የአንባቢያን ጥያቄዎች
ሕዝቅኤል 18:20 “ልጅ በአባቱ ኀጢአት አይቀጣም” ሲል ዘፀአት 20:5 ደግሞ ይሖዋ ‘ልጆችን ከአባቶቻቸው ኀጢአት የተነሣ እንደሚቀጣ’ ይናገራል። ታዲያ እነዚህ ጥቅሶች እርስ በርሳቸው አይጋጩም?
እነዚህ ጥቅሶች እርስ በርሳቸው አይጋጩም። የመጀመሪያው ጥቅስ እያንዳንዱ ሰው በግለሰብ ደረጃ እንደሚጠየቅ ያጎላል፤ በሁለተኛው ጥቅስ ላይ የተገለጸው እውነታ ደግሞ አንድ ሰው የሚሠራው ኃጢአት የሚያስከትለው መዘዝ ዘሮቹንም ሊነካ እንደሚችል ያሳያል።
በሕዝቅኤል ምዕራፍ 18 ላይ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ጥቅሱ የሚያጎላው እያንዳንዱ ሰው በግለሰብ ደረጃ ተጠያቂ እንደሚሆን ነው። ቁጥር 4 “ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች” ይላል። “በቅንነትና በትክክል የሚሠራ ጻድቅ” ሰውስ ምን ይሆናል? እንዲህ ዓይነቱ ሰው “ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል።” (ሕዝ. 18:5, 9) በመሆኑም ኃላፊነት መውሰድ የሚችልበት ዕድሜ ላይ የደረሰ እያንዳንዱ ግለሰብ ‘የሚፈረድበት እንደየሥራው’ ነው።—ሕዝ. 18:30
ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በምሳሌ ለማስረዳት ቆሬ የተባለው ሌዋዊ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። እስራኤላውያን በምድረ በዳ ይጓዙ በነበረበት ወቅት ቆሬ በተሰጠው የአገልግሎት መብት ባለመርካቱ በክህነት አገልግሎት ለመካፈል ፈለገ። ይህን ምኞቱን ለማሳካት ሲል ከተወሰኑ ሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን የይሖዋ ወኪል በነበሩት በሙሴና በአሮን ላይ ዓመፀ። ቆሬና ከእሱ ጋር ያመፁት ሰዎች የማይገባቸውን የክህነት መብት ለማግኘት በመሞከራቸው ይሖዋ በሞት ቀጣቸው። (ዘኍ. 16:8-11, 31-33) ይሁን እንጂ የቆሬ ልጆች በዓመፁ ከእሱ ጋር አልተባበሩም። በመሆኑም አምላክ ልጆቹን በአባታቸው ኃጢአት ተጠያቂ አላደረጋቸውም። ለይሖዋ ታማኝ በመሆናቸው ሕይወታቸው ሊተርፍ ችሏል።—ዘኍ. 26:10, 11
ይሁን እንጂ የአሥርቱ ትእዛዛት ክፍል የሆነው በዘፀአት 20:5 ላይ የሚገኘው ማስጠንቀቂያስ ምን ትርጉም አለው? አሁንም በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ እንመልከት። ይሖዋ የሕጉን ቃል ኪዳን ለእስራኤል ብሔር ሰጠ። እስራኤላውያን ቃል ኪዳኑን ከሰሙ በኋላ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው ተናገሩ። (ዘፀ. 19:5-8) በዚህ መንገድ ብሔሩ በጠቅላላ ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና መሠረተ። በመሆኑም በዘፀአት 20:5 ላይ የሚገኙት ቃላት የተነገሩት ለብሔሩ በጠቅላላ ነበር።
እስራኤላውያን ለይሖዋ ታማኝ ሲሆኑ መላው ብሔር የተትረፈረፈ በረከት ያገኝ ነበር። (ዘሌ. 26:3-8) ለይሖዋ ታማኝ ባይሆኑስ? የእስራኤል ብሔር ይሖዋን ትቶ የሐሰት አማልክትን መከተል ሲጀምር ይሖዋም ለብሔሩ በረከት መስጠቱንና ጥበቃ ማድረጉን አቆመ፤ በዚህም የተነሳ ሕዝቡ ለመከራና ለሥቃይ ተዳረገ። (መሳ. 2:11-18) እርግጥ ነው፣ ብሔሩ ጣዖት አምላኪ ቢሆንም ታማኝነታቸውን የጠበቁና አምላክን የታዘዙ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። (1 ነገ. 19:14, 18) ለይሖዋ ታማኝ የነበሩት ሰዎች በብሔሩ ኃጢአት የተነሳ አንዳንድ ችግሮች ደርሰውባቸው ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች ፍቅራዊ ደግነቱን አሳይቷቸዋል።
