መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
በሃይማኖት ተስፋ ቆርጣ የነበረች አንዲት ሴት በአሁኑ ወቅት አብዛኛውን ጊዜዋን ሌሎች ስለ አምላክ እንዲማሩ በመርዳት የምታሳልፈው ለምንድን ነው? ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን ስፖርቶች ይወድ የነበረ ሰው ሰላም ወዳድ እንዲሆን ያነሳሳው ምንድን ነው? አደገኛ ዕፆችን የሚወስድ እንዲሁም ጠጪና ተደባዳቢ የነበረ ሰው እነዚህን ልማዶቹን አሸንፎ አኗኗሩን ማስተካከል የቻለው እንዴት ነው? እስቲ እነዚህ ግለሰቦች የሚሉትን እንስማ።
አጭር የሕይወት ታሪክ
ስም፦ ፐነሎፒ ቶፕሊቼስኩ
ዕድሜ፦ 40
አገር፦ አውስትራሊያ
የኋላ ታሪክ፦ በሃይማኖት ተስፋ ቆርጣ የነበረች
የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በሲድኒ፣ አውስትራሊያ ቢሆንም የሁለት ዓመት ልጅ እያለሁ ቤተሰቦቼ ወደ ኒው ጊኒ ሄዱ። በራባውል ለሁለት ዓመት ገደማ ከኖርን በኋላ ወደ ቡገንቨል ተዛወርን፤ በዚያም ለስምንት ዓመታት ቆይተናል። በዚያ ወቅት በኒው ጊኒ ቴሌቪዥን ስላልነበረ እኔና ወንድሜ አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናሳልፈው ከቤት ውጭ ነበር፤ ባሕር ውስጥ እንዋኝ እንዲሁም ድንኳን ተክለን ውጭ እናድር ነበር።
አሥር ዓመት ገደማ ሲሆነኝ ስለ ሃይማኖት የማወቅ ፍላጎት አደረብኝ። እማማ ካቶሊክ ስለነበረች በአካባቢያችን ከሚኖሩት መነኮሳት አንዷ ጋ ሄጄ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንድማር ሐሳብ አቀረበችልኝ። እኔም የካቶሊክን እምነት በመቀበል በአሥር ዓመቴ ተጠመቅሁ።
ከጊዜ በኋላ ወደ አውስትራሊያ ተመለስን፤ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ስሆን ስለ ሃይማኖት የተማርኳቸውን ነገሮች መጠራጠር ጀመርኩ። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበርኩበት ወቅት ስለ ጥንታዊ ታሪኮች ተማርኩ፤ እኔና አባቴ ስለ ሃይማኖት አመጣጥ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት ዘገባዎች ረዘም ያሉ ውይይቶች እናደርግ የነበረ ሲሆን እነዚህ ዘገባዎች ተራ አፈ ታሪክ እንደሆኑ ይሰማን ነበር። የኋላ ኋላ የካቶሊክን ሃይማኖት መከተል አቆምኩ።
አሥራ ስድስት ዓመት ሲሆነኝ ወላጆቼ ተለያዩ። እማማ ሁኔታውን መቀበል ከብዷት ነበር፤ እኔም ውሎ አድሮ ከአባቴና ከእጮኛው ጋር መኖር ጀመርኩ። ወንድሜ ከእናቴ ጋር መኖሩን የቀጠለ ሲሆን ወደ ሌላ የአውስትራሊያ ግዛት ተዛወሩ። በዚህ ወቅት በብቸኝነት ስሜት ተዋጥኩ። ከእናቴ ጋር የነበረኝን ግንኙነት እንደገና ለማደስ ሁለት ዓመት ወሰደብኝ። መጠጣት፣ አደገኛ ዕፆችን መውሰድ እንዲሁም ወደ ጭፈራ ቤቶች መሄድ ጀመርኩ። ትምህርቴን አቋርጬ ሥራ ያዝኩ። በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ በነበርኩበት ወቅት ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት በመምራት ዕድሜዬን በከንቱ አባከንኩት።
ሃያ አምስት ዓመት ሲሆነኝ እንደገና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማሰብ ጀመርኩ። ሌላ ቦታ ተቀጥሬ መሥራት ስጀምር ሊና ከተባለች ደስ የምትል ወጣት ጋር ተዋወቅሁ፤ ሊና አለቃዋ ያመናጭቃት የነበረ ቢሆንም እሷ ግን ሁልጊዜ በትሕትና ታናግረው ነበር። አለቃዋ እንዲህ ሲያደርግ እሷ በትሕትና የምትመልስለት ለምን እንደሆነ ሊናን ስጠይቃት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናች እንደሆነና የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሕይወቷ ተግባራዊ ለማድረግ እንደምትጥር ነገረችኝ። ሊና መጽሐፍ ቅዱስን