‘አምላክ ከቁም ነገር ይቆጥረኛልን?’
“አምላክ ከቁም ነገር ይቆጥረኛልን? ያስብልኛልን?” ይህ ክርስቲያኒቲ ቱዴይ በተባለ መጽሔት ላይ የአንድ ዓምድ ርዕስ ነው። የዚህ ዓምድ አዘጋጅ የሆኑት ፊሊፕ ያንሲ እንዲህ ብለዋል፦ “የደራሲነት ሙያዬ በአብዛኛው በሰው ልጆች አሳዛኝ ገጠመኝ ላይ ያተኮረ ነው። አንድ ሰው ሙሉ በሙሉ ያልዳነውን የቆየ ቁስሉን በጣቶቹ እንደሚያሻሽ እነዚህን ጥያቄዎች ደጋግሜ አነሳቸዋለሁ። የጻፍኳቸውን መጽሐፎች የሚያነቡ ሰዎች ደብዳቤዎች ይጽፉልኛል። በጭንቀት የተሞላው ሕይወታቸው ጥርጣሬዬን ይበልጥ ያጠናክሩታል።”
አንተም አምላክ ስለ እኔ ያስባልን? ብለህ ራስህን ጠይቀህ ታውቅ ይሆናል። “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል” በማለት የሚናገረውን ዮሐንስ 3:16ን በሚገባ ታውቅ ይሆናል። ወይም ደግሞ ኢየሱስ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ’ እንደመጣ የሚናገረውን ማቴዎስ 20:28ን አንብበህ ይሆናል። ቢሆንም ‘አምላክ እኔን በቁም ነገር ይመለከተኛልን? በግለሰብ ደረጃ ያስብልኛልን?’ በማለት አሁንም ትጠይቅ ይሆናል። ቀጥሎ እንደምንመለከተው አምላክ በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል ብለን እምነት የምንጥልበት ጥሩ ምክንያት አለን።