ከፍርሃት ነጻ በሆነ ዓለም ውስጥ ለመኖር ትናፍቃለህ?
“‘በማንኛውም ሰዓት አለምንም ማስጠንቀቂያ ምንነቱ ያልታወቀ . . . አደጋ’ ሊደርስብን እንደሚችል በማሰብ ‘ሁልጊዜ በከፍተኛ ስጋትና . . . በረዳት የለሽነት ስሜት ተውጠን’ እንኖራለን።”
ባለፈው ዓመት ኒውስዊክ በተሰኘው መጽሔት ላይ ወጥቶ የነበረው ከላይ የሰፈረው ሐሳብ ሁከት በነገሠበት በዚህ ዓለም ውስጥ የሚኖሩትን የብዙ ሰዎች ስሜት የሚያስተጋባ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመናችን እንደዚህ ያለው ስሜት እየተባባሰ እንደሚሄድ ተናግሮ ነበር። በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች የሚጨነቁበትና የሚታወኩበት እንዲሁም በፍርሃትና በዓለም ላይ ምን ይመጣ ይሆን እያሉ በመጠባበቅ የሚዝሉበት ጊዜ እንደሚመጣ አስቀድሞ ገልጿል። እኛ ግን በፍርሃት ልንርድ ወይም ረዳት እንደሌለን ሊሰማን አይገባም። ምክንያቱም ኢየሱስ አክሎ “እናንተም እነዚህ ነገሮች መፈጸም ሲጀምሩ፣ መዳናችሁ ስለተቃረበ፣ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ወደ ላይ ቀና አድርጉ” ብሎናል።—ሉቃስ 21:25-28
ይሖዋ አምላክ ሕዝቡን ካዳናቸው በኋላ በምድር ላይ ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖራቸው ሲገልጽ “ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ መኖሪያ፣ በሚያስተማምን ቤት፣ ጸጥ ባለም ስፍራ ዐርፎ ይኖራል” ብሏል። (ኢሳይያስ 32:18) በነቢዩ ሚክያስ በኩል ደግሞ “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም” ብሏል።—ሚክያስ 4:4
ይህ በዛሬው ጊዜ ካለው ሕይወት ምንኛ የተለየ ነው! የሰው ዘር ምንነቱ ያልታወቀ አደጋ ሊደርስበት እንደሚችል በማሰብ አይፈራም። ዘወትር በስጋት መኖሩና በረዳት የለሽነት ስሜት መዋጡ ይቀርና ለዘላለም በሰላምና በደስታ ይኖራል።