ልታስጠናኝ እንደምትችል ገለጸችልኝ። እንዲህ ስትለኝ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የምታውቀውን ነገር ሁሉ በአንድ ሰዓት ውስጥ ልታስጠናኝ እንደምትችል ተሰምቶኝ ነበር። የዚያን ቀን ማታ ከሊና ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በነበሩኝ ጥያቄዎች ላይ ለሦስት ሰዓት ያህል ተወያየን። ለጥያቄዎቼ የሰጠችኝ መልስ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተደገፈ መሆኑ በጣም አስገረመኝ።
የዚያን ዕለት ማታ ከሊና ጋር ከተለያየን በኋላ መኪናዬን እየነዳሁ ወደ ቤቴ ስመለስ አምላክ ስለ እሱ የሚገልጸውን እውነት ቀደም ብዬ እንዳውቅ ስላላደረገኝ ተናድጄበት እንደነበረ አስታውሳለሁ። የይሖዋ ምሥክሮች በሥነ ምግባር ረገድ ንጹሖች እንደሆኑ አውቃለሁ፤ እኔ ግን ከዚህ በኋላ መጥፎ ልማዶቼን ማሸነፍ እንደማልችል ተሰማኝ። ከዚህም ሌላ መቼም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚያደርጉት ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ መስበክ እንደማልችል አስብ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን የቀጠልኩ ቢሆንም ዓላማዬ ከትምህርታቸው ውስጥ ስህተት ለማግኘትና ያንን ሰበብ አድርጌ ጥናቴን ለማቆም ነበር። ውሎ አድሮ ግን እንዲህ ያለውን ሰበብ ማግኘት እንደማልችል ተገነዘብኩ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ይበልጥ ባወቅሁ መጠን የዚያኑ ያህል ሕሊናዬ ይረብሸኝ ነበር። ከሕሊና ወቀሳ ለመገላገል ስል አደገኛ ዕፆችን መውሰድ አቆምኩ። ይሁንና ለተወሰነ ጊዜ ያህል ወደ ሌላ አገር ሄጄ በነበርኩበት ወቅት እንደገና ወደ ጭፈራ ቤቶች መሄድና መጠጣት ጀመርኩ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር በማደርገው ጥረት የተወሰነ ማሻሻያ ባደረግሁ ቁጥር የቀድሞ ልማዶቼ እንደገና እያገረሹብኝ እቸገር ነበር። በሐፍረት ተውጬ ወደ ይሖዋ ብጸልይም የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር።
ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ስለፈጸመው ኃጢአትና ይሖዋ እንዴት ምሕረት እንዳደረገላቸው ማወቄ ይሰማኝ የነበረውን መጥፎ ስሜት ለማሸነፍ ረድቶኛል። ዳዊት ምክር ሲሰጠው ድርጊቱን ለማስተባበል ከመሞከር ይልቅ ስህተቱን አምኗል። እንዲሁም የተሰጠውን ተግሣጽ በትሕትና ተቀብሏል። (2 ሳሙኤል 12:1-13) እኔም ስህተት በምሠራበት ጊዜ ይህንን ታሪክ ማስታወሴ በድርጊቴ መጸጸቴን ለይሖዋ ለመንገር ቀላል እንዲሆንልኝ ረድቶኛል። በፈተና ከተሸነፍኩ በኋላ ሳይሆን አስቀድሜ ለመጸለይ ቆረጥኩ፤ ይህም ትልቅ ለውጥ አምጥቶልኛል።
ያገኘሁት ጥቅም፦ በቀላሉ የምቆጣ ሰው ነበርኩ። ሆኖም በኤፌሶን 4:29-31 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እንደ “ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት” ያሉትን ባሕርያት ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል። እያደር ቁጣዬን መቆጣጠር የቻልኩ ሲሆን ይህ ደግሞ አንደበቴንም መግታት እንድችል አድርጎኛል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ “ቃላችሁ አዎ ከሆነ አዎ ይሁን” በማለት የሰጠው ምክር ከማወላወል ይልቅ ቆራጥ እርምጃ እንድወስድ አስችሎኛል።—ማቴዎስ 5:37
እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በማጥናቴ መጀመሪያ ላይ ብትቃወመኝም የኋላ ኋላ ግን በእኔ እንደምትኮራ ነገረችኝ። እንዲያውም “እንደዚህ ዓይነት ሰው እንድትሆኚ የረዳሽ ስለ ይሖዋ የተማርሽው ነገር እንጂ አስተዳደግሽ እንዳልሆነ አውቃለሁ” ብላኛለች። ከእናቴ አፍ ይህን መስማቴ በጣም አስደስቶኛል።
