ሁላችንም ምስጋና እንፈልጋለን
ለትንሿ ልጅ የቀኑ ውሎዋ አስደሳች ነበር። በሌሎች ጊዜያት ተግሳጽ ይሰጣት የነበረ ቢሆንም ዛሬ ግን ጨዋ ሆና ውላለች። ይሁን እንጂ በዚያን ዕለት ምሽት ካስተኟት በኋላ አልጋዋ ውስጥ ሆና ስታለቅስ እናትዋ ሰማቻት። ለምን እንደምታለቅስ ስትጠይቃት “ዛሬ ጨዋ ልጅ ሆኜ አልዋልኩም?” ስትል እያነባች እናቷን ጠየቀቻት።
እናትየው ይህን ስትሰማ በጣም ተሰማት። በትንሹም በትልቁም ልጅዋን ትቆጣት ነበር። ሆኖም ዛሬ ልጅዋ ሳትረብሽ ጨዋ ሆና ለመዋል ያደረገችውን ጥረት ብትመለከትም እናትየዋ አንድም የምስጋና ቃል አልተናገረቻትም።
ምስጋናና ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው ትናንሽ ልጆች ብቻ አይደሉም። ሁላችንም ምክርና እርማት እንደሚያስፈልገን ሁሉ ምስጋናም የዚያኑ ያህል ያስፈልገናል።
አንድ ሰው ከልቡ ሲያመሰግነን ምን ይሰማናል? ልባችን በደስታ አይሞላም? ቀኑን ደስ ብሎን እንድናሳልፍ አያደርገንም? ለእኛ የሚያስብ ሰው እንዳለ ሆኖ ይሰማናል። ያከናወንነው ነገር ትልቅ ዋጋ እንዳለው እንዲሰማን ከማድረጉም በላይ ወደፊትም ጠንክረን እንድንሠራ ያበረታታናል። ብዙውን ጊዜ ከልብ የመነጨ ምስጋና ወደ ሰጠን ሰው ለመቅረብ የምንገፋፋው በዚህ የተነሳ ነው።—ምሳሌ 15:23
ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎችን ማመስገን አስፈላጊ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ስለ መክሊቶቹ በሚናገረው ምሳሌ ላይ (ኢየሱስን የሚወክለው) የባሪያዎቹ ጌታ ሁለቱንም ታማኝ ባሪያዎች “መልካም፣ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ” በማለት ሞቅ ባለ ስሜት አመስግኗቸዋል። ምንኛ የሚያስደስቱ ቃላት ናቸው! በችሎታቸውም ሆነ በሥራቸው ውጤት በጣም የተለያዩ ቢሆኑም ሁለቱም እኩል ተመስግነዋል።—ማቴዎስ 25:19-23
ስለዚህ የትንሿን ልጅ እናት እናስታውስ። ሌሎችን ለማመስገን ቅር እስኪሰኙብን ድረስ አንጠብቅ። ከዚህ ይልቅ ሌሎችን ማመስገን የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች ልንፈልግ እንችላለን። እውነት ነው፣ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከልብ በመነጨ ስሜት ሌሎችን እንድናመሰግን የሚያደርጉን በቂ ምክንያቶች አሉን።