‘ሐቀኛ ሰዎች ያስፈልጉናል’
በዛሬው ዓለም ውስጥ ሐቀኝነት እየጠፋ ሄዷል። ይሁን እንጂ ሐቀኝነት ክርስቲያኖች ሊኖራቸው የሚገባ መሠረታዊ ባሕርይ ነው። ጳውሎስ ‘በነገር ሁሉ በሐቀኝነት ልንመላለስ’ እንወዳለን ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 13:18 NW) ከይሖዋ ምሥክሮች አንዷ የሆነችውን በኢጣሊያ ፋኤንዛ ከተማ የምትኖረው ቬልማም ያደረገችው ይኸንኑ ነበር።
ኢል ሬስቶ ዴል ካርሊኖ የተባለው ጋዜጣ በምትኖርበት ከተማ ውስጥ ከሚገኝ አንድ የገበያ አዳራሽ ውጭ ብዙ ገንዘብ የያዘ የገንዘብ ቦርሳ ባገኘች ጊዜ ለባለንብረቱ ይመለስ ዘንድ “ያለ ምንም ማመንታት” ለፖሊስ ወስዳ እንዳስረከበች ገልጿል።
የከተማው ከንቲባ ይህን ሲሰሙ ወዲያው ለቬልማ አጭር የምስጋና ደብዳቤ ላኩላት። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ለፈጸምሽው ሰናይ ምግባር በከተማችን ነዋሪዎች ስም ላመሰግንሽ እወዳለሁ። ስመ ጥሯ ከተማችን ፋኤንዛ ጥሩና ሐቀኛ ሰዎችን ትፈልጋለች።”
የምናከናውነው መልካም ድርጊት ለሰዎች የሚታይ ሆነም አልሆነ ሁልጊዜ ሐቀኞች ለመሆን መጣር ይኖርብናል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳስቡን “በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን” ለማድረግ እንጥራለን።—2 ቆሮንቶስ 8:21