በአሁኑ ወቅት ሕይወቴ ትርጉም ያለው እንደሆነ ይሰማኛል። እኔና ባለቤቴ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በሙሉ ጊዜያችን መጽሐፍ ቅዱስን ለሰዎች ስናስተምር ቆይተናል። አሁን ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ የምሰብክ ሲሆን ይህ ሥራ እስከ ዛሬ ካከናወንኳቸው ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ እርካታ የሚያስገኝ እንደሆነ ይሰማኛል።
አጭር የሕይወት ታሪክ
ስም፦ ዴኒስ ቡሲገን
ዕድሜ፦ 30
አገር፦ ሩሲያ
የኋላ ታሪክ፦ ካራቴ ይወድ የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በፐርም ከተማ ሲሆን ያደግኩት ደግሞ ኢቫኖቫ በሚባል የሩሲያ ግዛት ውስጥ በምትገኘውና 40,000 ነዋሪዎች ባሏት በፈርመኖፍ ነው። ፈርመኖፍ በርካታ የሚያምሩ ዛፎች ያሏት ውብ ከተማ ናት፤ በመጸው ወቅት የዛፎቹ ቅጠሎች ወደ ቢጫና ቀይ ቀለም ይቀየራሉ። በ1980ዎቹና በ1990ዎቹ ዓመታት በከተማዋ ውስጥ ወንጀል በጣም ተስፋፍቶ ነበር። የቤተሰባችን ገቢ አነስተኛ በመሆኑ ኑሯችን በጣም ዝቅተኛ ነበር። ከወላጆቼና ከታናሽ ወንድሜ ጋር ሆነን አንድ መኝታ ክፍል ባለው አፓርታማ ውስጥ ተጨናንቀን እንኖር ነበር።
ሰባት ዓመት ሲሆነኝ ካራቴ መማር ጀመርኩ። ይህንን ስፖርት በጣም ስለምወደው ሕይወቴ በሙሉ በዚያ ላይ ያተኮረ ነበር። ትርፍ ጊዜዬን በሙሉ የማሳልፈው በጂምናዝየም ውስጥ በመሆኑ ጓደኞቼ ሁሉ ስፖርተኞች ነበሩ። አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ በካራቴ ስፖርት ቀይ ቀበቶ ያገኘሁ ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላም ቡኒ ቀበቶ አገኘሁ። በሩሲያ እንዲሁም በአውሮፓና በእስያ የሻምፕዮና ውድድሮች ላይ የሚካፈል የካራቴ ቡድን አባል ነበርኩ። የወደፊቱ ጊዜ ብሩኅ ይመስል ነበር፤ ሆኖም በ17 ዓመቴ መላ ሕይወቴን የሚለውጥ ነገር አጋጠመኝ።
እኔና አንዳንድ ጓደኞቼ ወንጀል በመፈጸማችን ተይዘን ታሰርን። እኔ የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ። የእስር ቤት ሕይወት በጣም ከባድ ነው። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ማግኘት የቻልኩት በእስር ቤት ነበር። ወኅኒ ቤት እያለሁ የዘፍጥረትና የመዝሙር መጻሕፍትን እንዲሁም አዲስ ኪዳንን አነበብኩ። አባታችን ሆይ የሚባለውን ጸሎት በቃሌ ያጠናሁት ሲሆን ሁልጊዜ ማታ ማታ ከመተኛቴ በፊት ይህን ጸሎት እደግመው ነበር፤ ይህን ማድረጌ በሆነ መልኩ እንደሚጠቅመኝ ይሰማኝ ነበር።
በ2000 ከእስር ቤት ተለቀቅሁ፤ ሆኖም በሕይወቴ ውስጥ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገብቶኝ እንዲሁም የመኖር ትርጉሙ ጠፍቶብኝ ነበር። በመሆኑም አደገኛ ዕፆች መውሰድ ጀመርኩ፤ በዚሁ ጊዜ እናቴን በሞት አጣሁ። እናቴን ከማንም በላይ እወዳት ስለነበር ሐዘኑን መቋቋም በጣም ከበደኝ። ከዚህም ሌላ ከዕፅ ሱሴ ለመላቀቅ ከፍተኛ ትግል ማድረግ ጠይቆብኝ ነበር፤ ሆኖም ከዚህ ሱስ በመላቀቅ እንደገና ወደ ጂምናዚየም መሄድ ጀመርኩ። እንዲሁም ወደ ኢቫኖቫ ከተማ በመሄድ በአንድ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ውስጥ ሥራ አገኘሁ። የመደብሩ ረዳት ተቆጣጣሪ የይሖዋ ምሥክር ነበረች። ይህች ሴት መሠረታዊ የሆኑ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ካብራራችልኝ በኋላ ሌላ የይሖዋ ምሥክር በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠናኝ ዝግጅት አደረገች።