የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ—ኒው ዚላንድ
ደሴቶች ይሖዋን ሊያወድሱ ይችላሉን? ኢሳይያስ 42:10 “ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፣ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፣ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ” በማለት ስለሚናገር ደሴቶች ይሖዋን ሊያወድሱ ይችላሉ። ኒው ዚላንድን ኒው ዚላንድ ያሰኟት ደሴቶችም ይሖዋን እንደሚያወድሱ አያጠራጥርም። ኒው ዚላንድ በሐይቆቿ፣ በባሕረ ሰላጤዎቿ፣ በረዣዥም ተራሮቿ፣ በግግር በረዶቿ፣ በባሕር ዳርቻዎቿ፣ ፈርን የተባሉ ተክሎች ባሉባቸው የዝናባማ ክልል ጥቅጥቅ ያሉ ደኖቿና ለም በሆኑ የግጦሽ መስኮቿ የሰማይና ምድር ፈጣሪ ስለሆነው አምላክ ግርማና ታላቅነት በግልጽ ትናገራለች።
ብዙ ቁጥር ያላቸው የኒው ዚላንድ ነዋሪዎች ከ20ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ጀምሮ ፊታቸውን ወደ ንጹሕ አምልኮ በማዞርና የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች በማካፈል የውዳሴ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። በቅርብ ጊዜ ለዘመድ አዝማድ ስለ መመሥከር ጥሩ ተሞክሮ የሰማ አንድ የይሖዋ ምሥክር ለቤተሰቦቹ እውነትን ለመንገር ወሰነ። ለአብዛኞቹ የቤተሰቡ አባላት በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ሰጣቸው። ምን ውጤት ተገኘ? እህቱና ወንድሙ እንደሚያጠኑ፣ የወንድሙ ልጅ ደግሞ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነና ብዙዎቹ ዘመዶቹ በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው እውነት ጥሩ ምላሽ እያሳዩ እንደሆነ ተናግሯል። ወላጆቹ ሳይቆጠሩ ስድስት ወንድሞችና ዘጠኝ እህቶች ስላሉት ገና ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል!
የይሖዋ ምሥክሮች በአንድነት የመንግሥት አዳራሽ ሲሠሩም ይሖዋ ተወድሷል። ለምሳሌ ያህል የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ የሆነው ሮይ ፔርኪንስ ኦፖቲኪ ኒውስ በተባለው ጋዜጣ የግንቦት 17, 1994 እትም ላይ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አማኝ ባልሆንም ለአምላክ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው አብዛኛውን ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ለግንባታው ሥራ የሠውት ሠራተኞች የሠሯቸው ሥራዎችና ያደረጉት ጥረት በጣም ነክቶኛል።
“አብዛኛው ሥራ በተከናወነበት በእነዚህ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት አንድም ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው አላየሁም ወይም እንዳለ አልሰማሁም። . . . ሁሉም ሴቶች በጊዜያዊ መወጣጫዎቹ ላይ ከወንዶች ጋር የሚሠሩት ዘና ብለውና ተደስተው ነው። ግድግዳውን እየፈቀፈቁ እንደገና ይለስናሉ፣ ለግንባታው የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ይዘው ይወጣሉ እንዲሁም ከቦታ ወደ ቦታ ያጓጉዛሉ።
“እስቲ አንዴ ሲጋራ ላጭስ በማለት የሥራ ጊዜ የሚያባክን ሠራተኛ አልነበረም። ከቀለም ሽታና ከጡብ ብናኝ በስተቀር ሁሉም ሠራተኞች ንጹሕ አየር ይተነፍሱ ነበር።”
