ታስታውሳለህ?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-
• በዛሬው ጊዜ ክፋት እንዲባባስ ያደረጉት አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
አንደኛው ምክንያት ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ መሆኑ ነው። (ዘፍጥረት 8:21) ሌላው ደግሞ ብዙ ሰዎች ስለ አምላክ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀት ስለሌላቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ የክፋት ምንጭ የሆነው ሰይጣን በሰዎች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባቱ ክፋት እንዲባባስ አድርጓል።—1/1 ገጽ 4-6
• በወቅቱ የተነገረ ቃል የሚያስገኛቸው መልካም ውጤቶች ምንድን ናቸው? (ምሳሌ 12:25)
በተቀባዩ ዘንድ በራስ የመተማመን ስሜት ይፈጥራል፤ እንዲሁም ለሥራ ሊያነሳሳ፣ ሊያበረታታና የመቀራረብ ስሜት እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ አመስጋኞች መሆን የሌሎች ሰዎች መልካም ጎን እንዲታየን ያደርጋል።—1/1 ገጽ 16-17
• በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ምን ነገሮች ነበሩ?
ሕጉ የተጻፈባቸው ሁለት የድንጋይ ጽላቶችና ጥቂት መና ይገኝበት ነበር። ከቆሬ ዓመጽ በኋላ ደግሞ የአሮን በትር በዚያን ጊዜ ለነበረው ትውልድ ምሥክር እንዲሆን በታቦቱ ውስጥ ተቀምጦ ነበር። (ዕብራውያን 9:4) የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ከመወሰኑ በፊት የአሮን በትርና መናው ከቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ወጥተው ሊሆን ይችላል።—1/15 ገጽ 31
• በነህምያ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ለቤተ መቅደሱ እንጨት ማቅረብ የነበረባቸው ለምንድን ነው?
የሙሴ ሕግ ሕዝቡ የእንጨት መሥዋዕት እንዲያቀርብ አያዝም። ሆኖም በነህምያ ዘመን በመሠዊያው ላይ የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች ለማቃጠል በቋሚነት እንጨት ማቅረብ ያስፈልግ ነበር።—2/1 ገጽ 11
• ሙራቶሪያን ፍራግመንት ምንድን ነው?
የላቲኑ ጥንታዊ ቅጂ ክፍል ነው። የመጀመሪያው ጽሑፍ በግሪክኛ ተጽፎ የተጠናቀቀው በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ማብቂያ አካባቢ ነው። ጽሑፉ በመንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፉ የሚታመኑትን በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን ጥንታዊ መጻሕፍት ዝርዝር ከመያዙም በላይ መጽሐፎቹንና ጸሐፊዎቹን የሚመለከት ትንታኔም ይሰጣል።—2/15 ገጽ 13-14
• የፋርስ ንግሥት የሆነችው አስጢን ንጉሡ ዘንድ ለመሄድ አሻፈረኝ ያለችው ለምን ነበር? (አስቴር 1:10-12)
መጽሐፍ ቅዱስ ለምን እንዲህ እንዳደረገች በግልጽ አይነግረንም። ሆኖም አንዳንድ ምሑራን ንግሥቲቱ ለመታዘዝ ፈቃደኛ ያልነበረችው በሰከሩት የንጉሡ እንግዶች ፊት በመቅረብ ራሷን ማዋረድ ስላልፈለገች ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ። አሊያም ደግሞ ማራኪ ውጪያዊ ውበት ያላት ይህቺ ንግሥት የታዛዥነት ባሕርይ ይጎድላት ይሆናል። በዚህ ምክንያት በፋርስ ግዛት ለሚኖሩ ሌሎች ሚስቶች መጥፎ ምሳሌ ልትሆን ትችላለች።—3/1 ገጽ 9
• ቤዛው ነጻ የሚያወጣው እንዴት ነው?
የኢየሱስ መሥዋዕት ከወረስነው ኃጢአትና ወደ ሞት ከሚመሩት የኃጢአት ውጤቶች ነጻ ያወጣናል። (ሮሜ 6:23) ይህ መሥዋዕት እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከሕሊና ወቀሳ ነጻ ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም በቤዛው ላይ ያለን እምነት በአምላክ ፊት ያለንን አቋም በተመለከተ ከመስጋት ያሳርፈናል። (1 ዮሐንስ 2:1)—3/15 ገጽ 8
• ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል ከሚለው ሕግ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? (ዘፀአት 23:19)
ጠቦትን በእናቱ ወተት መቀቀል፣ ዝናብ እንዲዘንብ በሚቀርብ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የሚደረግ አረማዊ ልማድ ሊሆን ይችላል። (ዘሌዋውያን 20:23) አምላክ የእናት ጡት ወተትን ያዘጋጀው ጠቦቱ እንዲመገበውና እንዲያድግበት ነው። ጠቦቱን በእናቱ ወተት መቀቀል አምላክ በወላጆችና በልጆች መካከል ለፈጠረው ዝምድና ንቀት ማሳየት ነው። ሕጉ ይህንን መከልከሉ የአምላክን ርኅራኄ ያሳያል።—4/1 ገጽ 31