የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
‘ለተረሱት የእልቂቱ ሰለባዎች’ መታሰቢያ
በ2001 መጀመሪያ አካባቢ ሃይጋዝ የተባለ አንድ የ15 ዓመት የይሖዋ ምሥክር “የተረሱት የእልቂቱ ሰለባዎች” በሚል ጭብጥ በበርን፣ ስዊዘርላንድ በተዘጋጀ አንድ ኤግዚቢሽን ላይ ተገኝቶ ነበር። ኤግዚቢሽኑ የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ አገዛዝ ወቅት ስለደረሰባቸው ስደት የሚያሳይ ነበር። በጉብኝቱ መጨረሻ ላይ ሃይጋዝ እንዲህ ብሏል:- “የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ አገዛዝ ወቅት ስለደረሰባቸው ኢሰብዓዊ እንግልትና ሥቃይ ሰምቼ ነበር፤ ሆኖም በጊዜው የተፈጸመውን ሁኔታ በዝርዝር የሚያሳዩ እውነተኛ ሰነዶችንና ፎቶግራፎችን ስመለከት የመጀመሪያዬ ነው። በኤግዚቢሽኑ ላይ የቀረቡት ሥዕሎች፣ የዓይን ምሥክሮች ዘገባና የታሪክ ምሑራን የሰጡት አስተያየት በአእምሮዬና በልቤ ላይ በቀላሉ የማይፋቅ ስሜት አሳድሮብኛል።”
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሃይጋዝ በሚማርበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለክፍሉ ተማሪዎች አንድ ሪፖርት አጠናቅሮ እንዲያቀርብ ሲታዘዝ “የይሖዋ ምሥክሮች፣ የተረሱት የናዚዝም ሰለባዎች” የሚል ርዕስ መረጠ። መምህሩ በዚህ ርዕስ ሪፖርቱን እንዲያቀርብ ቢፈቅድለትም በይሖዋ ምሥክሮች ያልታተሙ ጽሑፎችንም በዋቢነት መጥቀስ እንዳለበት ነገረው። ሃይጋዝ በደስታ ተስማማ። “የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ አገዛዝ ወቅት ስለደረሰባቸው ስደት ከሚናገሩ አንዳንድ መጻሕፍት ላይ የተወሰኑ ሐሳቦችን ጠቀስኩ። እንዲሁም ‘የተረሱት የእልቂቱ ሰለባዎች’ ስለተባለው ኤግዚቢሽን በግል ያደረብኝን ስሜት አከልኩበት። ያዘጋጀሁት የ43 ገጽ ሪፖርት ሥዕላዊ መግለጫዎችንና ፎቶግራፎችንም ያካተተ ነበር።”
በኅዳር ወር 2002 ሃይጋዝ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ በተገኙበት ሪፖርቱን አቀረበ። ከሪፖርቱ በኋላ በነበረው የጥያቄና መልስ ውይይት ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለተመሠረተው እምነቱ ማብራሪያ ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ አግኝቷል። ከአድማጮቹ መካከል አንዲት ወጣት ይህን ርዕስ የመረጠበትን ምክንያት ስትጠይቀው ሃይጋዝ በርካታ የታሪክ መጽሐፍት የይሖዋ ምሥክሮች ስለደረሰባቸው ሁኔታ ስለማይጠቅሱና ምሥክሮቹ ለክርስቲያናዊ እምነታቸው እንዴት በድፍረት እንደቆሙ ሰዎች እንዲያውቁ ስለሚፈልግ እንደሆነ ነገራት። ያቀረበው ሪፖርት ምን ውጤት አስገኘ?
ሃይጋዝ እንዲህ ይላል:- “የትምህርት ቤት ጓደኞቼ በጣም ተደነቁ። የይሖዋ ምሥክሮች በቡድን ደረጃ ከፍተኛ ስደት እንደደረሰባቸው አያውቁም ነበር። እንዲሁም በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የታሠሩት የይሖዋ ምሥክሮች ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ባለ ሦስት ማዕዘን ጨርቅ በልብሳቸው ላይ ለምልክት ይደረግ እንደነበር ብዙዎቹ አያውቁም ነበር።”
ከዚያ በኋላ ሃይጋዝ ደም ስለ መውሰድ፣ ስለ አልኮል መጠጥና ስለ ሥነ ምግባር የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሰረተ አቋም በሚመለከት ከክፍል ጓደኞቹ ጋር ለመወያየት የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎች አግኝቷል። “ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ መካከል አንዳቸውም አላሾፉብኝም” ብሏል። ከዚህም በላይ ያዘጋጀው ሪፖርት በትምህርት ቤቱ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የተቀመጠ ሲሆን ይህም የይሖዋ ምሥክሮች የወሰዱት የድፍረት አቋም ተረስቶ እንዳይቀር ለማድረግ ያስችላል።