እስራኤላውያን የይሖዋን መመሪያዎች በመጣስ አስከፊ ድርጊቶችን በመፈጸማቸው የይሖዋ ስም በአሕዛብ መካከል እንዲሰደብ ባደረጉበት ጊዜ ይሖዋ ወደ ባቢሎን በምርኮ እንዲወሰዱ በመፍቀድ ቀጣቸው። እርግጥ ነው፣ ይህን ቅጣት የተቀበሉት ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቡ በአጠቃላይ ነበር። (ኤር. 52:3-11, 27) በእርግጥም የእስራኤል ብሔር በአጠቃላይ የፈጸመው በደል በጣም ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ በዘፀአት 20:5 ላይ እንደተገለጸው ሦስትና አራት ምናልባትም ከዚያ የሚበልጡ ትውልዶች በአባቶቻቸው ኃጢአት የተነሳ መከራ እንደደረሰባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።
ወላጆች በፈጸሙት ስህተት የተነሳ የቤተሰቡ አባላት ችግር እንደደረሰባቸው የሚያሳዩ ታሪኮችም በአምላክ ቃል ውስጥ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሊቀ ካህናቱ ዔሊ “ምናምንቴዎች” ተብለው የተጠሩት መጥፎ ሥነ ምግባር ያላቸው ልጆቹ ካህናት ሆነው እንዲቀጥሉ በመፍቀዱ ይሖዋ በጣም ተቆጥቶ ነበር። (1 ሳሙ. 2:12-16, 22-25) ዔሊ ከይሖዋ ይልቅ ልጆቹን በማክበሩ አምላክ የዔሊ ቤተሰብ ከሊቀ ካህንነት አገልግሎት እንደሚያስወግዳቸው ተናገረ፤ ከዔሊ በኋላ አራተኛ ትውልድ የነበረው አብያታር ከክህነት አገልግሎት ሲወገድ ይህ ፍርድ ፍጻሜውን አግኝቷል። (1 ሳሙ. 2:29-36፤ 1 ነገ. 2:27) የግያዝ ታሪክም በዘፀአት 20:5 ላይ ለሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ምሳሌ ይሆነናል። ግያዝ፣ ከለምጽ ተፈውሶ ከነበረ ንዕማን የተባለ ሶርያዊው አዛዥ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ሲል የኤልሳዕ አገልጋይ በመሆን ያገኘውን ሥልጣን አላግባብ ተጠቅሞ ነበር። ይሖዋ በኤልሳዕ አማካኝነት በግያዝ ላይ “የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ ይጣበቃል፤ ለዘላለምም ወደ ዘርህ ይተላለፋል” የሚል ፍርድ በየነ። (2 ነገ. 5:20-27) በመሆኑም ግያዝ የፈጸመው ስህተት ያስከተለው መዘዝ ለዘሮቹም ተረፈ።
ይሖዋ፣ ፈጣሪና ሕይወት ሰጪ እንደመሆኑ መጠን ትክክልና ተገቢ የሆነውን ቅጣት የመወሰን ሙሉ መብት አለው። ከላይ የተጠቀሱት ታሪኮች እንደሚያሳዩት አያት ቅድመ አያቶች የሠሩት ኃጢአት መዘዙ ለልጆቻቸው ወይም ለዘሮቻቸው ሊተርፍ ይችላል። ያም ቢሆን ይሖዋ “የመከረኞችን ጩኸት [ስለሚሰማ]” እሱን ከልባቸው የሚፈልጉት ሰዎች ሞገሱን የሚያገኙ ከመሆኑም ሌላ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከሥቃያቸው እፎይታ ያገኛሉ።—ኢዮብ 34:28
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቆሬና ከእሱ ጋር የተባበሩት ዓመፀኞች ለድርጊታቸው ተጠያቂ ሆነዋል