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ወቅት አምላክ ምድርን ገነት የማድረግ ዓላማ እንዳለው ስገነዘብ ልቤ በጥልቅ ተነካ፤ እኔም በዚያ ለመኖር የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ፈለግኩ። ይሖዋ አምላክ፣ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ እንዲመሩባቸው የሚጠብቅባቸው ላቅ ያሉ መሥፈርቶች እንዳሉ ተገነዘብኩ። አብዛኛውን ሕይወቴን ያሳለፍኩት ስለ ራሴ ብቻ በማሰብ ነበር። ይሁንና ይሖዋ ለሌሎችም እንዳስብ የሚፈልግ መሆኑን ተማርኩ፤ እንዲሁም ደግነትንና ሰላም ወዳድ መሆንን ጨምሮ ሌሎች በወቅቱ ያልነበሩኝን ባሕርያት እንዳዳብር እንደሚጠብቅብኝ አወቅሁ።
ይሖዋ ለኃጢአቴ ሲል ልጁን መሥዋዕት አድርጎ መስጠቱን ጨምሮ ስላደረገልኝ ሌሎች በርካታ ነገሮች በጥልቅ ማሰቤ አምላክ ላሳየኝ ፍቅር አድናቆት እንዲያድርብኝ አደረገ፤ ይህም በሕይወቴ ውስጥ ለውጦች እንዳደርግ አነሳሳኝ። ለምሳሌ መዝሙር 11:5ን ሳነብ ይሖዋ ዓመፅን እንደሚጠላ አወቅሁ። በመሆኑም ዓመፅና ጥላቻ የሚንጸባረቅባቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን መመልከቴን አቆምኩ። እንዲሁም ከብዙ ትግል በኋላ፣ ዓመፅን የሚያበረታቱ ስፖርቶችን አቆምኩ። በአንደኛ ቆሮንቶስ 15:33 ላይ የሚገኘው መመሪያ ደግሞ ጓደኞቼ በእኔ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ እንዳስተውል ረዳኝ። ወኅኒ ቤት መውረዴ በራሱ፣ ይህ መመሪያ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። በመሆኑም ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን ስፖርቶች ከሚወዱ ሰዎች ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማቆም ወሰንኩ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰቤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ ሐቀኛ ሰው እንድሆን ረድቶኛል። ለምሳሌ በዕብራውያን 13:5 ላይ የሚገኘው ሐሳብ፣ ባለኝ የመርካትንና የገንዘብ ፍቅርን የማስወገድን አስፈላጊነት እንድገነዘብ አድርጎኛል። ይህንን ምክር በተግባር ማዋሌ ከውሸትና ከስርቆት እንድርቅ አስችሎኛል።
በሕይወቴ ውስጥ ለጓደኝነት ትልቅ ቦታ እሰጣለሁ። ከዚህ ቀደም ስግብግብነት ወይም ሌሎችን መፍራት ለጓደኝነት መፍረስ ምክንያት ሲሆን ተመልክቻለሁ። የይሖዋ ምሥክሮች ፍጹም ባይሆኑም የአምላክን መሥፈርቶች እንደሚያከብሩና ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት የእሱን ምክር በተግባር ለማዋል ልባዊ ጥረት እንደሚያደርጉ ማስተዋል ችያለሁ። በአሁኑ ወቅት ከአንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር እውነተኛ ወዳጅነት መሥርቻለሁ።
የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ባላደርግ ኖሮ ሕይወቴ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ይከብደኛል። ምናልባትም እንደገና ወኅኒ ቤት እወርድ አሊያም ለብዙ ሰዎች ሥቃይና መከራ ምክንያት እሆን ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ደስ የምትል ሚስትና ሁለት ልጆች አሉኝ፤ በቤተሰብ ሆነን ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን እንዲያውቁ መርዳታችን እውነተኛ ደስታ አስገኝቶልናል።
አጭር የሕይወት ታሪክ
ስም፦ ዡዜ ካርሎስ ፐሬራ ዳ ሲልቫ
ዕድሜ፦ 31
አገር፦ ብራዚል
