተወሰነ።
በሌላ ስፍራ የይሖዋ ምሥክሮች የጌታ ራት ለማክበር በአንድ መኖሪያ ቤት ተሰብስበው ነበር። በነጋታው ብዙ ፖሊሶች መጥተው የቤቱን ባለቤትና ስብሰባውን ይመራ የነበረውን ወንድም ያዟቸው። በፖሊስ ጣቢያው ውስጥ በአሠቃቂ ሁኔታ ተደበደቡ። ረዥም ሰዓት የፈጀ ጭካኔ የተሞላበት ምርምራ ተደረገ። በተጨማሪ አንዱን የይሖዋ ምሥክር ቀዝቃዛ የውኃ ጉድጓድ ውስጥ በመጨመር አሠቃይተውታል።
ፖሊሶቹ ይህንን ሥቃይ ያደረሱባቸው ለምን ነበር? አሁንም ሃይማኖታዊ አክራሪዎቹ በአካባቢው ቄስ በመታገዝ ፖሊሶቹ ከወሰዱት እርምጃ በስተጀርባ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ የፖሊስ አዛዡ ምሥክሮቹ የተያዙት ያለእርሱ ትእዛዝ እንደነበረ ገለጸ። በግልጽ ይቅርታ ከመጠየቃቸውም በላይ ለድብደባው ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ተግሣጽ ተሰጣቸው።
ኃይለኛ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበካቸውን ቀጥለዋል። “እነሆ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች፣ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ” የሚለውን የኢየሱስ ምክር ይከተላሉ።—ማቴዎስ 10:16 የ1980 ትርጉም
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለመጀመሪያ ጊዜ ስደት የደረሰበት አቤል ነው