ታስታውሳለህ?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
• ልጆችህን ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርገህ እንድታሳድግ ምን ሊረዳህ ይችላል?
ልጅህ ኃላፊነት የሚሰማው ሆኖ እንዲያድግ “አርዓያ” ሁን። (ዮሐ. 13:15) በምትጠብቅበት ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁን፤ ልጁ እያደገ ሲሄድ በንጽሕና አጠባበቅ፣ ሰዓት በማክበርና በትምህርት ቤት ሥራ ረገድ የበለጠ ልትጠብቅበት ትችላለህ። ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ለማሠልጠን ግልጽ መመሪያ ስጠው።—5/1 ከገጽ 19-20
• አምላክ አሮንን የወርቅ ጥጃ በመሥራቱ ያልቀጣው ለምንድን ነው?
አሮን፣ አምላክ የጣዖት አምልኮን አስመልክቶ የሰጠውን ሕግ ጥሷል። (ዘፀ. 20:3-5) ያም ሆኖ ሙሴ ለአሮን ምልጃ ያቀረበ ሲሆን ምልጃውም “ታላቅ ኃይል” ነበረው። (ያዕ. 5:16) አሮን የታማኝነት ታሪክ አስመዝግቦ ነበር። በተጨማሪም ጥጃውን የሠራው በሕዝቡ ግፊት ቢሆንም በኋላ ላይ ከሌዊ ልጆች ጋር በመሆን ከይሖዋ ጎን መቆሙ ጥጃውን የሠራው አምኖበት እንዳልነበር ያሳያል። (ዘፀ. 32:25-29)—5/15 ገጽ 21
• መጽሐፍ ቅዱስ ወርቅ ይገኝበታል ብሎ የሚናገርለት ኦፊር የተባለው ቦታ የት ነበር?
ሰለሞን ከኦፊር ወርቅ ለማስመጣት በዔጽዮንጋብር መርከቦች አሠርቶ ነበር። (1 ነገ. 9:26-28) ይህ ወደብ ይገኝ የነበረው በአቃባ ባሕረ ሰላጤ ጫፍ ላይ አሊያም በቀይ ባሕር ላይ በአሁኗ ኤላት ወይም አቃባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነበር። በመሆኑም ኦፊር የሚገኘው በቀይ ባሕር አጠገብ ባለው የዓረብ ምድር ወይም በአፍሪካ አሊያም በሕንድ የባሕር ዳርቻዎች ሊሆን ይችላል።—6/1 ገጽ 15
• የገለዓድ “በለሳን” ምን ያመለክታል? (ኤር. 8:22 NW)
የበለሳን ዘይት ከተለያዩ ዕፅዋቶች የሚገኝ ጥሩ መዓዛና ሙጫነት ያለው ዘይት ነበር፤ ይህ ዘይት ከሚገኝባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ በዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ የሚገኘው የገለዓድ ምድር ነበር። በለሳን የመፈወስ ባሕርይ ስለነበረው ቁስል ላይ ይቀባ ነበር። የእስራኤል ብሔር የነበረበት አሳዛኝ ሁኔታ ፈውስ እንዲፈልግ ሊያነሳሳው ይገባ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ እንዲህ አላደረገም። (ኤር. 8:9)—6/1 ከገጽ 21-22
• አንድ ክርስቲያን የትዳር ጓደኛው ምንዝር ሲፈጽም ሁኔታውን ለመቋቋም ምን ሊረዳው ይችላል?
ታማኝ የሆነው የትዳር ጓደኛ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት መሠረት ለመኖር ጥረት እስካደረገ ድረስ ሌላኛው ወገን ምንዝር ሠርቶ ክህደት ቢፈጽም የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማው አይገባም። አምላክ ማጽናኛና ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል። በክርስቲያን ባልንጀሮቻችሁ አማካኝነት ማጽናኛ ሊሰጣችሁ ይችላል።—6/15 ከገጽ 30-31
• የታመመን ሰው ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ጥሩ አዳማጭ ሁኑ። (መክ. 3:7) የሌሎችን ችግር እንደ ራሳችሁ የምትመለከቱና አሳቢ ሁኑ። (ሮም 12:15) የምታበረታቱ ሁኑ እንዲሁም ከመርዳት ወደኋላ አትበሉ። (ቆላ. 4:6፤ 1 ዮሐ. 3:18) ከጓደኛችሁ ጋር ያላችሁ ግንኙነት አይቋረጥ። (ምሳሌ 17:17 NW)—7/1 ከገጽ 10-13
• አምላክ መጀመሪያ እንደሌለው እንዴት ማወቅ እንችላለን?
ሙሴ በጸሎቱ ላይ ይህን ገልጿል። (መዝ. 90:2 የ1980 ትርጉም) በመሆኑም ይሖዋ ‘የዘላለም ንጉሥ’ የሚለው ልዩ ማዕረግ ተሰጥቶታል። (1 ጢሞ. 1:17)—7/1 ገጽ 28
• ልጆቻችሁ የንባብ ፍቅር እንዲያድርባቸው መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?
ፍቅር የሰፈነበት ሁኔታና የወላጆች ምሳሌ የንባብ ፍቅር እንዲያድርባቸው ይረዳሉ። በተጨማሪም መጻሕፍት ስጧቸው። ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ አንብቡ። ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አበረታቷቸው እንዲሁም የምታነቡትን ተወያዩበት። ልጆቻችሁ እንዲያነቡላችሁ አድርጉ፤ ጥያቄም እንዲጠይቋችሁ አበረታቷቸው።—7/15 ገጽ 26
• ኢየሱስ የታመመውን ወዳጁን አልዓዛርን ለመፈወስ ቶሎ ያልሄደው ለምን ነበር?
ኢየሱስ ሲደርስ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ኢየሱስ በመቆየቱ ስለ አባቱ ጥሩ ምሥክርነት ሊሰጥ ችሏል። በመሆኑም ብዙዎች ሊያምኑ ችለዋል። (ዮሐ. 11:45)—8/1 ከገጽ 14-15
• ‘በኰረብታ ላይ የተሠሩ መስገጃዎች’ ምን ነበሩ?
አብዛኛውን ጊዜ በኮረብታ ላይ ያሉ ስፍራዎችን ወይም የሐሰት አምልኮ የሚካሄድባቸውን ቦታዎች ያመለክታሉ። አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ ቦታዎች ላይ አምላክ የሚያወግዛቸውን ልማዶች ለማከናወን መሠዊያዎች፣ ቅዱስ ዓምዶች ወይም ምሰሶዎች እንዲሁም ሌሎች ሃይማኖታዊ ማስጌጫዎችና ዕቃዎች ይቆሙ ነበር። (ዘኍ. 33:52)—8/1 ገጽ 23