የኋላ ታሪክ፦ ተደባዳቢ የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት ሳኦ ፓውሎ ውስጥ በሚገኘው አሜሪካና በተባለ ከተማ ውስጥ ትርኪምርኪ በሆነ ሰፈር ነው። ንጹሕ የመጠጥ ውኃ የማናገኝ ሲሆን አካባቢያችንም ለጤና ጎጂ የሆኑ ነገሮች የሞሉበት ነበር። ሰፈራችን የሚታወቀው በዓመፅና በወንጀል ነበር።
እያደግሁ ስሄድ ዓመፀኛና ጠብ አጫሪ ሆንኩ። ተደባዳቢ በመሆኔ ስለምታወቅ በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ይፈሩኝ ነበር። አለባበሴና አጠቃላይ ገጽታዬ አደገኛ ዱርዬ እንደሆንኩ ያስታውቅ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ራሴን እስክስት ድረስ ጥንብዝ ብዬ እሰክር እንዲሁም ልክ እንደ ወንድሞቼ አደገኛ ዕፆችን እወስድ ነበር። እንዲያውም አንዱ ወንድሜ ሕይወቱ ያለፈው አደገኛ ዕፆችን በብዛት በመውሰዱ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስገናኝ አምላክ ወደፊት መላዋን ምድር ገነት እንደሚያደርጋት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳዩኝ። (ሉቃስ 23:42, 43፤ ራእይ 21:3, 4) ከዚህም በተጨማሪ ሙታን ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ እንዲሁም አምላክ መጥፎ ሰዎችን በገሃነም እሳት እንደማያቃጥል ተማርኩ። (መክብብ 9:5, 6) ይህን ማወቄ ትልቅ እፎይታ አመጣልኝ። ስለ አምላክ የተማርኩት ነገር በአኗኗሬ ላይ ለውጥ እንዳደርግ አነሳሳኝ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን ለውጥ ማድረግ ይኸውም አደገኛ ዕፆችን የመውሰድና የመስከር እንዲሁም የመደባደብና ጸያፍ ቃላት የመናገር ልማዴን መተው ቀላል አልነበረም።
በአንደኛ ቆሮንቶስ 6:9-11 ላይ የሚገኘው ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈው ሐሳብ ትልቅ ማበረታቻ ሆኖልኛል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በአንድ ወቅት እኔ የነበሩኝ ዓይነት መጥፎ ልማዶች እንደነበሯቸው ጥቅሱ ይገልጻል። ሆኖም ይኸው ጥቅስ አክሎ እንዲህ ይላል፦ “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ። ሆኖም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣ ተቀድሳችኋል እንዲሁም ጻድቃን ተብላችሁ ተጠርታችኋል።” ይህ ጥቅስ እኔም አምላክን ለማስደሰት አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ እንደምችል ተስፋ ሰጠኝ።
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ስጀምር አኗኗራቸው እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ማስተዋል ቻልኩ። ቀደም ሲል ዓመፀኛና ጠበኛ እንደነበርኩ ቢያውቁም በፍቅርና ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ተቀበሉኝ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንቼ በአኗኗሬ ላይ ለውጥ ባላደርግ ኖሮ እስካሁን በሕይወት አልኖርም ነበር። አሁን ግን ከወንድሞቼ መካከል አንደኛው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና እንዲሁም ከዕፅ ሱስ እንዲላቀቅ መርዳት ችያለሁ፤ ይህም ከፍተኛ ደስታ አምጥቶልኛል። ሌሎች ዘመዶቼም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ አበረታትቻቸዋለሁ። ስለ እኛ በጥልቅ የሚያስበውን አምላካችንን ለማገልገል ሕይወቴን መወሰን በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ!
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በፈተና ከተሸነፍኩ በኋላ ሳይሆን አስቀድሜ ለመጸለይ ቆረጥኩ፤ ይህም ትልቅ ለውጥ አምጥቶልኛል”