የኦፖቲኪ ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “መላው የግንባታ ሥራ የከተማውን ነዋሪዎች አፍ አስከፍቷል። ሁሉም ሰው ስለ ግንባታው የሚነጋገር ይመስላል። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተጀምረዋል። ከሁሉም በላይ ያስደሰተን አጥባቂ ሃይማኖተኛ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ጉዳይ ነው። እነዚህ ባልና ሚስት ለብዙ ዓመታት ከእኛ ጋር ለመነጋገር አይፈልጉም ነበር። ግንባታው ይከናወንበት ወደነበረው ስፍራ በየቀኑ ይመጡ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመሩ። ከዚያም ባልየው እንዲህ አለ፦ ‘የአምላክ ሕዝቦች እንደሆናችሁ ለማየት ችዬአለሁ። እንደነዚህ ከመሰሉ ሰዎች ጋር መቀራረቡን ዕድሜ ልኬን ስመኘው የነበረ ነገር ነው።’”
ባለፈው ዓመት ኦታጎ ዴይሊ ታይምስ የተባለ ጋዜጣ አዘጋጅ በዱኔዲን ከተማ በፈጣን ግንባታ ስለተሠራ አንድ የመንግሥት አዳራሽ የሚከተለውን ብሏል፦ “የሚያስገርም ቅልጥፍና፣ የሚያስገርም ታታሪነትና ራስን በራስ መቻል የታየበት ነበር።” ይኸው ጋዜጣ እንዲህ በማለት ሐሳብ ሰጥቷል፦ “የከተማው ነዋሪዎች እዚያው ፊታቸው አንድ ትልቅ ሕንፃ በአንድ አፍታ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ በመመልከታቸው በጣም ተደንቀዋል። አብዛኞቹ ሰዎች እነዚህን የመሰሉ ሕብረት ያላቸው ብዙ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከተገኙና የመተባበር መንፈስ ካለ ሌሎች ከፍተኛ ለውጦችን ማምጣትና ጠቃሚ ግንባታዎችን ማከናወን ይቻላል ብለው ሳያስቡ አልቀሩም። ጠቃሚ የሆነ የጋራ ጥረት የሚያስገኘውን ስኬት ለማሳየት የመንግሥት አዳራሾችን በምሳሌነት መጥቀስ ይበቃል።”
የግንባታውን ቦታ ከጎበኙት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ የእርሱ ሃይማኖት በአባላት መቀነስ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኖችን እየሸጠ ሳለ ምሥክሮቹ “ቤተ ክርስቲያኖችን” እየገነቡ መሆኑን ተመለከተ። ሰውዬው እንዲህ በማለት በድፍረት ተናገረ፦ “አሥራ ሁለት ወር ያህል ብትታገሱ አንዱን የእኛን ቤተ ክርስቲያን መግዛት ትችሉ ነበር። ክፍያዎቹን መክፈል ስላልቻልን አንዱን መሸጥ ይኖርብናል። እናንተ ግን ለቄሶች አትከፍሉም። . . . ሕንፃዎቻችሁ ለጥገና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ አይደሉም። ለጥገና አስቸጋሪ የሆኑ ሾጣጣ ጣሪያዎች የሏቸውም።”
በእርግጥም ደሴቶች ይሖዋን ማወደስ ይችላሉ። በዚህች ውብ የፓስፊክ አገርና በዓለም ዙሪያ ለይሖዋ የሚቀርበው የውዳሴ ድምፅ ወደፊትም ከፍ ብሎ መሰማቱን ይቀጥል!
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአገሪቱ ሪፖርት መግለጫ፦
የ1994 የአገልግሎት ዓመት
የምሥክሮቹ ከፍተኛ ቁጥር፦12,867
ከሕዝቡ ብዛት ጋር ሲነጻጸር፦1 ምሥክር ለ271 ሰዎች
የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች፦24,436
የአቅኚዎች ብዛት በአማካይ፦1,386
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በአማካይ፦7,519
የተጠማቂዎች ቁጥር፦568
የጉባኤዎች ብዛት፦158
ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኝበት ቦታ፦ማኑሬዋ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1930 አካባቢ አቅኚዎች ወደ መስክ ሲሰማሩ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በማኑሬዋ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዴቮንፖርት ኦክላንድ የመንግሥቱ መልእክት ሲሰበክ