ውስጣዊ ውበት ዘላቂ ጥቅም አለው
አንድ ታማኝ አረጋዊ ክርስቲያን “አንድ ወጣት ውበትንና መልካም ሥነ ምግባርን በእኩል ዓይን ይመለከታቸዋል” በማለት ተናግሯል።
አዎን፣ ሰው ለውጪያዊ ውበት ተገቢ ያልሆነ ቦታ ሲሰጥ ቆይቷል። ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ለውስጣዊው ውበት የተሳሳተ ግምት እንዲሰጥ ያደርጋል። ይሁን እንጂ ውጪያዊው ውበታችን ምንም ይምሰል ምን ፈጣሪያችን ውስጣዊ ማንነታችንን ይመለከታል። በዚህ መንገድ ብስለት የታከለበት ሚዛናዊ ፍርድ በመስጠት ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል። አምላክ ራሱ “ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—1 ሳሙኤል 16:7
የእውነተኛ ሰብዓዊ ውበት ምንጭ አምላክ ነው። ቃሉም ስለ አንድ ሰው መልካም ምግባር በሚገልጽበት ጊዜ ለመንፈሳዊ ባሕርያት የላቀ ግምት ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ “ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 31:30) እርግጥ ነው፣ ውጪያዊ ውበት የአንድን ሰው ውስጣዊ መጥፎነት ሊጋርድ ይችላል። (አስቴር 1:10-12፤ ምሳሌ 11:22) ውጪያዊ ውበት ከጊዜ በኋላ አላፊ ቢሆንም ውስጣዊ ውበት ይኸውም ውስጣዊው ማንነት እያበበ ሊሄድ የሚችልና ዘላቂ ነው።
በመሆኑም ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ እምነትን፣ የዋህነትንና ራስን መግዛትን የመሳሰሉ ባሕርያትን ማፍራት እንዴት ያለ ብልህነት ነው! (ገላትያ 5:22, 23) በዚህ መንገድ ዘላቂ ጥቅም ያለውን ውስጣዊ ውበት ማግኘት እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 3:3, 4