ከፍተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት የተመዘገበበት ዓመት
ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ አላቸው። ይህን ሪፖርት የዘገበው የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ሲሆን በ1998 የመጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት ቀደም ሲል ከነበረው ዓመት በግማሽ ሚልዮን ከፍ ብሏል። በሙሉም ይሁን በከፊል በጠቅላላው ከ585, 000, 000 የሚበልጥ ብዛት ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሶች በመላው ዓለም ተሰራጭተዋል። “በእርግጥም ይህ የሚያበረታታ ነው” በማለት ሪፖርቱ ይገልጻል። “በዛሬው ጊዜ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የአምላክ ቃል ደርሷቸዋል።”
እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በእጃችን መኖሩ አንድ ነገር ሲሆን ማንበቡ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ጥናት እንዳመለከተው 90 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን ቢያንስ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ሲሆን ይህንኑ የሚያክል ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ የሥነ ምግባር ማስተማሪያ መጽሐፍ እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ምክር ለማግኘት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር የሚሉት 59 በመቶ ብቻ ናቸው። እንዲሁም 29 በመቶ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱስን “እምብዛም” ወይም “ጨርሶ” እንደማያውቁት አምነዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ከማተምና ከማሰራጨትም በተጨማሪ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ሰዎችን ያለ ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራሉ። በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ጥቅም በማግኘት ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲያሸንፉ እርዳታ ያገኛሉ፤ እንዲሁም ወደፊት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ስለሚኖረው ብሩህ ተስፋ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ይማራሉ።—ኢሳይያስ 48:17, 18፤ ማቴዎስ 6:9, 10
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(ከላይ ከግራ ወደ ቀኝ) በቦሊቪያ፣ በጋና፣ በስሪ ላንካ እና በእንግሊዝ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲደረግ