“የገሊላ ምድር ጌጥ”
ኢየሱስ ካደገባት ከናዝሬት 6.5 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቃ የምትገኝ ቢሆንም ስሟ በወንጌሎች ውስጥ ያልተጠቀሰ አንዲት ከተማ አለች። የአንደኛው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ታዋቂው ፍላቪየስ ጆሴፈስ ይህችን ከተማ “የገሊላ ምድር ጌጥ” ሲል አወድሷታል። እርሷም ሴፎረስ ናት። ስለዚህች ከተማ ምን የሚታወቅ ነገር አለ?
ታላቁ ሄሮድስ በ1 ከክርስቶስ ልደት በፊት አካባቢ ከሞተ በኋላ የሴፎረስ ነዋሪዎች በሮም ላይ በማመጻቸው ምክንያት ከተማቸው ተደመሰሰች። የሄሮድስ ልጅ የነበረው አንቲጳስ ገሊላንና ፔሪያን መግዛት ሲጀምር በሴፎረስ ፍርስራሽ ላይ አዲሷን ዋና ከተማ ገነባ። ከተማዋ ዳግም የተገነባችው በግሪካውያንና በሮማውያን የዕደ ጥበብ ንድፍ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ነዋሪዎቿ አይሁዳውያን ነበሩ። እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ቤቲ አባባል ከሆነ አንቲጳስ ጥብርያዶስን በ21 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ ገንብቶ ዋና ከተማዋን ከሴፎረስ ወደ ጥብርያዶስ እስካዛወረበት ጊዜ ድርስ ሴፎረስ “ገሊላንና ፔሪያን ለሚቆጣጠረው መንግሥት አስተዳደራዊ ማዕከል ነበረች።” በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ይኖር የነበረው በዚህች ከተማ አቅራቢያ ነበር።
በሴፎረስ ከተማ ቁፋሮ ያካሄዱት ፕሮፌሰር ጄምስ ስትሬንጅ እንደተናገሩት ከተማዋ በአንድ ወቅት ቤተ መዛግብት፣ ግምጃ ቤቶች፣ የጦር መሣሪያ ማስቀመጫ መጋዘኖች፣ ባንክ ቤቶች፣ ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎች የነበሯት ሲሆን በገበያ ቦታዎቿ ላይም የሸክላ ዕቃዎች፣ መስተዋት፣ ከብረት የተሠሩ ዕቃዎች፣ ጌጣጌጦችና የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ይሸጡ ነበር። ሸማኔዎችና ልብስ ነጋዴዎች ከመኖራቸውም በተጨማሪ የቅርጫቶች፣ ከእንጨት የተሠሩ የቤት ዕቃዎች፣ የሽቱና የመሳሰሉት የንግድ ዕቃዎች ግብይት ይካሄድ ነበር። በዚያን ወቅት በከተማዋ የሚኖረው ሕዝብ ብዛት ከ8,000 እስከ 12,000 ይደርስ እንደነበር ይገመታል።
ታዲያ ኢየሱስ ከናዝሬት የአንድ ሰዓት ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደዚች ትልቅ ከተማ ሄዶ ያውቃል? የወንጌል ዘገባዎች መልሱን አይሰጡንም። ሆኖም ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ “ከናዝሬት ተነስቶ በገሊላ ወደምትገኘው ቃና የሚወስደው አንደኛው መንገድ በሴፎረስ በኩል እንደሚያልፍ” ተናግሯል። (ዮሐንስ 2:1፤ 4:46) ናዝሬት ላይ ሆኖ፣ ከሸለቆው ወለል 120 ሜትር ከፍታ ያለውን የሴፎረስ ኮረብታ ማየት የሚቻል ሲሆን አንዳንዶች ኢየሱስ “በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም” ብሎ ምሳሌ ሲሰጥ ይህችን ከተማ በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል ብለው ያምናሉ።—ማቴዎስ 5:14
ኢየሩሳሌም በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ስትጠፋ ሴፎረስ የአይሁዳውያን ዋና ከተማ ሆነች። እንዲሁም የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማለትም የሳንሄድሪን ሸንጎ መቀመጫ እና ለተወሰነ ጊዜም የአይሁድ ምሁራን የትምህርት ማዕከል ነበረች።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የገሊላ ባሕር
ገሊላ
ቃና
ጥብርያዶስ
ሴፎረስ
ናዝሬት
ፔሪያ
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሸክላ ዕቃዎች:- Excavated by Wohl Archaeological Museum, Herodian Quarter, Jewish Quarter. Owned by Company for the Reconstruction of the Jewish Quarter in the Old City of Jerusalem, Ltd